2018-01-03 16:44:00

የሕጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ፣ የእርስ በርስ ግጭቶች ባሉባቸው የዓለማችን ክፍሎች፣ በሕጻናት ላይ የሚደርሰው ጥቃት እጅግ መጨመሩን ገለጸ።


የሕጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ፣ የእርስ በርስ ግጭቶች ባሉባቸው የዓለማችን ክፍሎች፣ በሕጻናት ላይ የሚደርሰው ጥቃት እጅግ መጨመሩን ገለጸ።

በተባበሩት መንግሥት የሕጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ፣ የእርስ በርስ ግጭቶች ባሉባቸው የዓለማችን ክፍሎች፣ በሕጻናት ላይ የሚደርስ ጥቃት በዓመት ውስጥ እጅግ መጨመሩን ገለጾ ለዚህም ምክንያቱ በጦርነት የተጠመዱ መንግሥታት፣ የሕጻናትን መብት የሚያስከብር ዓለም አቀፍ ሕጎችን ችላ በማለታቸው ነው ብሏል።

የዚህን ዘገባ ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!


በተባበሩት መንግሥት፣ የሕጻናት መርጃ ድርጅት አስቸኳይ እርዳታ አቅራቢ ክፍል ዳይሬክተር የሆኑት ማኑ ኤል ፎንቴን እንደገለጹት፣ ከዓመት ዓመት በሕጻናት ላይ እየተፈጸመ ያለውን ጭካኔ እያየን ዝም ማለት አንችልም ብለዋል። በአፍጋኒስታን ባለፈው ዓመት ውስጥ፣ በዘጠኝ ወራት ብቻ 700 ሕጻናት መገደላቸው፣ በመካከለኛው አፍሪቃ ሪፓብሊክ፣ ጦርነቱ እንደገና ባገረሸበት በጥቂት ወራት ብቻ፣ በቁጥር በርካታ ሕጻናት መገደላቸው፣ መደፈራቸው፣ በግዞት መወሰዳቸውና ለውትድርና መመልመላቸው፣ በሕዝባዊ ዴሞክራቲክ ኮንጎ በተቀሰቀሰው ግጭት 850,000 ሕጻናት ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸው፣ በ200 የጤና ማዕከላት እና በ400 ትምህርት ቤቶች ላይ ጥቃት መድረሱና በግምት 350,000 ሕፃናት በአደገኛ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንደገጠማቸው ታውቋል።

በጎርጎሮሳዊያኑ 2016 ዓ .ም. በሰሜናዊው ናይጀሪያና በካሜሩን አሸባሪው የቦኮ ሃራም ታጣቂዎች ቢያንስ 135 ሕጻናትን በአምስት እጥፍ ለአጥፍቶ ጠፊነት እንደመለመላቸው ይነገራል።

በሚያንማርም የሮሂንጊያ ሕጻናት፣ በራኪን ግዛት ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ሲባረሩ መጠነ ሰፊ ጥቃት የደረሰባቸው ሲሆን በድንበር አካባቢ በሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች ማለትም በሚያንማር ታጥቂዎችና በጎሳ ቡድናች መካከል በሚካሄዱት ግጭቶች ሕጻናት ስቃይ እንደደረሰባቸው ታውቋል።

በደቡብ ሱዳንም ግጭቶች ባሉባቸው አካባቢዎች ሕዝቡ ለረሃብ በጋለጡና ከ19,000 ሕጻናት በላይ ለውትድርና መመልመላቸውና ግጭቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተቀሰቀሰበት ከህዳር ወር 2006 ዓም ወዲህ ከ2300 ሕጻናት በላይ እንደተገደሉና የመቁሰል አደጋ እንደደረሰባቸው ታውቋል።

በጎርጎሮሳዊያኑ ያለፈው ዓመት ማለትም በ2017 ዓ ም በሶማሊያ፣ በመጀመሪያዎቹ 10 ወራት ውስጥ 1,740 ሕጻናት ለውትድርና ተመልምለው እንደነበር ታውቋል።

በየመን የርስ በርስ ጦርነት በተካሄዱባቸው 1000 ቀናት ዉስጥ 5000 ሕጻናት መገደላቸው ወይም መቁሰላቸው ቢነገርም ከእርግጠኛ ምንጭ ከሚወጣው መረጃ ይህ አሃዝ ሊያድ እንደሚችል ታውቋል። ከ11 ሚሊዮን በላይ ሕጻናትም አስቸኳይ ሰብዓዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ሲነገር፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ካጋጠማቸው 1 ሚሊዮን ስምንት መቶ ሺህ ሕጻናት መካከል 385,000 ሕጻናት በሞት አፋፍ ላይ መገኘታቸው ታውቋል።

በምስራቅ ዩክሬን 220,000 ሕጻናት ፈንጂዎች በተቀበሩበት አካባቢዎች የሚኖሩ ሲሆን 500 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሥፍራ ውጊያ የተስፋፋበትና በዓለማችንም ውስጥ በፈንጂ ከተበከሉ አካባቢዎች መካከል እጅግ አደገኛ እንደሆነ ታውቋል።                     

 

 








All the contents on this site are copyrighted ©.