2018-07-20 09:32:00

ቅድስት መንበር ከቻይና መንግሥት ጋር የምታደርገውን ውይይት አጠናክራ ትቀጥላለች


ቅድስት መንበር ከቻይና መንግሥት ጋር የምታደርገውን ውይይት አጠናክራ ትቀጥላለች

ከቻይና መንግሥት ጋር የሚደረጉት ውይይቶች የጋራ መተማመን ላይ ለመድረስ የሚያስችሉ አነስተኛ እርምጃዎች ናቸው።

ቫቲካን ከቻይና መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ውይይት የምታደርገው ለምንድነው? በቻይና የሚኖሩ ካቶሊኮች ምንም እንኳን ከፍተኛ የሆነ ስቃይ ቢደርስባቸውም ለእምነታቸው ታማኝ ሆነው ቆይተዋል። ታዲያ እንደነዚህ ዓይነት ውይይቶች ምን ሊያስገኙ ይችላሉ?

ውይይቶች ለቤተክርስቲያን ሕይወት መሠረታዊ የሆኑ አስፈላጊ ነገሮች ናቸው። ውይይት በቤተክርስቲያኗ ውስጥም ሆነ በአለም ውስጥ ካለው ግንኙነት አኳያ የቤተክርስቲያኗን የአኗኗር ዘዴ የሚደግፍ አስፈላጊ ነገር ነው። መወያየት ማለት ከሕብረተሰብ፣ ከሃይማኖቶች እና ከባህሎች ጋር ግንኙነት መፍጠር ማለት ነው። የሁለተኛው የቫቲካን ጉባሄ ሰነድ እንደ ሚያመለክተው ውይይት ሐዋሪያዊ የሆነ ተግባር መሆኑን የገለጸ ሲሆን ይህ ውይይት በብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ብቻ የሚካሄድ ሳይሆን ነገር ግን ክርስቲያን ካልሆኑ የማኅበርሰብ ክፍሎች፣ ከሲቪል ባለስልጣኖች እና ከሁሉም በጎ ፈቃድ ካላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር የሚደረግ እንደ ሆነ ይገልጻል። ከሁለተኛው የቫቲካን ጉባሄ ሰነዶች መካከል “በዚህ ዘመን የምትገኝ ቤተክርስቲያን” በሚለው ሐዋሪያዊ ሕገ-ደንብ (Gaudium et Spes no.21) ላይ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ እንዳሰፈረው “ለሁሉም ሰዎች፣ አማኞች እና እምነት የሌላቸው ሰዎች ጭምር አብሮ የሚኖሩባትን ዓለም ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት የራሳቸውን አስተዋጾ ማድረግ ይኖርባቸዋል፣ ይህ ያለእውነተኛ እና በጥበብ መንፈስ ከሚደረግ ውይይት ውጪ እውን ሊሆን አይችልም (21) ይላል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ 6ኛ “Ecclesiam Suam” በአማሪኛው በግርድፉ ሲተረጎም (የራሱ ቤተክርስቲያን) በሚል አርእስት በጻፉት ሐዋሪያዊ መልእክት ላይ ይህንን በተመለከተ ተመሳሳይ በሆነ መልኩ “ቤተክርስቲያን ራሷ ከምትገኝበት ከአለም ጋር መወያየት ይኖርባታል። ቤተክርስቲያን ስትናገር ራሷ መልእክት ትሆናለች” (ቁ.67) በማለት ያስቀምጣል። የካቶሊክ ቤተክርስቲያን “መልካም ፈቃድ ካላቸው፣ በራሷ ውስጥ ካሉ ሰዎች ጋር ይሁን ከራሷ ውጪ ካሉ ሰዎች ጋር የሚደረጉትን ውይይቶች ለመደገፍ ዝግጁ ናት” (97)።

