2017-12-23 15:47:00

የታህሣሥ 15 ቀን 2010 ዓ.ም. ቃለ እግዚኣብሔር እና የወንጌል አስተንትኖ በክብር አባ ግርማቸው ተስፋዬ


 

የታህሣሥ 15 ቀን 2010 .. ቃለ እግዚኣብሔር እና የወንጌል አስተንትኖ

በኩብር አባ ግርማቸው ተስፋዬ

 

የዚህን ዝግጅት ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

የእለቱ ምንባባት

ቅዱስ ሐዋሪያ ጳውሎስ ወደ ሮም ሰዎች የጻፈው መልእክት  1311-14

 

ዘመኑን በማስተዋል ይህን አድርጉ፤ ከእንቅልፋችሁ የምትነቁበት ጊዜ አሁን ነው፤ መዳናችን መጀመሪያ ካመንበት ጊዜ ይልቅ አሁን ወደ እኛ ቀርቦአልና። ሌሊቱ ሊያልፍ፣ ቀኑም ሊጀምር ነው። ስለዚህ የጨለማን ሥራ ጥለን፣ የብርሃንን ጦር ዕቃ እንልበስ። በቀን እንደምንመላለስ በአግባብ እንመላለስ። በጭፈራና በስካር አይሁን፤ በዝሙትና በመዳራት አይሁን፤ በክርክርና በቅናትም አይሁን። ይልቁንም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት፤ ምኞቱንም ይፈጽም ዘንድ ለሥጋ በሐሳባችሁ አትመቻቹለት።

 

1 ዮሐ. 1፡1-10

የሕይወት ቃል

ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውን፣ የሰማነውን፣ በዐይኖቻችን ያየነውን፣ የተመለከትነውንና እጆቻችን የዳሰሱትን እንናገራለን። ሕይወት ተገለጠ፤ እኛም አይተነዋል፤ እንመሰክርለታለንም። በአብ ዘንድ የነበረውን፣ ለእኛም የተገለጠልንን የዘላለም ሕይወት እንነግራችኋለን፤ እናንተም ከእኛ ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ፣ ያየነውንና የሰማነውን እንነግራችኋለን፤ ኅብረታችንም ከአብ፣ ከልጁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው። ደስታችንም ፍጹም ይሆን ዘንድ ይህን እንጽፍላችኋለን።

በብርሃን መመላለስ

ከእርሱ የሰማነው ለእናንተም የምንነግራችሁ መልእክት፣ እግዚአብሔር ብርሃን ነው፤ ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም፤ የሚል ነው። በጨለማ እየተመላለስን ከእርሱ ጋር ኅብረት አለን ብንል እንዋሻለን፤ እውነትንም አንኖረውም። ነገር ግን እርሱ በብርሃን እንዳለ፣ እኛም በብርሃን ብንመላለስ እርስ በእርሳችን ኅብረት አለን፤ የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኀጢአት ሁሉ ያነጻናል።

ኀጢአት የለብንም ብንል፣ ራሳችንን እናስታለን፤ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም። ኀጢአታችንን ብንናዘዝ ኀጢአታችንን ይቅር ሊለን፣ ከዐመፃ ሁሉ ሊያነጻን እርሱ ታማኝና ጻድቅ ነው። ኀጢአት አልሠራንም ብንል፣ እርሱን ሐሰተኛ እናደርገዋለን፤ ቃሉም በእኛ ውስጥ የለም።

 

 

 

 

ዮሐንስ ወንጌል  1፡1-18

ቃል ሥጋ ሆነ

በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። እርሱም በመጀመሪያ ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ። ሁሉ ነገር በእርሱ ተፈጥሮአል፤ ከተፈጠረው ሁሉ ያለ እርሱ የተፈጠረ ምንም የለም። ሕይወት በእርሱ ነበረች፤ ይህች ሕይወት የሰው ብርሃን ነበረች። ብርሃንም በጨለማ ያበራል፤ ጨለማውም አላሸነፈውም።

ከእግዚአብሔር የተላከ ዮሐንስ የተባለ አንድ ሰው ነበረ። ሰዎች ሁሉ በእርሱ በኩል እንዲያምኑ፣ ስለ ብርሃን ምስክር ሆኖ ለመቆም መጣ፤ ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ እንጂ እርሱ ራሱ ብርሃን አልነበረም። ለሰው ሁሉ ብርሃን ሰጪ የሆነው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም እየመጣ ነበር።

