2018-07-16 14:55:00

19ኛውን የምስራቅ አፍሪካ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤዎች መግለጫ


19ኛው የምስራቅ አፍሪካ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤዎች ህብረት ጉባኤን በማስመልከት ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን 19ኛውን የምስራቅ አፍሪካ ጳጳሳት ጉባኤዎች ህብረት (አመሰያ) ጉባኤ ከሐምሌ 6 - 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ለመጀመሪያ ጊዜ ታስተናግዳለች፡፡ የመክፈቻ ስነስርዓቱ በሐምሌ 8 ከጠዋቱ 3፡00 ጀምሮ በሚሊኒየም አዳራሽ ከቅድስት መንበር ቫቲካን የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ብፁዕ ወቅዱ አቡነ ፍራንቼስኮስ ተወካይና የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች በክብር እንግድነት እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ መዕምናን በተገኙበት የሚደረግ ሲሆን ጉባኤውም በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ) የመሰብሰቢያ አዳራሽ በቀጣዮቹ ቀናት ይካሄዳል፡፡ አመሰያ 9 አባል ሀገራት ያሉት ሲሆን እነሱም ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ዛምቢያና ማላዊ ሲሆኑ ሶማሊያና ጅቡቲ ደግሞ ተባባሪ አባላት ናቸው፡፡ ከ300 በላይ የሚሆኑ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ገዳማዊያንና ገዳማዊያት ምእመናንና የአጋር ድርጅቶች ፕሬዚደንቶች ከምስራቅ አፍሪካና ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በጉባኤው ለመሳተፍ ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ፡፡

የ19ኛው ጉባኤ መሪ ቃልም በእግዚአብሔር ላይ የተመሠረተ ሕያው ብዝኃነት ሰብአዊ ክብርና ሰላማዊ አንድነት ለምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የሚል ነው፡፡ የሰው ልጆች በዘር፣ በቋንቋ፣ በቀለም መለያየት ታላቅ የእግዚአብሔር የፍጥረት ሥራ ጥበብ መገለጫ ነው፤ ሁላችንንም እግዚአብሔር በአምሳሉ የፈጠረን ሲሆን ልዩነታችንም ከፈጣሪያችን ያገኘነው ነው፡፡ ነገር ግን ይህንን ልዩነት መነሻ በማድረግ በተለያዩ የምስራቅ አፍሪካ ክፍሎች ግጭቶች ተነስተው ንብረት ይወድማል፣ ብዙዎች ይፈናቀላሉ፣ የብዙዎች ሕይወት ይጠፋል፡፡ ልዩነታችን እርስ በእርስ የምንማማርበት እሴታችን እንደመሆን ፈንታ የጥላቻ ምክንያት ሲሆን ይታያል፡፡ የምስራቅ አፍሪካ ካቶሊክ ጳጳሳትም ይህንን አርእስት ለጉባኤያቸው መሪ ቃል አድርገው የመረጡት በዚህ ወቅት በአህጉራችን በተለይም በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ህዝቦች ውብ የሆነውን ብዝኃነታችን የእግዚአብሔር ስጦታ እንደሆነ ተገንዝበው በእግዚአብሔር ላይ የተመሰረተ የሰው ልጆችን ሁሉ ክብር የጠበቀ ሰላማዊ አንድነት እንዲኖር በተለይ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምን መስራት አለባት በሚለው ዙሪያ ለመወያየትና መፍትሄ ለማምጣት በማሰብ ነው፡፡ በተለይም የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ከሌሎች የእምነት ተቋማት ጋር፣ ከመንግስታትና ከአፍሪካ ሕብረት ጋርም በመተባበር  በጋራ እንዴት መስራት እንዳለባት በዚህ ጉባኤ ይወያያሉ፡፡

19ኛው የአመሰያ ጉባኤ ለቀጣዮቹ 4 ዓመታት በምስራቅ አፍሪካ የምትገኘው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ለምታከናውናቸው ሐዋሪያዊና ማህበራዊ ስራዎች ብዝኃነትን በተገቢው መንገድ ማስተናገድ እንዲቻል አቅጣጫ የምታሳይበትና ጳጳሳት ልዩ ልዩ ውሳኔዎች የሚያስተላልፉበትም ጭምር እንደመሆኑ መጠን በምስራቅ አፍሪካ ያሉ ነባራዊ ሁኔታዎችን በግልፅ የሚዳስሱ ጥናታዊ ፅሁፎች በሊቃዉንት ይቀርባሉ፡፡ ወጣቶችና ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል የሚሏቸዉን ጉዳዮች ለውይይት ያቀርባሉ የመፍትሄ ሃሳቦችንም ያካፍላሉ፡፡ በተለይም የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የሆኑት የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ፍራንቼስኮስ ተወካይ ከቅድስት መንበር ቫቲካን በመምጣት በጉባኤው ስለሚሳተፉ በሚተላለፉት ውሳኔዎች ሁሉ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቡራኬ ይኖራል፡፡ በተለይም በቅርቡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ስለሃገራችን ኢትዮጵያና ስለ ጎረቤት ሃገር ኤርትራ ሰላማዊ ግንኙነት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ጸሎት ያደረሱ ሲሆን ይህንን የሰላም ግንባታ ጥረት በተመለከተም የእርሳቸው ልዩ መልዕክትና ቡራኬ ይኖራል፡፡

