2018-07-12 15:58:00

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዓለም የወጣቶች ቀን በዓል ላይ እንደሚገኙ ታወቀ።


ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዓለም የወጣቶች ቀን በዓል ላይ እንደሚገኙ ታወቀ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከጥር 14 እስከ ጥር 19 ቀን 2011 ዓ. ም. በመካከለኛው የላቲን አሜሪካ አገር በፓናማ በሚከበረው የመላው ዓለም ወጣቶች በዓል ላይ እንደሚገኙ፣ በቅድስት መንበር የህትመት ክፍል አስታወቀ።

የዚህን ዝግጅት ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ።

የቅድስት መንበር የሕትመት ክፍል ተጠሪ የሆኑት አቶ ግረክ ቡርኬ፣ ባለፈው ሰኞ ዕለት እንዳረጋገጡት፣  ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከጥር 14 እስከ ጥር 19 ቀን 2011 ዓ. ም. በፓናማ በሚከበረው የመላው ዓለም ወጣቶች በዓል ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል። ቅዱስነታቸው በዓሉ ወደ ሚከበርበት አገር ከአንድ ቀን አስቀድመው እንደሚደርሱ፣ የቅድስት መንበር የሕትመት ክፍል ሃላፊው አከለው ገልጸዋል።  ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ከፓናማ መንግሥት እና ከፓናማ ካቶሊካውያን ብጹዓን ጳጳሳት የቀረበላቸውን ግብዣ በደስታ እንደተቀበሉ የሕትመት ክፍል ሃላፊው ገልጸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ዓለም አቀፍ የወጣቶችን በዓል ሲካፈሉ ይህ ሦስተኛቸው ሲሆን፣ የመጀመሪያቸው የሆነውን የወጣቶች በዓል የተካፈሉት፣ ከስመተ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትነት ጥቂት ወራት በኋላ፣ በብራዚል፣ በ2005 ዓ. ም. የተከበረውን ሲሆን ቀጥሎም፣ በ2008 ዓ. ም. በፖላንድ እንደነበር ታውቋል።

በየሦስት ዓመቱ የሚከበረው የመላው ዓለም ወጣቶች በዓል፣ ወጣቶች ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት እና ከዓለም ዙሪያ ከሚሰበሰቡ ወጣቶች ጋር እርስ በርስ የሚገናኙበት እና የሚተዋወቁበት ተናፋቂ በዓል መሆኑ ታውቋል። ይህ አጋጣሚ ወጣቶች የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ኩላዊነትን በግልጽ የሚያዩበት እና እምነታቸውን የሚመሰክሩበት አጋጣሚ እንደሆነ ታውቋል።

የፓናማው ፕሬዚደንት፣ ክቡር አቶ ዩዋን ካርሎ ቫሬላ፣ ያለፈው ሰኞ በቲዩተር ማሕበራዊ መገናኛ ድረ ገጻቸው እንደገለጹት፣ በፓናማ የሚከበረው የዓለም ወጣቶች በዓል፣ ከዓለም ዙሪያ የሚመጡ ወጣቶች የፓናማን ሕዝብ ደስታን የሚቋደሱበት እንደሆነ ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በፓናማው የዓለም ወጣቶች በዓል ላይ እንደሚገኙ ያለፈው ሰኞ ይገለጽ እንጂ ቅዱስነታቸው በኢንተር ኔት ድረ ገጽ በተዘጋጀላቸው የመመዝገቢያ ቅጽ ላይ አስቀድመው ስማቸውን ያሰፈሩት፣ እሁድ የካቲት 4 ቀን 2010 ዓ. ም. መሆኑ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዕለቱ እንደተናገሩት፣ በፓናማ በሚከበረው የዓለም ወጣቶች በዓል ላይ ለመገኘት የማደርገው ጉዞ ንግደት ወይም መንፈሳዊ ጉዞ ነው ብለዋል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ ለመላው የዓለም ወጣቶች ባስተላለፉት መልዕክት ወጣቶች በበዓሉ ላይ እንዲገኙ ጠርተው፣ ወደ ፓናማ የሚሄዱትም ይሁን የማይሄዱት በሙሉ ከበዓሉ የሚገኘውን ጸጋ በመጋራት ለእምነታቸው ታማኞች በመሆን በያሉበት ሥፍራ እንዲያከብሩት አስጻስበዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በየካቲት ወር 2009 ዓ. ም. ባስተላለፉት የቪዲዮ ምስል መልዕክታቸው፣ ወጣቶች ወደ ፓናማ በሚያደርጉት መንፈሳዊ ጉዞ ወቅት ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ጸሎታቸውን እንዲያቀርቡና እንዲያስታውሷት ተማጽነዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዚህ መልዕክታቸው፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በእምነቷ ሙላት የተነሳ ከቦታ ወደ ቦታ በመጓዝ፣ በሕይወቷ ሁሉ የእምነትን ታላቅነት መስክራለች ብለዋል።

 

ከዮሐንስ መኰንን     








All the contents on this site are copyrighted ©.