እርሱ በዓለም ውስጥ ነበረ፤ ዓለም የተፈጠረው በእርሱ ቢሆንም እንኳ፣ ዓለም አላወቀውም። ወደ ራሱ ወገኖች መጣ፤ የገዛ ወገኖቹ ግን አልተቀበሉትም፤ ለተቀበሉትና በስሙ ላመኑት ሁሉ ግን የእግዚአብሔር ልጆች የመሆን መብት ሰጣቸው። እነዚህም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ፣ ከደምወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም።

ቃልም ሥጋ ሆነ፤ በመካከላችንም አደረ፤ እኛም ጸጋንና እውነትን ተሞልቶ ከአባቱ ዘንድ የመጣውን የአንድያልጅን ክብር አየን። ዮሐንስም፣ “ ‘ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ በፊት ስለ ነበረ ከእኔ ይልቃል’ ብዬ የመሰከርሁለት እርሱ ነው” በማለት ጮኾ ስለ እርሱ መሰከረ። ከእርሱ ሙላት ሁላችንም በጸጋ ላይ ጸጋ ተቀብለናል፤ ሕግ በሙሴ በኩል ተሰጥቶ ነበር፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል መጣ። ከቶውንም እግዚአብሔርን ያየ ማንም የለም፤ ነገር ግን በአብ እቅፍ ያለው አንድያ ልጁየሆነው አምላክ እርሱ ገለጠው።

 

የታህሣሥ 15 ቀን 2010 .. ቃለ እግዚኣብሔር እና የወንጌል አስተንትኖ

በኩብር አባ ግርማቸው ተስፋዬ

 

 

በክርሰቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ ዛሬ እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት አቆጣጠር ዘብርሃን ወይንም ዘስብከት 2ኛ ሰንበትን እናከብራለን ፡፡

በዚህም ዕለት የእግዚአብሔር ጸጋና በረከት በዝቶልን በቤቱ ሰብስቦናል ቃሉንም እንድንካፈል አድርጐናልና የእግዚአብሔር ሥም ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የተመሰገነ ይሁን፡፡

እግዚአብሔር ቃሉን ሲያካፍለን አድማጮች ብቻ ሣይሆን በተግባርም ለማዋል እንድንችል አእምሮአችንን ያብራልን መንፈሳችንን ያነሳሳልን ፡፡ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ ሲነበብ እንደሰማነው “ከእንቅልፍችሁ ተነሱ ይለናል” ይህ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ የሚጠቅሰው እንቅልፍ ጠዋት በተለምዶ የምንሳውን እንቅልፍ ሳይሆን “ከመንፈሳዊ እንቅልፋችሁ ተነሱ” ማለቱ ነው፡፡ ከአንድ ሰው ስለመንፈሳዊ ሕይወቱ ምንም ሳይጨነቅ የሥጋውን ፍላጐት ብቻ በሟሟላት የሚኖር ከሆነ በእርግጥም የዛ ሰው መንፈሳዊነት ሕይወቱ ተኝቷል፡፡ ሰው ቆሞ የሚሔደው በሥጋና በነፍስ ወይንም ደግሞ በስጋና በመንፈስ ነው፡፡  ለሥጋችን የምናደርገውን ዓይነት እንክብካቤ ለመንፈሳዊነታችንም ልንሰጥ ይገባል፡፡ ምክንያቱም ሰው የሁለቱ የሥጋና የነፍስ ጥምረት እንጂ የአንዳቸው ብቻ ውጤት አይደለም፡፡

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ “ከእንቅልፍችሁ ንቁ ብሎናል” ከእንቅልፋችሁ ከነቃችሁ በኃላ “የብርሃን የጦር መሣሪያ የሆነውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልበሱት” ይለናል፡፡ የብርሃን የጦር መሣሪያ ከያዝን ጨለማን እናሸንፋለን፡፡  የኃጢያት መገለጫ የሆነውን ጨለማንና የኃጢያት አባት የሆነውን ሰይጣንን እናሸንፍለን፡፡

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ የጨለማ ሥራ ምን እንደሆነ በሮሜ. 1፡29-31 እና በገላ. 5፡19-21 በዝርዝር ይናገራል፡፡ (ሥሥት፣ ማታለል፣ምቀኝነት፣ ዝሙት፣ ጣኦትን ማምለክ፣ ቁጣ፣መለያየት ወዘተ) ናቸው ይላል፡፡

