2018-07-09 13:52:00

ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮስ “የተጠመቁ ብዙ ሰዎች እግዚኣብሔር የለሽ የሚያስመስል ሕይወት በመኖር ላይ ይገኛሉ”።


ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮስ፡ ምስጢረ ጥምቀት የተቀበሉ ብዙ ሰዎች እግዚኣብሔር የለሽ የሚያስመስል ሕይወት በመኖር ላይ ይገኛሉ ማለታቸው ተገለጸ። ቅዱስነታቸው ይህንን የተናገሩት በትላንትናው እለት ማለትም በሐምሌ 01/2010 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥርስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን እና የሀገር ጎብኚዎች በእለቱ ከማርቆስ ወንጌል ከምዕራፍ 6፡1-6 ላይ ተወስዶ በተነበበው እና ነቢይ በገዛ ሀገሩ አይከበርም በሚል አርእስት በቀረበው የእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ መሰረቱን ያደረገ እንደ ነበረ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን እግዚአብሔር የእያንዳንዱን የሰው ልጆች  እቅድ ይቀይራል፣ ሁልጊዜም ከእርሱ ጋር እንድንወያይ ይጋብዘናል ካሉ በኃላ አካላዊ መግለጫዎችን ብቻ መጠቀም በቂ እንዳልሆነ ጠቅሰው በእውነተኛ ልብ ወደ ኢየሱስ መቀረብ እና ለቃሉ ታማኝ መሆን ያስፈልጋል ማለታቸውን ለመረዳት ተችሉዋል።

ክቡራን እና ክቡራት አድማጮቻችን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በትላንትናው ዕለት ማለትም በሐምሌ 01/2010 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን እና የሀገር ጎብኚዎች በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተመርኩዘው ያደርጉትን አስተንትኖ ሙሉ ይዘት እንደ ሚከተለው እንስደምጣችኃለን አብራችሁን በመሆን እንድተከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዛሬው እለት የተነበበልን ቅዱስ ወንጌል (ማርቆስ 11-6) ኢየሱስ ወደ ናዝሬት መመለሱን እና በሰንበት ቀን በምኵራብ ማስተማር መጀመሩን የገልጻል። በእዚያም እንደ ደረሰ በየመንደሩ እና በየሰፈሩ እየተዘዋወረ ማስተማር ጀመረ፣ ከእዚያን በኃላ በፍጹም ወደ ገዛ ሀገሩ ተመልሶ አልሄደም ስለዚህ በእዛ ሀገር የሚኖረው መላው ሕዝብ ይህንን የሕዝብ ልጅ ለማዳመጥ የወጡ ሲሆን ይህም ጥበበኛ ጌታ እንደ ሆነ እና በኃይሉ እንደ ሚፈውስ የሚገልጽ ዜና በገሊላ እና ከእዚያ ባሻገር በሚኖሩ ሀገራት ውስጥ ተሰማ። ነገር ግን ይህ ጉዳይ እንደ ስኬት ሊታይ የሚችል ቢሆንም ቅሉ ኢየሱስ ከእዚህ የበለጠ እጅግ አስገራሚ ነገር ማከናወን አልቻለም፣  ጥቂት ሰዎችን ብቻ ፈውሱዋል። ወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ የእዚያን ዕለት ተለዋዋጭነት በዝርዝር ይገልጻል፡ የናዝሬት ሰዎች በቅድሚያ ኢየሱስን አዳመጡት ከእዚያም በጣም ተደነቁ፡ ከእዚያም በኃላ ግራ በተጋባ ስሜት እንዲህ በማለት ጥያቄ ያነሳሉይህ ሰው እነዚህን ነገሮች ከየት አገኛቸው? ይህ የተሰጠው ጥበብ ምንድን ነው? ደግሞም እነዚህ ታምራት እንዴት በእጁ ይፈጸማሉይህ ዐናጢው አይደለምን? የማርያም ልጅ፣ የያዕቆብና የዮሴፍ፣ የይሁዳና የስምዖን ወንድም አይደለምን? በዚህም የተነሣ ተሰናከሉበት” (ማርቆስ 12-3) በመሆኑም ኢየሱስ ምሳሌያዊ በሆነ አገላለጽነቢይ የማይከበረው በገዛ አገሩ፣ በዘመዶቹ መካከልና በቤተ ሰቡ ዘንድ ብቻ ነው” (ማር 64) በማለት መደምደሚያ ላይ  ይደርሳል።

