2018-02-14 08:50:00

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መፍትሄው የሰዎች ልብ መለወጥ እንደሆነ አስገንዝበዋል።


ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መፍትሄው የሰዎች ልብ መለወጥ እንደሆነ አስገንዝበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህን የተናገሩት ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለማስቀረት በቫቲካን በተደረገው ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ ለተካፈሉት ተሳታፊዎች እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ብዙ የግንዛቤ ማነስና ወንጀሉን ለማስቀረት ቅን ፍላጎት ያንሳል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ምክንያቱም ሕሊናችንን በቅርብ የሚነካ አደገኛ ክስተት በመሆኑ ነው ብለዋል።

በቅዱስ ቀለመንጤዎስ አዳራሽ ከተገኙት የስብሰባው ተካፋዮች በኩል ለቀረቡት የተለያዩ ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከስብሰባው ተሳታፊዎች ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ሲሰጡ ባሰሙት ንግግር፣ የድርጊቱን ሕገ ወጥነት እያወቁ በወንጀሉ የሚሳተፉ መኖራቸውን፣ በኢንተርኔት ሳይቀር በሚካሄደው ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ተግባር ላይ የሚሳተፉ ግለ ሰቦች መኖራቸውን፣ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ከሚያራምዱ ድርጅቶች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት በመፍጠር በርካታ ገንዘብን የሚሰበስቡ ሰዎች መኖራቸውን ገልጸዋል። ይህ በመሆኑ አሉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ማንኛውም ማሕበረ ሰብ የዚህ ወንጀል ተጠቂ እንዳይሆን ማስጠንቀቅና ግንዛቤን መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በማከልም ወንጀሉ እንዳይስፋፋ እና ለማስቆም ይቻል ዘንድ ወጣቶች ድምጻቸውን ማሰማት ያስፈልጋል ብለዋል። ወንጀሉን ለመዋጋት ከሚያስችሉ መንገዶች አንዱ ወደየ ቁምስናዎች በመሄድ በምዕመናን መካከል ግንዛቤን የማስጨበጥ ሥራ እንዲሰራ አስተያየታቸውን ለግሰዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም ወጣቶች በብዛት የሚጠቀሟቸው ማሕበራዊ ሚዲያዎች፣ አሉታዊ ገጽታቸውንም ሳንዘነጋ፣ ወንጀሉን ለመከላከል የሚያስችሉ መልካም አጋጣሚዎችን በመፍጠርና ወንጀሉን ለመቆጣጠር የተሰማሩትን ሰዎች በማሰባሰብ እገዛን እንደሚያደርጉ መዘንጋት የለብንም ብለዋል።

የሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባ የሆኑት፣ በራሳቸው የደረሰው ስቃይ በሌሎችም እንዳይደገም በማለት የተለያዩ ጠቃሚ መረጃዎችን በማቀበል ሊተባበሩ እንድሚችሉ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በማብራሪያቸው አስገንዝበዋል። ቀጥለውም ሁሉን የሚያካትት ማሕበራዊ እድገትን ለሕዝቡ ማደረስ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ጠቅሰው ይህም እርሳቸው ብዙን ጊዜ እንደሚናገሩት፣ በሕዝቦች መካከል ልዩነትን በመፍጠር፣ አንድን ሰው ከሌላው የማበላለጥ እና የማግለል አዝማሚያ ካለ፣ ሰዎች ሰብዓዊ ክብራቸውን በመነጠቅ ለባርነት፣ ለብዝበዛ እና ለሌሎች በርካታ የማሕበራዊ ችግሮች እንደሚጋለጡ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስገንዝበዋል። ቅዱስነታቸው በንግግራቸው፣ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል በሚደረግ ጥረት ውስጥ መንግሥታት በተግባር ላይ የሚውሉ ዘላቂ ሕጎችን በማውጣት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላሉ ብለዋል። በርካታ የሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባ የሆኑ ሴቶች ያሉ ከሆነ ለዚህ ምክንያቱም የሚፈልጉትን ለመፈጸም የተዘጋጁ በርካታ ወንዶች ከመኖራቸው የተነሳ ነው። ስለዚህ በእርግጥ ለሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ቀዳሚ ተጠያቂዎች በወንጀሉ የተሰማሩ ስዎች ናቸው ወይ የሚለውን ጥያቄ መመለስ ያስፈልጋል ብለዋል። ዋነኛው መንስኤ፣ በዓለማችን ውስጥ እጅግ በጣም ብዙ ስግብግብነት እና ራስ ወዳድነት ስለተበራከት እንደሆነ ይሰማኛል ብለዋል። በወንጀሉ የተሰማሩትን ወደ ሕግ ዘንድ ማቅረብ ሕጋዊ ግዴታነው። ነገር ግን እውነተኛ መፍትሄ የሚሆነው የሰዎች ልብ መለወጥና በገንዘብ ራሳቸውን ለማበልጸግ የተነሱትን ሰዎች ፍላጎት ማዳከም ነው ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በመጨረሻም በሕጻንነት ዕድሜ፣ በባርነት የተሸጠችውን ቅድስት ጁሴፒና ባኪታ አስታውሰው ጸሎታችንን ወደ እርስዋ ማቅረብ እንዳለብን አስታውሰው፣ በጥቅምት ወር 2011 ዓ ም በተለይ በወጣቶች ጉዳይ ዙሪያ በስፋት የሚወያይ የጳጳሳት ሲኖዶስ እንደሚካሄድ ገልጸው በዚህ የጳጳሳት ሲኖዶስ ወቅት የመላው ዓለም ወጣቶች በንቃት በመሳተፍ ቀዳሚ ተዋናዮች እንደሚሆኑ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በኩል በሰዎች ላይ የሚፈጸመውን ወንጀል በመከላከል፣ ከባርነት ሕይወትም ሰዎችን በመታደግ መላዋ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን የበኩልዋን አስተዋጽኦ ታበረክታለች ብለዋል። የጳጳሳቱ ሲኖዶስ በኩል በመላው ዓለም የሚገኙ ሀገረ ስብከቶችና ቁምስናዎች የሰውን ልጅ ከጥቃት በመከላከል እገዛን እንደሚያደርጉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።             








All the contents on this site are copyrighted ©.