2018-07-07 18:02:00

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ፣ በመካከለኛው ምስራቅ ሰላምን ማረጋገጥ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው።


ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ፣ በመካከለኛው ምስራቅ ሰላምን ማረጋገጥ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የደቡብ ኢጣሊያ ሀገረ ስብከት ወደ ሆነው፣ ወደ ባሪ ቢቶንቶ ያደረጉትን ሐዋሪያዊ ጉብኝት ከማገባደዳቸው አስቀድመው በቅዱስ ኒኮላስ ባዚሊካ በመገኘት የሚከተለውን መልዕክት አስተላልፈዋል።

ውድ ወንድሞቼ፣

የአብያተ ክርስቲያናት መሪዎች በሕብረት እንድንገናኝ መልካም ጊዜን ለሰጠን አምላካችን ምስጋናዬን አቀርባለሁ። በዚህ አጋጣሚ በመካከለኛው ምስራቅ አገሮች የክርስቲያኖችን ሕብረት እንደገና በማጤን አድናቆትን እንድንቸር በቅተናል። በመካከለኛው ምስራቅ አገሮች የክርስቲያኖች መኖር፣ የሰላም ንጉሥ የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክሮች እንድንሆን ያደርገናል።ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል (ትንቢተ ኢሳ. 9 . 6)ኢየሱስ ክርስቶስ የሰላም አለቃ እንጂ ሰይፍን አላነሳም። ሐዋርያቱንም ሰይፍ እንዲይዙ አላዘዛቸውም። ይልቅስ ሰይፋቸውን ወደ ሰገባው እንዲከቱ ጠይቆአቸዋል። (የዮሐንስ ወንጌል በምዕ. 18 . 11) ቤተ ክርስቲያንነታችን በዓለማዊ አስተሳሰብ በመውደቁ፣ በስልጣንና በሃብት፣ በምቾትም በመታለሉ የተንሳ በፈተና ላይ ወድቋል። ከዚህም በተጨማሪ በሐጢአት በመውደቅ፣ ከእምነት በመራቅ የሕይወት ምስክርነታችን በግልጽ እንዳይታይ ጨለማ ጋርዶታል። ከዚያ ሁሉ እንቅፋት ወጥተን፣ በወንጌሉ ቃል በመታደስ፣ ለመካከለኛው ምስራቅ ሕዝብ፣ የስቃይ ዘመን አብቅቶ እውነተኛ ነጻነት ሳይዘገይ እንዲመጣ እንፈልጋለን። በጌተ ሰማኒ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ተከታዮቹ በሙሉ ለስቃይ ትተውት እንደሸሹ ዓይነት ሳይሆን ወይም አመጽን የሚቀሰቅስ የጦር መሣሪያን ማንሳት ሳይሆን የሰላም አለቃ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን መስለን ራሳችንን ማቅረብ ያስፈልጋል።

በመስቀል ተሰቅሎ የሞተውና በፍቅር ከሞት በመነሳት መልካም ዜና የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ የመጣው ከመካከለኛው የምስራቅ አገር ነው። ለዘመናት የሰዎችን ልብ በፍቅር የማረከው በዓለማዊ ስልጣንና ሃይል በመመካት ሳይሆን በመስቀሉ ሃይል በመመካት ነው። የወንጌሉ ቃል፣ በእግዚብሔር ዕቅድ መሠረት ዘወትር ራሳችንን በማደስ፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ ሆነን የሚያደናቅፉንን እንቅፋቶች እንድናልፍ ያደርገናል። የመካከለኛው ምስራቅ አገር እምነት ጥልቀት ያለው እንደመሆኑ፣ ከማይደርቅ ምንጭ እንድንጠጣ እና እንድንፈወስ ያደርገናል። ይህን የምናውቀው ወደ ክርስትና ምንጭ ወደ ሆነው ወደ ኢየሩሳሌም በምናደርገው መንፈሳዊ ጉዞ፣ እንደዚሁም በግብጽ፣ በዮርዳኖስ፣ በሊባኖስ፣ በሶርያ፣ በቱርክና በእነዚህ አካባቢዎች በሚገኙት ቅዱስ ስፍራዎች አማካይነት ነው።