የኢየሱስ የሀገር ዜጎች እንዴት ነው ከመደነቅ ወደ አለማመን ሊሻገሩ የቻሉት? ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ የገባል። በኢየሱስ ትሁት በሆነው አወላለዱ እና አሁን ባለው ከፍተኛ አቅም መካከል ያለውን ልዩነት በማነጻጸር፣ አንድ አናጺ የነበረ ያልተማረ ሰው ከተማሩ ከጸሐፍት በላይ በማስተማሩ እና ተዐምር በመሥራቱ ግራ ይጋባሉ። ለእውነታው ራሳቸውን ከማዘጋጀት እና ከመክፈት ይልቅ ይሰናከላሉ። በናዝሬት ሰዎች ዘንድ እግዚኣብሔር በጣም ትልቅ የሆነ ነገር በመሆኑ የተነሳ ራሱን እንዲህ ዝቅ አድርጎ በአንድ ተራ በሆነ ሰው አማካይነት እንዲህ ይናገራል የሚል ግምት አለንበራቸውም። ይህም ቃል ሥጋ የሆነበት ምስጢር እንዲሰናከሉ አደረጋቸው፣ እግዚአብሔር ሥጋ መልበሱ፣ እንደ ሰው ማሰቡ፣ የሰው እጅን ተጠቅሞ መሥራቱ እና መንቀሳቀሱ፣ በሰው ልብ በመወደዱ፣ እንደ ማነኛውም ሰው የሚጥር የሚተጋ እግዚኣብሔር በመሆኑ ልክ እንደ እያንዳንዳችን የሚበላ እና የሚተኛ በመሆኑ የተነሳ ይህ ጉዳይ ለእነርሱ አስከፊ የነበረ ክስተት ነበር። የእግዚአብሔር ልጅ እያንዳንዱን የሰው ልጅ ቅድ ይሽራል፡ የኢየሱስን እግር ያጠቡት ሐዋሪያት አለነበሩም፣ ነገር ግን የሐዋሪያቱን እግር ያጠበው ኢየሱስ ነበር እንጂ (ዮሐንስ 131.20) ይህ ጉዳይ ለእነርሱ መሰንካል ሆነባቸው እንዳያምኑም አደረጋቸው፣ ይህ ጉዳይ በእዚያን ጊዜ ተፈጽሞ ያለፈ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ነገር ግን በሁሉም ዘመናት ውስጥ ዛሬም ቢሆን በተመሳሳይ መልኩ እይተፈጸመ የሚገኝ ጉዳይ ነው።

ኢየሱስ ያደረጋቸው ለውጦች ትላንትና እና ዛሬም የእርሱ ተከታዮች ለሆኑት ሁሉ ለግለሰብ እና ለማህበረሰብ ማረጋገጫ ይሰጣሉ። እንዲያውም በእኛ ዘመን እውነታን እንዳንቀበል የሚከለክለን ጭፍን ጥላቻን እንድንመለከት ያግዘናል። ዛሬ ጌታ በትህትና እና በትዕግሥት የማዳመጥ እና የመጠበቅ ዝንባሌን እንድንከተል ይጋብዘናል፣ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ጸጋ እኛ ከምንጠብቀው እና በገመትነው መልኩ ሳይሆን በተደጋጋሚ በሚያስደንቅ መንገድ ራሱን ለእኛ ስለሚያቀርብ ነው። ለምሳሌ ስለ የካልካታዋ እማሆይ ትሬዛ እናስብ። በጣም ዝቅ ያሉ እማሆይ ነበሩ- ማንም ሰው ቤሳቤስቲን አይሰጣቸውም ነበር -- እርሳቸው ግን በእየመንገዱ እንዲሞቱ የተተውትን ሰዎች ለመፈለግ በእየጎዳናው ላይ ይዘዋወሩ ነበር። እኝህ ምስኪን እና ትንሽ የሆኑ እማሆይ ትሬዛ በጸሎት ኃይል እና በተግባራቸው ድንቅ የሆኑ ነገሮችን ፈጽመው አልፈዋል። የአንድ ትንሽ እማሆይ ተግባር ቤተክርስቲያን የምታከናውነውን የፍቅር ሥራዎች በከፍተኛ ደረጃ ማሻሻያ እንድታደርግበት አስችሉዋል። አሁን ባለንበት ዘመናችን የተከሰተ ተምሳሌታዊ ተግባር ነው። አምላክ ጭፍን የሆነ ጥላቻን አይቀበልም። እኛን ለመገናኘት የሚመጡትን መለኮታዊ እውነቶችን ለመቀበል ልባችንንና አእምሮአችንን ለመክፈት ጥረት ማድረግ አለብን። እምነት እንድኖረን የሚያመልክት ነገር ነው፡ እምነት ማጣት ደግሞ የእግዚአብሔርን ጸጋ እንዳንቀበል እንቅፋት ይሆናል። ምስጢረ ጥምቀትን የተቀበሉ ብዙ ሰዎች የሚኖሩት ሕይወት ልክ ኢየሱስ እንዳልነበረ የሚያሳይ ዓይነት ሕይወት ነው፣ ወግ እና ስረዓትን ብቻ ይጠብቃሉ ነገር ግን ሕይወታቸው ለኢየሱስ እና ለቅዱስ ወንጌል ያላቸውን እውነተኛ ታማኝነት አይገልጽም። እያንዳንዱ ክርስቲያን እኛ ሁላችን እነዚህን መሠረታዊ የሆኑ ከኢየሱስ ጋር ያለንን ትስስር እንድናጠናክር የሚያደጉንን የአሠራር ክህሎቶች ላይ ከፍተኛ የሆነ ተኩረት መስጠት ይኖርብናል፣ በሕይወታችን በአኗኗራችን ልንመስክር ይገባል የእዚህም ተግባር መሪ  ሊሆን የሚገባው ደግሞ ሁል ጊዜ የበጎ አድራጎት ተግባርን ማከናወን ነው። በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማሪያም አማላጅነት ጌታ የደነደነ ልባችንን እንዲያለሰልስ እና አእምሮአችንን በጥንቃቄ በመመልከት ለእርሱ ጸጋ መክፈት የምንችልበትን፣ ለእውነት እና ለወንጌላዊ መልካም ተልዕኮ እና ለምሕረት ጸጋ ራሳችንን ማዘጋጀት እንችል ዘንድ ጸጋውን እንዲሰጠን በእዚህም ጸጋ ታግዘን ማንንም ሳናገል ለሁሉም ተደራሽ እንድንሆን እንዲረዳን ልንማጽነው የገባል።








All the contents on this site are copyrighted ©.