እንደሚታወቀው በቀጠናችን በተለያዩ ምክንያቶች ግጭቶች ሲፈጠሩ ቤተክርስቲያናችን ከህዝብ ጎን ቆማ የሰላም ድልድይ በመሆን ታገለግላለች፤ በቅርቡ በደቡብ ሱዳን ይህንኑ እያደረገች የቆየች ሲሆን ከዚህ ቀደም በአገራችን ኢትዮጵያና ጎረቤት ኤርትራ ግጭት በተነሳበት ጊዜም የሁለቱ ሀገራት የጳጳሳት ጉባኤዎች በየጊዜው በመገናኘት የህዝቡን ሁኔታ በማንሳት ሲወያዩና በጋራ የሰላም ጸሎት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ አሁንም የሰላም ድልድይ ሆና ለመቀጠል የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የምታደርገውን ጥረት ሁሉም በጎ ፈቃድ ያላቸው ወገኖች ሁሉ እንዲተባበሩ ጥሪዋን ታቀርባለች፡፡ ምእመናንም እንደተለመደው ሁሉ በጸሎት መትጋታቸውን እንዲቀጥሉ አደራ ትላለች፡፡

በመጨረሻም የአመሰያ አባል ሀገራት ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ደናግልና ምእመናን ሁሉ የአመሰያን ጉባኤ እንድናስተናግድና በታሪክ የሚያውቋትንና የሚወዷትን ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ እድል እንድንፈጥርላቸው ለዓመታት ሲመኙ ቆይተው አሁን በእግዚአብሔር ፈቃድ ጊዜው ደርሶ እነርሱን ለመቀበል ተዘጋጅተናል፡፡ እንግዶቻችን የሁላችንም ኢትዮጵያውያን እንግዶች ስለሆኑ የሀገራችንን መልካም መንፈሳዊነት፣ ባህልና እሴት ከእነርሱ ጋር ተካፍለን መልካምና ለሕይወት ጠቃሚ የሆነ ትዝታ ይዘው ወደ ሀገራቸው በሰላም እንዲመለሱ በምናደርገው መስተንግዶ የሁሉም ትብብር እንደማይለየን እናምናለን፡፡ ላለፉት 4 ዓመታት ለተደረገው ዝግጅት መላው የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ደናግል፣ ምዕመናን፣ በጎ በጎ ፈቃድ ያለቸው ግለሰቦችና ድርጅቶች እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግስት ድጋፍና ጥረት ሁሉ በእግዚአብሔር ስም እናመሰግናለን፡፡ ይህን የሰላም ጥሪ የያዘ የአመሰያ መልዕክትንም ለህዝብ እንዲደርስ ስለምታደርጉ የሚዲያ ባለሞያዎችና ተቋማትን እጅግ እናመሰግናለን፤ እግዚአብሔር አገልግሎታችሁን ይባርክ፡፡

ሁላችንም በትብብር ለመስራት ይረዳን ዘንድም የጉባኤው ውሳኔዎችና የምስራቅ አፍሪካ የጳጳሳት መልዕክትንም ለመላው የምስራቅ አፍሪካና የአገራችን ህዝብ እናሳውቃለን፡፡ ጉባኤው በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ በአህጉራችን በተለይም በቀጠናችን ማንኛውንም ዓይነት ልዩነቶችና ጥላቻ እንድናስወግድ እንዲሁም በሁከትና ጠብ ምክንያት የተፈጠሩ ቁስሎች እንዲፈወሱ፣ ይቅር ባይነት እንዲስፋፋ፣ የተለያዩ ነገዶችና የዘር ልዩነቶች የእግዚአብሔር ፀጋ መሆኑን እንድንረዳ እንዲያደርገንና በእግዚአብሔር የተመሰረተ ህያው ብዝኃነት ሰብአዊ ክብር ሠላማዊ አንድነት በምሥራቅ አፍሪካ እንዲነግስ የእግዚአብሔር መልካም ፍቃዱ ይሁን፡፡ እያንዳንዳችንም ለዚህ ዓላማ መሣካት ግዴታችንን እንወጣ፤ በጸሎትም እንትጋ፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!








All the contents on this site are copyrighted ©.