በሰዎች፣ ተቋማት እና በማህበረሰቦች መካከል የሚደረጉ ውይይቶች የጓደኝነት ስሜት ሊፈጥር የሚችል የእውቀት ሽግግር እንዲኖር ያደርጋል። በማነኛውም ሁኔታ ገንቢ የሆነ ውይይት ለማድረግ በቅድሚያ መተማመን ያስፈልጋል። የጋራ መተማመን የብዙ ትናንሽ የሚባሉ እርማጃዎች፣ እንቅስቃሴዎች እና ግንኙነቶች ፍሬ ሲሆን ይህም በተደጋገሚ በረጋ መንፈስ እና በከፍተኛ ጥበብ የሚፈጸም ተግባር ሊሆን ይገባል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በግንቦት 8/2009 ዓ.ም እንደ ተናገሩት “ሁልጊዜም ቢሆን ያልተዘጉ በሮች አሉ"።

በቅርብ ጊዜያት የነበሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ለምሳሌም ብጹዕ ጳውሎስ 6ኛ ከቻይና ጋር ጥንቃቄ የተሞላ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲጀመር በማድረግ በቀጣይነት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ እና ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በኔዴክቶስ 16ኛ ከቻይና መንግሥት ጋር የሚደረገውን ውይይት ውጤታማ እንዲሆን ግልጽ አቅጣጫ በመስቀመጣቸው የተነሳ  ምስጋና ይድረሳቸውና በአሁኑ ወቅት በቅድስት መንበር እና በቻይና መንግሥት መካከል በተወሰነ መልኩም ቢሆን ውይይት ለማድረግ የተቻለ ሲሆን እያንዳንዱ ውይይት የራሱ የሆነ አዲስ መንገድ የከፈተ እና በሚገነባው የጋራ ግንኙነት ላይ የራሱን አዲስ ጡብ  ወይም የመሰረት ድንጋይ ያስቀመጠ በተስፋ የተሞላ የመነቃቂያ ሐሳቦችን ያፈለቀ እና እንቅስቃሴዎች እንዲጀመሩ ያስቻለ አጋጣሚ ነው። በጣም በቅርብ ጊዜ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስን ግላዊ ሕይወት፣ አስተምህሮ እና አቀራረብ በመመልከት የቻይንን ጨምሮ በብዙ ሕዝቦች እና ሀገራት ውስጥ የሚኖሩ ሁሉ የውይይት መድረኮች እንዲከፈቱ በማበረታታት ላይ ናቸው።

የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ውይይትን በራሱ እንደ አንድ መቋጫ ወይም መደምደሚያ ግብ አድርጋ አትመለከትም። ያላትን ሁሉ አቅም ተጠቅማ የፖለቲካ እና የዲፕሎማሲ ጥቅሞችን ለማግኘት “አስፈላጊ የሆኑትን መሰረታዊ መርሆች አሳልፋ ለመስጠት ተዘጋጅታለች ማለትም አይደለም። ይህንን ጉዳይ ከቻይና ጋር በተያያዘ መልኩ ስንመለከተው በቻይንና በሚገኙ የካቶሊክ ማኅበርሰቦች ላይ የደረሰውን  መከራ መርሳት ማለት አይደለም። ቤተክርስቲያን የምታደርጋቸው ውይይቶች ሁልጊዜም ቢሆን በእውነት እና በፍትህ ላይ የተመሰረቱ፣ ከሰው ልጅ ጋር ሊነጣጠል በፍጹም የማይችለውን መልካም ጎን እና መሠረታዊ መብቶችን በማስከበር ላይ የተመሰረቱ መሆን አለባቸው። አንድ ግልጽ ሊሆን የሚገባው አስፈላጊ ነገር ቤተክርስቲያን በቻይና የምታደገው ተልዕኮ የመንግሥት መዋቅሮችን ወይም አስተዳደሮችን ለመቀየር ወይም የፖለቲካ ኃይል ለማዋቀር ወይም ባለሥልጣኖችን ለመቃወም ያለመ እንዳልሆን ልብ ሊባል ይገባዋል። ቤተክርስቲያን ተልዕኮዋን  በፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች አከባቢ የምታደግ ከሆነ የራሷን ትክክለኛ ማንነት በመካድ ከብዙ የፖሌቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ልክ እንደ አንዱ ተፎካካሪ በመሆን፣ መልኮታዊ የሆነውን ጥሪ በመርሳት ወይም በመካድ፣ በእንደነዚህ ዓይነት እንቅስቃሴዎች ውስጥ በመግባት ለጊዜያዊ ጥቅሞች ማስፈጸሚያንት ያለሙ ተግባራት ውስጥ በፍጹም አትሳተፍም።