ለዚህ ነው ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ከእንቅልፋችን እንንቃ የሚለው ከእነዚህ ኃጢያቶች አንዱ እንኳን በውስጣችን ካለ በምሥጢረ ንስሐ አማካኝነት ከውስጣችን አውልቀን እንጣለው ጨለማን ከውስጣችን እናስወግድ፡፡ የብርሃን የጦር መሳሪያ የሆነውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስንም እንልበስ ይህ ኃጢያት ይህ ጨለማ ወደ ውስጣችን ተመልሶ ለመግባት ቢሞክር እንኳን በያዝነው የጦር መሣሪያ እንዋጋው እናሸንፈዋለን፡፡

ቅዱስ ሐዋርያው ዮሐንስ በ1ኛ መልእክቱ  በዚህ ሐሳብ ላይ ይቀጥላል “ስለሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችን ያየነውንና በእጆቻችንም የዳሰሰነውን እናወራለን፡፡  እንመሰክራለን ይላል፡፡  ይህም እግዚአብሔር ብርሃን ነው ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም” የሚል ነው፡፡

በክርሰቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ወገኖች “ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ሕብረት አለን ብለን በጨለማም የምንመላለስ ከሆንን ግን እንዋሻለን” ብርሃንና ጨለማ በአንድ ጊዜ ሊከሰቱ እንደማይችሉት ሁሉ በኃጢያት እየተመላለስን የእግዚአብሔርን ልጆች ለመሆን አንችልም፡፡ ስለዚህ በውስጣችን ያለን ማንናውንም ዓይነት ጨለማ ወይንም ኃጢያት ልናስወግድው ይገባናል፡፡

በውስጣችን በልባችን የክርስቶስ ብርሃን አለ፡፡  ይህ በልባችን ያለ ብርሃን ኃጢያት በሰራን ጊዜ ይደበዝዛል ደግመን ኃጢያት በሠራን ቁጥር ይበልጥ እየደበዘዘ ይሄዳል በምሥጢረ ንሰሐ አማካኝንተ ደግሞ ይህ የደበዘዘው ብርሃን እንደገና ይደምቃል፡፡ ይህ በውስጣችን የፈነጠቀው ብርሃን  በተደጋጋሚ በምንሰራው ኃጢያት ምክንያት ደብዝዞ በምሥጢረ ንሰሐ አማካኝነት ካልበራና ሙሉ በሙሉ ከጠፋ ሕይወታችን በእርግጥም አደጋ ላይ ነው ሠይጣንም በቀላሉ ወደ ፈለገው አቅጣጫ ይመራናል፡፡

ጌታችን ኢየሱሱ ክርስቶስ ግን በዚህም ጊዜ ከጎናችን አይለይም “ሸክማችሁ የከበዳችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ እያለ በብርሃኑ ሊሞላን ይጠራናል፡፡” ቅዱስ ሐዋርያው ዮሐንስ በወንጌሉ ስለዚሁ ብርሃን ይናገራል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቃል እንደሆነ፣ ሕይወት እንደሆነ፣ ብርሃን እንደሆነ ይናገራል፡፡ ስለዚህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር ሲመጣ ይህንን ሕይወትና ይህንን ብርሃን ይዞልን መቷል፡፡

በጥምቀታችን አማካኝነት ይህንን ሕይወትና ይህንን ብርሃን ተቀብለናል፡፡ በዚህ መንፈሳዊ ሕይወትና ብርሃን ስንመላለስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ማየት እንችላለን፡፡  ይህ ብርሃን ከውስጣችን ከጠፋ ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መመልከት አንችልም ምክንያቱም በኃጢያት ምክንያት ውስጣችን ጨልሟልና ነው፡፡ ዮሐንስ ወንጌል 11፡10 ላይ በጭለማ የሚመላለስ ቢኖር ግን ብርሃን በእርሱ ስለሌለ ይሰናከላል ይላል፣ ስለዚህ ዘወትር ብርሃን የሆነውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ይዘን በብርሃን እንድንመላለስ ተጠርተናል፡፡

መጥምቁ ዮሐንስም ብርሃን የሆነውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ምድር ጨለማን ለማጥፋት እንደመጣ ሲመሰክር ሰምተናል፣  እኛም ይህንን ምስክርነት ተቀብለን በእውነተኛ ብርሃን እንድንመላለስ የኃጢያተኞች መማጠኛ የክርስቲያኖች ረዳት የሆነች እናታችን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጇ  ታማልደን  በእግዚአብሔር ፈት ጠበቃ ሆኖ ትቁምልን፡፡ አሜን!
All the contents on this site are copyrighted ©.