2018-05-29 09:35:00

በኮንጎ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹዕን ጳጳሳት በሀገሪቷ ሊካሄድ የታቀደው ምርጫ ሰላማዊ እና ግልጽ እንዲሆን ጠይቁ።


በኮንጎ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹዕን ጳጳሳት በሀገሪቷ ሊካሄድ የታቀደው አጠቃላይ ምርጫ ሰላማዊ እና ግልጽ ይካሄድ ዘንድ መጠየቃቸው ተገለጸ።

በኮንጎ ዲማክራቲክ ሪፖብሊክ የሚገኙ  የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹዕን ጳጳሳት በመጪው ታኅሳስ 14/2011 ዓ.ም በሀገሪቷ ሊካሄድ የታቀደው አጠቃላይ ምርጫ የተቀመጠለትን የጊዜ ሰሌዳ ጠብቆ ሰላማዊ እና ግልጽ በሆነ መልኩ ይካሄድ ዘንድ ጥሪ ማቅረባቸው ተገለጸ።

የጎንጎ ዲሞክራቲክ ሪፓብሊክ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹዕን ጳጳሳት ጉባኤ ቃል አቃባይ እና ጠቅላይ ጸሐፊ የሆኑት አባ ዶናቴል ናሾል እንደ ገለጹት የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፖብሊክ ጳጳሳት እ.ኤ.አ. ታህሳስ 31 ቀን 2016 ዓ.ም  ላይ የተፈረመውን የቅዱስ ሴልቬስቴር ስምምነት ወደ ሰላም እና ወደ መግባባት የሚወስድ ብቸኛው መንገድ በመሆኑ የተነሳ መንገሥት ይህንን ስምምነት ጠብቆ እንዲጓዝ ጥሪ ማቅረባቸውን ለመረዳት የተቻለ ሲሆን ከቅርብ አመታት በፊት የሀገሪቷ ርዕሰ ብሔር የሆኑት ጆሴፍ ካቢላ የስልጣን ጊዜያቸውን ለማራዘም በማሰብ በገዛ ስልጣናቸው ሕገመንግስቱን ለመቀየር በመፈለጋቸው የተነሳ የተከሰተው የፖሌቲካ አለመረጋጋት ሊቀረፍ የሚችለው በስምምነቱ መስረት አጠቃላይ የሆነ ምርጫ ሲካሄድ ብቻ መሆኑን ጨምረው ገለጸዋል።

ይህ የቅዱስ ሴልቬስቴር ስምምነት ተብሎ የሚጠራው ስምምነት በኮንጎ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹዕን ጳጳሳት ጉባሄ አነሳሽነት አሁን በስለጣን ላይ ያለው መንግሥት በስልጣን ላይ ለመቆየት ሕገመንግስቱን ለመቀየር የሚያደርገውን ጥረት በማቆም በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ይህ ስምምነት ተፈጻሚ መሆኑን ወይም አለመሆኑን የሚከታተሉ ሀገራቀፍ የሆነ ታዛቢ ቡድን እንዲቋቋም፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚሳተፉበት የብሔራዊ ምርጫ አዘጋጅ ኮሚቴ ተቋቁሞ በመጪው ታኅሳስ ወር 2011 ዓ.ም ሀገራዊ ምርጫ እንዲካሄድ ከስምምነት መደረሱ ይታወሳል።

በኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፖብሊክ በመጪው ታኅሳስ 14/2011 ዓ.ም የሚካሄደው አጠቃላይ ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ታማኝ እና ሁሉንም አሳታፊ እንዲሆን የጎንጎ ዲሞክራቲክ ሪፓብሊክ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹዕን ጳጳሳት ፍላጎት እና ምኞት እንደ ሆነ የገለጹት የጉባኤው ቃል አቃባይ እና ጠቅላይ ጸሐፊ የሆኑት አባ ዶናቴል ናሾል ሐሳብን በነፃ እና ሰላማዊ በሆነ መልኩ መገልጽ የሚለው መብት መገደቡ "በኮንጎ ሕገ-መንግስት ውስጥ የተቀመጠውን ይህን መብት የሚጻረር በመሆኑ የተነሳ ይህ ገደብ እንዲነሳ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲረጋገጡ እና ብሔራዊ ምርጫ በአግባቡ ግልጽ በሆነ መልኩ እና በሰላም እንዲካሄድ ማድረግ ያስፈልጋል ካሉ በኃላ አንድ ዲሞክራሲያዊ ነኝ የሚል መንግሥት ዲሞክራስያዊ መብቶችን የሚያፍን ከሆነ ይህ ጉዳይ አሳፋሪ የሆነ ጉዳይ ነው ብለዋል።

በእዚህም መልኩ በሀገሪቷ በመጪው ታኅሳስ 2011 ዓ.ም ላይ ለመካሄድ የታቀደው ብሔራዊ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ መንግሥት ያራሱን ድርሻ ሊወጣ እንደ ሚገባ የገለጸው በጎንጎ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹዕን ጳጳሳት ጉባሄ መግለጫ መንገሥት በሀገራቀፍ ደረጃ በአሁኑ ወቅት በተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊዎች እና በምንግስት የጸጥታ ኃይሎች መካከል በአንድ አንድ የሀገሪቷ ክፍል የተቀሰቀሰው ግጭት እንዲበርድ ባለድርሻ አካል የሆኑት በሙሉ ሰላም በማስፈን ሂደት ውስጥ እንዲሳተፉ ብጹዕን ጳጳሳቱ በመግለጫቸው ጥሪ አድርገዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.