ትክክለኛ እና ሐቀኛ የሆኑ ውይይቶች ቤተክርስቲያን በማኅበርሰቡ ውስጥ ሆና መሥራት እንድትችል የሚያደርጋት ሲሆን ይህም ለካቶሊኮች ሕጋዊ የሆነ ጥበቃዎችን በማድረግ የጋራ ጥቅሞች ዙሪያ እንድትሠራ ያስችላታል። በዚህ አግባብ ቤተክርስቲያን የትችት ቃላቶችን በምትናገርበት ወቅት ዓላማዋ ውዝግብ ለመፍጠር ሳይሆን ትክክለኛ እና ገንቢ መንፈስ ያለው ኅብረተሰብ ለመፍጠር በማሰብ የምታደገው ነው። ትችቶች ተጨባጭ የሆኑ የሐዋሪያዊ ሥራዎች የፍቅር መገለጫ ተመክሮዎች ተደርገው ሊቆጠሩ ይችላሉ፣ ምክንያቱም ደካማ የሆኑ ሰዎችን ስቃይ፣ ድምጻቸውን ለማሰማት የተሳናቸው ሰዎች ድምጻቸው እንዲሰማ ጥንካሬን ስለሚፈጥር ነው።

ከቻይና ጋር በተያያዘ መልኩ የቅድስት መንበር ያላት አቋም እና እምነት በአክብሮት እና በእውነተኛ መንፈስ የሚደረጉ ውይይቶች ምንም ያህል አስቸጋር እና አደገኛ ቢሆኑም እንኳን በእዚህ አኳኅን የሚደረጉ ውይይቶች እንዲካሄዱ ምቹ የሆኑ ሁኔታዎች በማሰናዳት እንዲካሄዱ የምትጥር ሲሆን ቀጣይነት ባለው መልኩ ውይይቶችን በማድረግ ሐሳቦችን በመቀያየር እና በመግባባት ግንዛቤን በመፍጠር በመኃል ያሉትን አለመግባባቶችን በመፍታት ገንቢ የሆነ ግንኙነት እንደ ሚፈጠር ታምናለች።

ቅድስት መንበር “በተለሳለሰ ኃይል” በዓለም ደረጃ እያከናወነች የምትገኘውን እንቅስቃሴ ቻይና ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ እይተከታተለች መሆኑን የሚያሳዩ የተለያዩ ምልክቶች አሉ። የቻይና ታሪክ በተመሳሳይ መልኩ እየቀጠለ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን  በቤተክርስቲያን ውስጥ በፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ላይ የሚሠሩ ሰዎች በጥበብ የተሞላ ውሳኔዎችን ማድረግ ይኖርባቸዋል። የቅድስት መንበር ከቻይና መንግሥት ጋር ለሩብ ምዕተ አመታት ያህል ውይይት ስታደግ የቆየችሁ በዚሁ ምክንያት ነው፣ በዘመናት ውስጥ ያሉትን ምልክቶች ለማንበብ ለሚፈልጉ እና በታሪክ ውስጥ የእግዚአብሔርን መገኘት ለመገንዘብ ለሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ የቤተክርስቲያኗ ሐዋሪያዊ ዓላማ ይህ መሆኑን ያሳያል።

 








All the contents on this site are copyrighted ©.