እርስ በርስ በመደጋገፍ፣ ወንድማዊ ውይይቶችን በማድረግ ላይ እንገኛለን። ይህን ውይይት የምናደርገው የአንድነትን አስፈላጊነት በሚገባ  በመረዳት፣ በልዩነታችንም ሳንፈራ እና ሳንሸማቀቅ ነው። ይህ ሰላም የመላበት ውይይት፣ በግጭት ምክንያት በቆሰለው የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች መካከል መከናወን አለበት። ምክንያቱም ከሁሉ በላይ ለመካከለኛው የምስራቅ አገሮች ሰላምን ከማምጣት በስተቀር ሌላ አማራጭ የለምና። ሃይልን የተጠቀመና ግድግዳን በመገንባት የሚመጣ የተኩስ አቁም ስምምነት ወደ ሰላም ሊመራ አይችልም። ነገር ግን መደማመጥ የሰፈነበት ወይይት ወደ ሰላም መንገድ ይመራል። ስለዚህ አብረን በመጸለይ እና አብረን በመሥራት በአመጽና በግጭት ላይ የበላይነትን ለመቀዳጀት በሕብረት መጓዝ ይኖርብናል። በሕብረት በምናመጣው ሃይል በመታገዝ ወይም ተስፋን በማድረግ፣ በጎ ፈቃድ ባላቸው አብያተ ክርስቲያናት ሰዎች አማካይነት፣ በልዩነታችን ምክንያት የተነሳ ለውይይት ሳንፈራ፣ መልካም ሃሳቦቻቸውን ለማዳመጥ ዝግጁዎች መሆን ያስፈልጋል። ይህን መንገድ በመከተል ብቻ ማንም ያለ ተስፋ እንዳይቀር፣ በልቶ እና ጠጥቶ የሚያድረው ሳይጎልበት፣ ጦርነት ያስከተለው የስቃይ ጩኸት ወደ ደስታ መዝሙር ሊቀየር ይችላል።

ይህ ከሆነ ደግሞ፣ በስልጣን ላይ የተቀመጡትም የራሳቸውን ፍላጎት ከማራመድ ወይም ከማስቀደም ይልቅ ለእውነተኛ ሰላም በቆራጥነት መሥራት ይችላሉ። በጦርነት በሚሰቃዩት በርካታ ሰዎች ስም ጥቂት ትርፍን ወይም ጥቅምን መሰበሰብ ይቁም። የአንድን አገር ሉዓላዊ ድንበርን በመውረር ነዋሪውን ሕዝብ ማፈናቀል ያብቃ። ግማሽ እውነትን ብቻ መናገርን በማዘውተር የሕዝብን ምኞት ማጨለም ይብቃ። ለመካከለኛው ምስራቅ ሕዝብ ምንም ጥቅም በማያስገኝ መንገድ የመካከለኛው ምስራቅ አገሮችን መጠቀም ይቁም።

ጦርነት እንደሆነ፣ ይህን ተወዳጅ የሆነውን የመካከለኛ ምስራቅ አካባቢን ለጉዳት የሚዳርግ መቅሰፍት መሆኑ አልቀረም። በዚህም በድህነት የሚሰቃዩ በርካታ ሰዎች ተጠቂዎች ይሆናሉ። ለዚህም በጦርነት የምትሰቃየውን ሶርያን ማየት በቂ ነው። ጦርነት ስልጣንንን ያለ አግባብ የመጠቀምና  የድህነት ውጤት ነው። የሚሸነፈውም ጀብደኝነትንና ማን አለኝ ባይነትን እንዲሁም ድህነትን በማስወገድ ነው። በርካታ አመጾች ሃይማኖትን ሽፋን ባደረጉ አክራሪነት የተደገፉ፣ የሰላም አለቃ የተባለውን የእግዚአብሔርንም ስም ያጎደፉ እና ለዘመናት የቆየውን የተጎራባች አገሮችን ሰላማዊ ግንኙነት ያበላሹ ናቸው። አመጽ ሁል ጊዜ በጦር መሣሪያ የታገዘ ነው። አዳዲስ የሆኑ ዘመናዊ የጦር መሣሪያ ለመግዛት እየተሯሯጡ ስለ ሰላም መናገር አይቻልም። እንዲህ ዓይነት አካሄድ፣ በተለይ በሃያላን መንግሥታት ሕሊና ውስጥ የሚገኝ ሃላፊነት ነው። ባለፈው ዘመን፣ በሂሮሺማ እና በናጋሳኪ የሆነውን ታሪክ መዘንጋት የለብንም። ስለዚህ የሰላም መልዕክት የፈለቀበትን የመካከለኛው ምስራቅ አገሮችን የዝምታን ማቅ ማከናነብ የለብንም። የአመጽ ተቃውሞ እንዲገታ ማድረግ አለብን። በአካባቢው የሚገኘውን የተፈጥሮ ሃብት፣ ነዳጅ ዘይትንና ጋዝን ለመቀራመት የሚደረገው ሩጫ እንዲያበቃ እና ሕዝቦች በሰላም አብረው በመኖር የተፈጥሮ ሃብታቸውን በጋራ የሚጠቀሙበት መንገድ እንዲዘረጋ ማድረግ ያስፈልጋል።

