2018-04-06 16:23:00

ብፅዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የትንሳኤ በዓል በማስመልከት ያስተላለፉት መልዕክት


ብፅዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳሳት በዘመነ ማርቆስ የ2010 (የ፳፻፲) ዓ/ም ለመላው የአገራችን ምዕመናን የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የትንሳኤ በዓል በማስመልከት ያስተላለፉት መልዕክት

የእዚህን ዝግጅት ሙሉ ይዘት ከእዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ተነሳ !

በታላቅ ኃይልና ሥልጣን !

ሰይጣንን አሠረው፣ አዳምን ነፃ አወጣው !

እንግዲህ ወዲህ ደስታና ሰላም ሆነ !” (ከሥረዓተ ቅዳሴ)

 

ብፁዐን ጳጳሳት

ክቡራን ካህናትና ገዳማውያን/ዊያት

ክቡራትና ክቡራን ምዕመናን

መላው ሕዝበ እግዚአብሔር

በጎ ፍቃድ ላላቸው ሰዎች በሙሉ

 

ከሁሉ አስቀድሜ በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንና በራሴ ስም ለመላው ህዝበ ክርስቲያንና ምዕመናን እንኳን ለ2010 ዓ.ም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞቴን አስተላልፍላችኃለሁ ፡፡

 ዛሬ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውና ድል ያደረገ ትንሣኤያችንና እውነታችን የሆነውን የእርሱን የትንሣኤን በዓል እናከብራለን፡፡ በዚህም እግዚአብሔር ከፍ እንዳደረገውና በቀኙ እንዳስቀመጠው ለሁላችንም በግልጥ የሚታይ ነው፡፡

በመስቀል ላይ የመሞትን ውርደት ከምንም ሳይቆጥር የመስቀልን መከራና ሞት ታገሠ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝም ተቀመጠ ” (ዕብ 121)

  በክርስቶስ ትንሣኤ ያገኘነውን በአዲሱ ሰውነታችን አዲስ መንፈስ ለብሰን ኃጢያትን ድል በማድረግ የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል በመሸከም የድል አክሊል እንቀዳጃለን ፡፡ የእርሱ የሞት ላይ ድሉ ለእኛ በመንፈስ ኃይላችን ከሆነ በእርሱ ቃል አምነንና ታምነን ደኅንነትን ለማግኘት ምዕመናን ሁላችን ዓይነልቦናችንን ከፍተን ወደ አምላካችን እንመለስ እርሱም በመሐሪነቱ መጥፎ ሥራዎቻችንን አስወግዶ ወደ እኛ ይመለሳል፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ፣ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላዓለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና”    (ዩሐ 3፡15) ይለናል፡፡

እግዚአብሔር አንድ ልጁን የላከልን የኛ ፍቅር አስገድዶት ነው፤ እርሱም እኛን ለማዳን ደሙን በማፍሰስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ እስከ መሞት ድረስ ወዶናል፡፡ ይህ ሁሉ ተደርጎልን ገና በእምነት ጉድለት የምንኖር ብዙዎች አለን፤ ሆኖም ግን በልጁ የምናምን ሁላችን የዘላዓለም  ሕይወት እንዳለውና በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቁጣ በእርሱ ላይ እንደሚኖርና ሕይወትን እንደማያይ በዩሐ 3፡36 ተገልጻል፡፡ ስለዚህ ከነፍስ ሞት የምንድንበትን መንገድ እንከተል፡፡

 የተወደዳችሁ ሕዝበ እግዚአብሔር!

ክርስቶስ ሞትን አሸንፎ  ወደ ዘለዓለም ክብር እንደገባ እኛም ክፋትን አሸንፈን የዘለዓለምን ሕይወት ለማግኘት እንትጋ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምንና እርቅን ያወረደልን በመስቀሉ ነው፡፡ ሰለዚህ መሰቀሉ ቤዛችን፣ ኃይላችን፣ ተስፋችን ነውና መመኪያችንና ሰላማችን ድል አድራጊው ንጉሣችን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሁሉም ሰዎች ጥሩ አርዓያ እንደሆነላቸው እናውቃለን፡፡ እኛም በጊዜያችን ያለውን ያለመረጋጋት ለማሻሻል በትዕግስትና በጥበብ ብሎም በሰላምና በፍቅር ከዚህም በላይ በተረጋጋና በአንድነት መንፈስ መቆጣጠርና መሥራት፤ ክቡር የሆነውም የሰዎች ሕይወት በከንቱ እንዳይጠፋ ጥንቃቄ ማድረግና ስለሰላም ማስተማር ይኖርብናል፡፡ ሁላችንም የአንድ አባት ልጆች መሆናችንን ተረድተን በአንድነት መንፈስ ተባብረን መሥራት ይኖርብናል፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያዊነት የሀገራችን ብቻ ሳይሆን የአህጉራችን አፍሪካና የጥቁር ሕዝብ ኩራት ነውና፡፡

በቅርቡ አገራችንን በጠቅላይ ሚንስትርነት ላለፉት ዓመታት በትጋት ያገለገሉና በገዛ ፍቃዳቸው ይህንን ታላቅ ኃላፊነት ለተተኪያቸው ያሰስረከቡትን የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር ክቡር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ላበረከቱት አገልግሎት በራሴ እና በቤተክርስቲያናችን ሰም አመሰግናለሁ፡፡  እንዲሁም ክቡር ደ/ር ዓብይ አህመድ የኢሕአዴግ ሦሰተኛው ሊቀመንበርና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ስለተመረጡ እንኳን ደስ አለዎት በማለት የተረከቡትን ታላቅ ኃላፊነት በብቃት እንዲወጡ ቤተ ክርስቲያናችን በጸሎት ከእርሳቸው ጋር መሆኗን ትገልጻለች፡፡

