2018-01-02 16:28:00

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የአመጸኞችን ልብ እግዚአብሔር እንዲያስተካክል በጸሎት ተማጸኑ።


ርዕሠ ሊቃነ  ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የአመጸኞችን ልብ እግዚአብሔር እንዲያስተካክል በጸሎት ተማጸኑ።

ርዕሠ ሊቃነ  ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በግብጽ ዋና ከተማ ካይሮ ውስጥ ከአሸባሪዎች በተሰነዘረው ጥቃት የተገደሉትን 12 ክርስቲያኖችን በጸሎታቸው አስታውሰው የአሸባሪዎችንም ልብ እግዚአብሔር እንዲያስተካክለው እሁድ ባሳረጉት የእኩለ ቀን ጸሎታቸው ተማጽነዋል።    

የዚህን ዜና ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

ባለፈው አርብ፣ በካይሮ ውስጥ በአንድ ኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውስጥ በነበሩ ክርስቲያኖችና በከተማይቱ በሌላ አካባቢም፣ ንብረትነቱ የክርስቲያን ግለ ሰብ በተባለ የንግድ ማዕከል ላይ አሸባሪዎች ባደረሱት ጥቃት፣ በድምሩ  አስራ ሁለት ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።

ርዕሠ ሊቃነ  ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በጥቃቱ የሞቱን ሰዎች ነፍስ እግዚአብሔር በምሕረቱ እንዲቀበል፣ ለቆሰሉትና ለመላው ኅብረተሰብ በሙሉ አጋርነታቸውን ገልጸው የዓመፀኞችንም ልብ እግዚአብሔር ወደ መልካም እንዲቀይር በጸሎት ተማጽነዋል።

በደቡባዊው ካይሮ በሚገኘው የኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ላይ ጥቃት ካደረሱት ታጣቂዎች መካከል ሦስቱ በመንግሥት የጸጥታ አስከባሪዎች መገደላቸው ታውቋል።

በግብጽ ከዚህ በፊት፣ በአናሳ ኮፕት ኦርቶዶክሶች ላይ በተሰነዘረው ጥቃት 100 ሰዎች መገደላቸውና በርካታ ሰዎችም መቁሰላቸው የሚታወስ ሲሆን ይህን ጥቃት ተከትሎ የግብጽ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገጉና ወደ ከተማዋ በሚያስገቡ ዋና ዋና መንገዶች ጠንካራ የጸጥታ አስከባሪ ሃይልን በማሰማራት ጥብቅ የፍተሻ ኬላዎችን ማቆሙ ይታወቃል።

የቅዱስነታቸው ጸሎት ለጥቃቱ ሰለባ ለሆኑት ሰዎች ብቻ ሳይሆን በመላው የአገሪቱ ክፍሎች ሰላም እንዲወርድ እንደሆነ ታውቋል።   

 

 








All the contents on this site are copyrighted ©.