የሰላም ጎዳናን የምናቀናው ሰላም እንዲወርድላቸው የሚወተውቱትን ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ማየት ያስፈልጋል። የብዙሃኑ ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱ ሕብረተሰብ ደህንነት እንዲጠበቅ ያስፈልጋል። የወደ ፊት መልካም እድልን ለማመቻቸት የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ሕዝብ የጋራ ዜግነት መብት እንዲከበር ያስፈልጋል። በመካከለኛው ምስራቅ አገሮች የሚገኙ ክርስቲያኖችም እኩል የዜግነት መብት እንዲኖራቸው ያስፈልጋል።

የማይታጠፍ ተስፋን በመያዝ፣ የብዙሃን ከተማ ወደ ሆነችው ኢየሩሳሌም ፊታችንን በመመለስ፣ የአይሁድና የሙስሊም እምነት ተከታዮች በመካከላቸው የሚታየውን አለመግባባት አስወግደው፣ ለዓለም ዓቀፍ ሕግ መገዛት፣ በቅድስት ሃገር ኢየሩሳሌም የሚገኙ ክርስቲያን ማሕበረሰብ የሚያቀርቡትን ስሞታ ማዳመጥ ያስፈልጋል። በእስራኤልና በፍልስጥኤም መካከል የሚታዩትን አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት የሚቻለው፣ በዓለም ዓቀፉ ማሕበረ ሰብ አደራዳሪነት፣ በሁለቱ አገሮች መካከል በሚደረጉ ሰላማዊ ውይይቶች እና የሁለቱ አገሮች ሉዓላዊነት ሲረጋገጥ ነው። 

በመካከለኛው ምስራቅ አገሮች መካከል ለዓመታት ያህል በተካሄደው አመጽ ምክንያት ሕጻናት ወላጆቻቸው ሲገደሉ፣ በገዛ አገራቸው መከራ እና ስደት ሲደርስባቸው በማየት ሲያለቅሱ ኖረዋል። ወደ ትምህርት ቤት ከመሄድ ይልቅ የከባድ ጦር መሣሪያ ድምጽ ሲሰሙ እና በበረሃ ሲንከራተቱ ኖረዋል።ከሕፃናትና ከሚጠቡ ልጆች አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ ስለ ጠላትህ፥ ጠላትንና ቂመኛን ለማጥፋት፣” (መዝ. ዳዊት . 8 . 2.)   የእነዚህን ሕጻናት እንባ ከዓይናቸው በመጥረግ ብቻ ሰብዓዊ ክብራቸውን ማስመለስ ይቻላል።

ለእነዚህ ሕጻናት ሰላም እንዲወርድ በመመኘት የሰላም እርግብ እንድትበር እናደርጋለን። ጨለማን አልፎ ዘላቂ ሰላም ከፍ ብሎ እንዲታይ እንመኛለን። የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች፣ በሁሉም አህጉሮች እና እምነቶችም ዘንድ የሰላም እንጂ የጦርነት እና የአመጽ ምሳሌ መሆን የለበትም። የተወደደው የመካከለኛው ምስራቅ ሕዝብ ከጦርነት፣ ከአመጽ፣ ከአክራሪነት፣ ከብዝበዛ፣ ከጭቆና፣ ከድህነት ከውርደት የተላቀቀ እንዲሆን እመኛለሁ። ሰላም ከእናንተ ጋር ይሁን። በመካከላችሁም ሰላም ይሁን፣ የእግዚአብሔር ቡራኬ በእናንተ ላይ ይሁን።

   








All the contents on this site are copyrighted ©.