 

የተወደዳችሁ ወጣቶች ሆይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስኮስ  ሁሌም  እንደሚያሳስቧችሁ  የወጣትነት ተስፋችሁና  የህይወት ብልጭታችሁ በተዘጋው ቤት ጨለማ እንዲጠፋ አታድርጉ፡፡ ይህ የተዘጋው ቤታችሁ ጨለማ  የሚበዛበት ምክንያት ብቸኛው  መስኮት  ኮምፒዩተሮቻችሁ እና ስማርት ስልኮቻችሁ ስለሆኑ ነው፡፡ ከእነዚህ የቴክኖሎጂ መሣሪያዎች ጋር  ብቻ  ተዘግታችሁ ስትኖሩ የወጣትነት ተስፋችሁ እንዳይደበዝዝ  ያስፈራል፡፡ የህይወታችሁን በር አስፍታችሁ ክፈቱት ፡፡ ጊዜያችሁና  ቦታችሁ  ትርጉም  ባለው መንገድ ምናባዊ  በሆኑ ሳይሆን እውነተኛ በሆኑ ሰዎች ግንኙነት ሙሉት ፡፡ ከምናባዊ   ሠዎች  ጋር እውነተኛና ተጨባጭ የሆነ የህይወት ልምድ መለዋወጥ አይቻልምና፡፡

እናንተ ወጣቶች ሆይ የሚያምንባችሁ እንዳለ እመኑ፡፡ ቤተሰቦቻችሁ፣ የሃይማኖት አባቶቻችሁ፣  እና ሀገራችሁ በእናንተ ይተማመናሉ፡፡  እናንተም በቤተሰቦቻችሁ፣ በሃይማኖት አባቶቻችሁ፣ እና በሀገራችሁ  ተማመኑ፡፡  ወጣቶች ጉልበትና ትጋት በሚያስፈልገው የሕይወት ወቅት ስታልፉ በእርግጥም ጥንካሬ አላችሁ፡፡ ይሄ አፍላ ኃይላችሁና ጥንካሬያችሁ እራሳችሁንና ሀገራችሁን  ለመቀየር ተጠቀሙበት ፡፡ ይህንንም ኃላፊነት በአካባቢያችሁ ካለው ነገር መጀመር ትችላላችሁ፡፡ ወጣቶች  በማህበረሰብ  ውስጥ ወሳኝ የሆነ  ኃላፊነት እና ተልዕኮ እንዲሠጣችሁ እንፈልጋለን፡፡ ሀገራችንም  ለእናንተ ቦታ ልታመቻች ድፍረት ሊኖራት ይገባታል፡፡ እናንተም ይህንን ቦታ ወይም ኃላፊነት ለመሸከም መዘጋጀት ይኖርባችኋል፡፡ ይህንን ኃላፊነት ለመሸከም   ከሱስ ከአደገኛ  እፅ ከዝሙት ራሳችሁን ጠብቁ፡፡ በሱስ የተጠመደ እና ስነምግባሩ የተበላሸ ወጣት የወደፊት ህይወቱ ተስፋ አልባ ይሆናል፡፡ ለሀገርም ለማህበረሰብም ሸክም ይሆናል፡፡ በእግዚአብሔርም ፊት ክብር አይኖረውም፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር የሰጣችሁን ክብር  ጠብቃችሁ ኑሩ ፡፡

 የተወደዳችሁ ምዕምናን እኛ ሰዎች ለእግዚአብሔርና ለሌሎች ሰዎች የተፈጠርን ነን ስለዚህ በእግዚአብሔር አምሳል ለተፈጠሩት ችግረኞች፣ ህሙማን፣ የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ ወላጆቻቸውን ላጡ ሕፃናት ካለን በማካፈል የትንሣኤውን በዓል በደስታ እንዲያከብሩና እንዲያሳልፉ ታደርጉ ዘንድ አደራ አላለሁ፡፡

 በመጨረሻም በውጭ አገር ለምትኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያን ፣ በስደት ላይ ያላችሁ ወንዶችና ሴቶች ወገኖቻችንና ልጆቻችን፣ የአገርን ድንበር ለማስከበር በየጠረፉና በውጭ አገራት ለምትገኙ የመከላለያ ሠራዊት አባላት፣ በየማረሚያ ቤቶች ለምትገኙ የህግ ታራሚዎች፣ በየቤቱና በየሆስፒታሉ ለምትገኙ ህሙማን፣ በውጭ አገራት ለምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት በሙሉ እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ በዓሉንም የሰላም የደስታ የፍቅር ያድርግላችሁ፡፡

የሰላም ንጉሥ ሆይ ሰላምህን ስጠን !

 የትንሳኤው ጸጋ በሙላት ከሁላችን ጋር ይሁን !!     

 እግዚአብሔር ኢትዮጵያ አገራችንን ይባርክልን ይጠብቅልን !

 

                                                        

+ብፅዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን የ

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት

የምስራቅ አፍሪካ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤዎች ኅብረት ሊቀመንበር

 








All the contents on this site are copyrighted ©.