2018-02-06 17:37:00

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የኢየሱስን አብነት በመከተል ወንጌልን በሕዝቡ መካከል በመግባት መስበክ ያስፈልጋል አሉ።


ውድ ወንድሞቼና እህቶቼ

ቅዱስ ማርቆስ የጻፈው የዛሬው የወንጌል መልዕክት በምዕ. 1 ከቁ. 21-39፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በቅፍርናሆም ያደረገውን ውሎ ያስሳስበናል። በማርቆስ ወንጌል በምዕራፍ 1 ከቁጥር 21-39 እንደተጻፈው የእብራዊያን ሰንበት የዋለበት፣ ቅዳሜ ዕለት ነበር። ይህን የወንጌል ክፍል፣ ሐዋርያው ቅዱስ ማርቆስ ከሰዎች እምነት ጋር ያመሳስለዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ በርካታ ሕሙማንን የፈወሰበትና እርሱ ይህን የፈውስ ሥራውን ሲያከናውን በተመለከቱት ሰዎች መካከል የታየውን የእምነት መነቃቃት ያመለከታል።  

የዚህን ዝግጅት ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ።

ኢየሱስ ክርስቶስ ዕለቱን ተግባር ማከናወን የጀመረው የስምኦን ጴጥሮስ አማት በመፈወስ ነበር። ይህ የፈውስ አገልግሎቱ፣ የመፈወስ ሃይል እንዳለው ማሳየት ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱን የሰውነት ክፍል ከያዘው በሽታ  መፈወስ እንድሚችልም የሚያሳይ ነው። በዚህ ታሪክ ውስጥ ሐዋርያው ቅዱስ ማርቆስ የኢየሱስን የማዳን ሥልጣኑን በአጭሩ ሲገልጽ የተዓምራትንም አጠቃላይ ትርጉም እንድንመለከት ይጋብዘናል። የሰውነት ክፍል መፈወስ ሲባል የልብንም መፈወስ ይገልጻል። ይህ ደግሞ እያንዳንዱ አማኝ በልቡ በማመን መከተል ያለበትን የእምነት መንገድ ያስታውሰናል። ከተለያዩ ደዌ በኢየሱስ ክርስቶስ የዳኑት ሁሉ ተመልሰው እርሱን መከተል እና ማገልገል እንዳለባቸው ይገልጻል።

በቀኑ መጨርሻ ላይ የመንደሩ ነዋሪዎች በሙሉ የታመሙባቸውን የቤተሰብ ክፍሎችንና ሌሎችንም ኢየሱስ ወደሚገኝበት ይዘው ሲመጡ እንመለከታለን። ሕዝቡን ከደረሰበት የሰውነት ስቃይና የመንፈስ ጉዳት ማውጣት፣ ማጽናናት እና መፈወስ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በቃልና በተግባር ያከናወናቸው አገልግሎቶች እንደሆኑ እንመለከታለን። ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ወይም የመፈወስ አገልግሎቱን ያከናወነው ከሕዝቡ መካከል ራቅ ብሎ፣ ወይም ራሱን በማግለል ወይም ተዘግቶ በሚቆይ ቤተ ሙከራ ውስጥ ሳይሆን ወደ ሕዝቡ መካከል በመሄድና ወደ ሕዝቡ ውስጥ በመግባት ነው። የኢየሱስን ሕይወት የተመለከትን እንደሆነ ወንጌልን ሲሰብክ ወይም ሲያስተምር በተለያዩ በሽታዎች የሚሰቃዩትን እየፈወሰ፣ ሕይወቱን በሙሉ በሕዝቡ መካከል አሳልፏል። ቅዱስ ወንጌል በተለያዩ ክፍሎች እንድሚናገረን፣ ኢየሱስ የፈውሳቸው እና ያጽናናቸው ሕዝቦች በመከራ እና በችግር ውስጥ የወደቁ ናቸው። ይህ ሕዝብ በእርግጥም ከችግራቸው የሚያወጣቸው፣ የስቃይ ድምጻቸውን የሚያዳምጥላቸው ታላቅ ሃይል የሚያስፈልገው ሕዝብ ነበር። ይህ ታላቅ ሃይልም ሌላ ሳይሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ኢየሱስም ዕለታዊ አገልግሎቱን የሚደመድመው ቀኑን በሙሉ፣ በተለያዩ በሽታ የተያዙትን ሲፈውስና ከበሽታቸውም ሲያድን ከቆየ በኋላ ሲመሽ ነው። ከዚያ በኋላስ ምን ያደርጋል?

በቀጣዩ ቀን ንጋት ላይ፣ ማንም ሳያየው ከከተማ ወጣ ብሎ ወደ ገለልተኛ ስፍራ በመሄድ ይጸልያል። ኢየሱስ ዘወትር ይጸልያል። ተአምራቶችን የሚያከናውንበት ሃይል እንዲጨመርለት ይለምናል። ተዓምራት ደግሞ ለእምነታችን፣ ለጥያቄዎቻችን የሚሰጡ መልሶችን የምናይባቸው ምልክቶች ናቸው። እነዚህ ምልክቶች፣ በወንጌል ቃል በመታገዝ፣ እምነታችን ዕለት በዕለት የሚታደስበት፣ የኢየሱስ ክርስቶስ መለኮታዊ ጸጋ በሕይወታችን እንዲገለጥ ያደርጋሉ።

ሐዋርያው ቅዱስ ማርቆስ በጻፈው ወንጌል በምዕ. 1 ላይ የተገለጸው የመጨረሻው ክፍል ማለትም ከቁ. 35-39፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት የሰበከው በአደባባይ፣ ሕዝብ በሚገኝበት፣ ወይም ሕዝቡ እርሱን በቀላሉ ሊያገኙት በሚችሉበት ቦታ ላይ ሆኖ ነው። ሐዋርያት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲጸልይ ከቆየበት ሥፍራ ወደ ከተማ ሊያመጡት በጠየቁት ጊዜ የመለሰላቸው መልስ፣ በአቅራቢያችን ወደሚገኙ ሌሎች መንደሮች እንሂድ፣ እኔ እዚያ በመገኘት ስለ እግዚ አብሔር መንግሥት መናገር፣ ማስተማር አለብኝ የሚል ነበር። ይህ የእግዚአብሔር ልጅ የከናወነው ዕለታዊ የሕይወት ጉዞ ነው። የደቀ መዛሙርቱም የሕይወት ጉዞ ይህንን ይመስላል። የእያንዳንዱ ክርስቲያን የሕይወት ጉዞ ይህን መምሰል ይኖርበታል። በዚህ መሠረት የሕይወታችን መንገድም፣ ወንጌል የሚበሰርበት፣ ቤተክርስትያንም ተልዕኮዋን ሳታቋርጥ በዘላቂነት የምታከናውንበት መሆን እንዳለበት ያሳየናል።

እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ መንፈስ ቅዱስ የሚናገረንን ለማዳመጥ የተዘጋጀን እንድንሆን፣ ቤተ ክርስትያንም ነፍስንና ስጋን ፈዋሽ የሆነውን የኢየሱስ ክርስቶስን ቃል  በሕዝቦች መካከል መመስከር እንድትችል ዘወትር ትርዳን በማለት የዕለቱን ስብከት አጠናቅቀዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.