2017-12-28 14:27:00

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በሆንዱራሱ ሊቀ ጳጳስ ላይ በተጠነሰሰው የሐሰት ክስ የተሰማቸውን ቅሬታ ገለጹ።


ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በሆንዱራሱ ሊቀ ጳጳስ ላይ በተጠነሰሰው የሐሰት ክስ የተሰማቸውን ቅሬታ ገለጹ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በሆንዱራስ ከተጉሲጋልፓ ሊቀ ጳጳስ፣ ካርዲናል ኦስካር አንድረ ሮድሪገስ ማራዲያጋ ጋር የስልክ መልዕክት መለዋወጣቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው በንግግራቸው፣ በካርዲናሉ ላይ የቀረበው የሐሰት ክስ፣ ባሁን ወቅት በቅድስት መንበር በመካሄድ ላይ ያለውን የተሃድሶ ሂደትን ከሚቃወሙ ግለሰቦች የተሰነዘረ ጥቃት እንደሆነ ገልጸዋል።

የዚህን ዜና ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

ሱያፓ ከተሰኘው የቤተክርስቲያን ቴለቪዥን ጣቢያ በኩል ከሊቀ ጳጳሱ ጋር የተደረገው ቃለ ምልልስ፣ ሊቀ ጳጳሱ የሆንዱራስ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ቻንስለር ሆነው በሚሰሩበት ጊዜ የተሰበሰበውንና ትልቅ አሃዝ ያለውን የዩኒቨርሲቲውን ገንዘብ እንዴት እንደተጠቀሙት የሚጠይቅ ነበር ተብሏል። ይሁንና ሊቀ ጳጳሱ ለቃለ ምልልሱ በቂ ምላሽ ሰጥተው ክሶችንም ተቃውመዋል።

የተጉሲጋልፓ ሊቀ ጳጳስ፣ ካርዲናል ኦስካር አንድረ ሮድሪገስ ማራዲያጋ፣ በቅድስት መንበር የሚካሄደውን  የተሃድሶ ሂደት ለማራመድ በተቋቋመው ምክር ቤት ውስጥ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ለማገዝ ከተሰየሙት ዘጠኝ ካርዲናሎች አንዱ መሆናቸው ታውቋል።

ሊቀ ጳጳስ ኦስካር አንድረ ሮድሪገስ እንደገለጹት እስካሁን ባበረከቱት አገልግሎት መልካም ስምና ዝናን ከማትረፍ ባሻገር ሌሎች አቢያተ ክርስቲያናትንም ሲያግዙ እንደቆዩ ተናግረዋል። ሊቀ ጳጳሱ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ያደረጉትን የስልክ መልዕክት ልውውጥ በማስመልከትም፣ ቅዱስነታቸው በተመሰረተብኝ የሐሰት ክስና፣ በሰዎች ክፋት እጅግ ማዘናቸውን ገልጸው ብርታትን ተመኝተውልኛል ብለዋል። ሊቀ ጳጳስ ኦስካር አንድረ ሮድሪገስም በበኩላቸው “የእያንዳንዱን ሰው ልብ መርምሮ ከሚደርስ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ስላለሁ፣ በውስጤ ሰላም ይሰማኛል ማለታቸውን ገልጸዋል።

በተጉሲጋልፓ ሊቀ ጳጳስ፣ በካርዲናል ኦስካር አንድረ ሮድሪገስ ማራዲያጋ የቀረበው ክስ፣ ኤስፕረሶ ለተባለ የዜና ማሰራጫ ተቋም ለሚሰራ ጋዜጠኛ በኩል እንደሆነ ታውቋል። ክሱም ሊቀ ጳጳሱ ከሆንዱራስ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ የተከፈላቸውንና በብዙ ሺህዎች የሚቆጠር ዩሮን አግባብ በሌለው መንገድ ተጠቅመዋል የሚል እንደሆነ ሲነገር፣ ሊቀ ጳጳስ ማራዲያጋ በበኩላቸው ገንዘቡን ለግል ጥቅም እንዳላዋሉት ነገር ግን ደሆችን ለመርዳት፣ ለሕክምና አገልግሎትና በገጠራማው አካባቢ በሚገኙት ቁምስናዎች ውስጥ ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን ለሚያበረክቱት ካህናት እገዛ እንዳዋሉት አስረድተዋል።    

ሊቀ ጳጳስ ክሱ በእውነት ላይ የተመሠረተ እንዳልሆነ አረጋግጠው፣ ክሱን ያቀረበው ጋዜጠኛ ሞያዊ ብቃት የሚያንሰው፣ እምነተ ቢስና ያለ አግባብ የሚከፈለው ካሉ በኋላ ምንም ዓይነት መረጃን ይፋ ከማድረግ አስቀድሞ እርግጠኛ መሆን እንድሚያስፈልግ አሳስበዋል።

በቅድስት መንበር የሚካሄደውን የተሃድሶ ሂደት ለማራመድ የተቋቋመው ምክር ቤት፣ በሊቀ ጳጳስ ኦስካር አንድረ ሮድሪገስ የተመሰረተው ክስ ከአንድ ዓመት በኋላ የቀረበበት ምክንያት ግልጽ እንዲሆን ጠይቆ፣ በካርዲናሉ ላይ የቀረበው የሐሰት ክስ፣ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና እርሳቸው በሚያካሂዱት  የተሃድሶ ሂደት ላይ የተደረገ ጥቃት ነው ብለዋል።

የተጉሲጋልፓ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ካርዲናል ኦስካር አንድረ ሮድሪገስ ማራዲያጋ በመጨረሻም ለ39 ዓመታት በጳጳስነት ማዕረግ፣ ለ25 ዓመታት በሊቀ ጳጳስነት ማዕረግ ማገልገላቸዉን ገልጸው፣ ይህ ለቤተክርስቲያን ያበረከትኩት ቅን አገልግሎት ለጡረታ ስደርስ፣ ሰላም በሰፈነበት የመኖር አጋጣሚን ይፈጠርብኛል ብለዋል።        

   

 

 
All the contents on this site are copyrighted ©.