2018-02-17 17:51:00

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ወቅት ያሰሙት ስብከት።


ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት ዓርብ በቅድስት ማርታ በሚገኘው ጸሎት ቤታቸው ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ወቅት ባሰሙት ቃለ ምዕዳን፣ ጾም በግብዝነት የተሞላ ወይም በሰዎች እንዲታይ ተብሎ የሚደረግ መሆን እንደሌለበት አሳስበዋል። የራስን ሕሊና በሚቃረን መልኩ፣ ጾምን በአግባቡ ሳንጾም ቀርተን፣ እኛ ካቶሊኮች እምነታችንን በተግባር እናሳያለን፣ ሁል ጊዜ እንጾማለን፣ የበደሉንን ይቅር እንላለን፣ የዚህ መንፈሳዊ ማሕበርም አባል ነን በማለት፣ በተግባር ሲታይ ግን ፍሬው በጣም ጥቂት የሆነና ሕሊናንችንን የሚቃረን ጾም መጾም የለብንም  ብለዋል።

በሰዎች ቤት ተቀጥረው የሚሰሩትን፣ የቤት ውስጥ ሠራተኞችን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ የተገነዘቡትንና በአንድ ሰው ቤት የተመለከቱትን ሲናገሩ፣ ለሰራተኛቸው የሚገባውን አክብሮት በመንፈግ በጥፊ ሲመቷት ተመልክቼአለሁ ብለዋል። ብዙዎች ለሰራተኞቻቸው ስለሚሰጡት አክብሮት ሲጠየቁ፣ በየዕለቱ የሚያደርሱትን በደል በመደበቅ ወይም በመካድ፣ መልካም አክብሮት እንዳላቸው ይናገራሉ። እንግዲህ ይህ ነው ሕሊናን የሚቃረን ክርስቲያናዊ አካሄድ። እስቲ በጥቂቱ የሚከተሉ ጥያቄዎችን እንመልከት፣ ለሠራተኛዬ ተገቢ የጉልበት ዋጋ ወይም ደሞዝ እከፍላለሁ? የሚገባውን ሰብዓዊ አክብሮት እሰጣለሁ? የእረፍት ጊዜ እንዲኖር እፈቅዳለህ? ብለን ራስን መጠይቅ ያስፈልጋል። በቤታችን፣ በድርጅቶቻችን ተቀጥረው የሚሰሩ በርካታ ሰራተኞች አሉ። እነዚህን ሠራተኞች እንዴት እንይዛቸዋለን ብለን መጠየቅ በቂ ይሆናል። 

በዕለቱ የተነበበው የመጀመሪያው ንባብ ይህን ያስገነዝባል። “በሃይል ጩህ፣ ምንም አታስቀር፣ ድምጽህን እንደ መለከት አሰማ ለሕዝቤ አመጻቸውን፣ ለያዕቆብም ቤት ሃጢአታቸውን ተናገር። ዕለት በዕለት ይፈልጉኛል፣ መንገዴን ለማወቅ የሚጓጉ ይመስላሉ፣ ትክክለኛውን ነገር እንደሚያደርግ፣ የአምላኩንም ትዕዛዝ እንዳልተወ ሕዝብ ሁሉ፣ ተገቢ የሆነ ፍትሕ ይለምኑኛል። እግዚአብሔር ወደ እነርሱ እንዲቀርብ የሚወዱ ይመስላሉ። አንተ ካልተቀበልከው ለምን ጾምን? አንተ ከጉዳይ ካልቆጠርከው ስለ ምን ራሳችንን አዋረድን? ይላሉ። ሆኖም በጾማችሁ ቀን የልባችሁን ታደርጋላችሁ፣ ሠራተኞቻችሁንም ትበዘብዛላችሁ። ጾማችሁ በጥልና በክርክር፣ በግፍ ጡጫና በመደባደብ ይፈጸማል፣ ከእንግዲህ ዛሬ እንደምትጾሙት ጾማችሁ፣ ድምጻችሁ ወደ ላይ እንደሚሰማም ተስፋ አታደርጉ። እኔ የመረጥሁት ጾም እንዲህ ዓይነቱ ነውን? ሰውስ ራሱን የሚያዋርደው በእንዲህ ያለው ቀን ብቻ ነውን? እንደ ደንገል ራስን ዝቅ ማድረግ ነውን? ወይስ ማቅ ለብሶ በዓመድ ላይ መንከባለል ነውን? ታዲያ ጾም ብለህ የምትጠራው ይህን ነውን? እግዚአብሔርስ የሚቀበለው እንዲህ ያለውን ቀን ነውን? እንግዲህ እኔ የመረጥኩት ጾም፣ የጭቆናን ሰንሰለት እንድትበጥሱ፣ የቀንበርን ገመድ እንድትፈቱ፣ የተጨቆኑትን ነጻ እንድታወጡ፣ ቀንበርን ሁሉ እንድትሰባብሩ አይደለምን? ምግብህን ለተራበ እንድታካፍለው፣ ተንከራታቹን ደሃ ወደ ቤትህ እንድታስገባው፣ የተራቆተውን ስታይ እንድታለብሰው፣ የሥጋ ዘመድህንም ፊት እንዳትነሳው አይደለምን? ይህ ከሆነ ብርሃንህ እንደ ንጋት ጮራ ይፈነጥቃል፣ ፈውስህ ፈጥኖ ይደርሳል፣ ጽድቅህ ቀድሞህ ይሄዳል፣ የእግዚአብሔር ክብር ደጀን ይሆንልሃል። የዚያን ጊዜ ትጣራለህ፣ እግዚአብሔርም ይመልስልሃል፣ ለዕርዳታ ትጮሃለህ፣ እርሱም አለሁልህ ይልሃል።” (ትንቢተ ኢሳይያስ ምዕ 58 ከቁ 1-9)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የምንጾመው ጾም ከራስ አልፎ ለሌሎች የሚሰጠው ጥቅም ምንድነው ብሎ በመጠየቅ፣ ጾማችን ለሌሎች ጥቅም ካልሆነ የግብዝነት ጾም ነው፣ ሕሊናን የሚቃረን ጾም ይሆናል፣ ወደ መንታ መንገድ የሚወስድ ጾም ይሆናል። ፈሪሳውያንና ሰዱቃዊያን እንደሚያደርጉት የውሸትና የአስመስይነት ይሆንና ክርስቲያናዊ አካሄዳችንን የሚቃረን ይሆናል። ከግብዝነት እንድንወጣ፣ የራስን ሕሊና ከሚቃረን አካሄድ እንድንላቀቅ የምንችልበትን የጸጋ በረከት መጠየቅ ያስፈልጋል። የምንችለውን እንጂ የማንችለውን ማድረግ የለብንም። የምንችለውንም ስናደርግ በቅን መንገድ፣ የራስን ሕሊና በማይወቅስ በክርስቲያናዊ መንገድ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበው ይህን የምናደርግበትን ጸጋ እግዚአብሔር እንዲሰጠን በጸሎት ተማጽነዋል።                                                                                                                                                                                           








All the contents on this site are copyrighted ©.