2017-12-16 14:33:00

የታህሣሥ 8/2010 ዓ.ም. የስብከተ ገና 1ኛ ሣምንት ምንባባት እና አስተንትኖ በክቡር አባ ግርማቸው ተስፋዬ


የታህሣሥ 8/2010 ዓ.ም. የመጀመሪያው የስብከተ ገና ሰንበት ቃለ እግዚኣብሔር በክቡር አባ ግርማቸው ተፋዬ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ካህን

የዚህን አስተንትኖ ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያሉትን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

 

የእለቱ ምንባባት

 

  1. ዕብ 1፡1-14

ልጁ ከመላእክት በላይ ነው

እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ በተለያየ ጊዜና በልዩ ልዩ መንገድ በነቢያት በኩል ለአባቶቻችን ተናግሮ፣ በዚህ መጨረሻ ዘመን ግን ሁሉን ወራሽ ባደረገውና ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ ለእኛ ተናገረን። እርሱ የእግዚአብሔር ክብር ነጸብራ ቅና የባሕርዩ ትክክለኛ ምሳሌ ሆኖ፣ በኀያል ቃሉ ሁሉን ደግፎ ይዞአል፤ የኀጢአት መንጻት ካስገኘ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ። ስለዚህ የወረሰው ስም ከመላእክት ስም እንደሚበልጥ ሁሉ፣ እርሱም ከመላእክት እጅግ የላቀ ሆኖአል።

እግዚአብሔር፣ “አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ፤” ወይስ ደግሞ፣ “እኔ አባት እሆነዋለሁ፤ እርሱም ልጅ ይሆነኛል” ያለው ከመላእክት ከቶ ለማን ነው? ደግሞም እግዚአብሔር በኵሩን ወደ ዓለም ሲያስገባ፣ “የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉ ይስገዱለት” ይላል። ስለ መላእክትም ሲናገር፣ “መላእክቱን ነፋሳት፣ አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል ያደርጋል” ይላል። ስለ ልጁ ግን እንዲህ ይላል፤“አምላክ ሆይ፤ ዙፋንህ ከዘላለም እስከ ዘላለም ጸንቶ ይኖራል፤ ጽድቅም የመንግሥትህ በትር ይሆናል፤ ጽድቅን ወደድህ፤ ዐመፃን ጠላህ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክህ ከባልንጀሮችህ በላይ አስቀመጠህ፣ የደስታንም ዘይት ቀባህ።”

ደግሞም እንዲህ ይላል፤ “ጌታ ሆይ፤ አንተ በመጀመሪያ የምድርን መሠረት አኖርህ፤ ሰማያትም የእጆችህ ሥራ ናቸው።

እነርሱ ይጠፋሉ፤ አንተ ግን ጸንተህ ትኖራለህ፤ ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ፤ እንደ መጐናጸፊያ ትጠቀልላቸዋለህ፤ እንደ ልብስም ይለወጣሉ። አንተ ግን ያው አንተ ነህ፤ ዘመንህም ፍጻሜ የለውም።”

እግዚአብሔር፣ “ጠላቶችህን የእግርህ መርገጫ እስከማደርግልህ ድረስ፣ በቀኜ ተቀመጥ” ያለው ከመላእክት ከቶ ለማን ነው? መላእክት ሁሉ መዳንን የሚወርሱትን ለማገልገል የሚላኩ አገልጋይ መናፍስት አይደሉምን?

2. ጴጥ. 3፡1-19

የጌታ ቀን

ወዳጆች ሆይ፤ ይህ አሁን የምጽፍላችሁ ሁለተኛው መልእክት ነው። ሁለቱንም መልእክቶች የጻፍሁላችሁ ቅን ልቦናችሁን እንድታነቃቁ ለማሳሰብ ነው፤ ደግሞም ቀድሞ በቅዱሳን ነቢያት የተነገረውን ቃል እንዲሁም በሐዋርያት አማካይነት በጌታችንና በአዳኛችን የተሰጠውን ትእዛዝ እንድታስቡ ነው።

ከሁሉ አስቀድሞ ይህን ዕወቁ፤ በመጨረሻው ዘመን የራሳቸውን ክፉ ምኞት የሚከተሉ ዘባቾች እየዘበቱ ይመጣሉ። እነርሱም፣ “ ‘እመጣለሁ’ ያለው ታዲያ የት አለ? አባቶች ከሞቱበት ከፍጥረት መጀመሪያ አንሥቶ እስካሁን ድረስ ሁሉም ነገር እንዳለ ይኖራል” ይላሉ። ነገር ግን እነዚህ ሰዎች ሰማያት ከጥንት ጀምሮ በእግዚአብሔር ቃል ተፈጥረው እንደሚኖሩ፣ መሬትም በውሃ መካከልና በውሃም እንደ ተሠራች ሆን ብለው ይክዳሉ፤ በዚያን ጊዜ የነበረው ዓለም በውሃ ተጥለቅልቆ ጠፋ። በዚያው ቃል ደግሞ አሁን ያሉት ሰማያትና ምድር፣ ኀጢአተኞች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ለእሳት ተጠብቀዋል።

ወዳጆች ሆይ፤ በጌታ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ ዓመት፣ ሺህ ዓመትም እንደ አንድ ቀን መሆኑን ይህን አንድ ነገር አትርሱ። አንዳንድ ሰዎች የዘገየ እንደሚመስላቸው ጌታ የተስፋ ቃሉን ለመፈጸም አይዘገይም፤ ነገር ግን ማንም እንዳይጠፋ ፈልጎ፣ ሁሉ ለንስሓ እንዲበቃ ስለ እናንተ ይታገሣል።

የጌታ ቀን ግን እንደ ሌባ ይመጣል፤ በዚያች ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፤ የሰማይም ፍጥረት በእሳት ይጠፋል፤ ምድርና በእርሷም ላይ ያለ ነገር ሁሉ ይቃጠላል።

እንግዲህ ሁሉም ነገር በዚህ ሁኔታ የሚጠፋ ከሆነ፣ እናንተ እንዴት ዐይነት ሰዎች ልትሆኑ ይገባችኋል? አዎን፣ በቅድስናና በእውነተኛ መንፈሳዊነት ልትኖሩ ይገባችኋል፤ ደግሞም የእግዚአብሔርን ቀን እየተጠባበቃችሁ መምጫውን ልታፋጥኑ ይገባል። በዚያን ቀን ሰማያት በእሳት ተቃጥለው ይጠፋሉ፤ የሰማይም ፍጥረት በታላቅ ትኵሳት ይቀልጣል። እኛ ግን ጽድቅ የሚኖርበትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር በተስፋ ቃሉ መሠረት እንጠባበቃለን።

ስለዚህ ወዳጆች ሆይ፤ እነዚህን ሁሉ ነገሮች የምትጠባበቁ ስለ ሆናችሁ፣ ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ከእርሱ ጋር በሰላም እንድትገኙ ትጉ። የጌታችን ትዕግሥት እናንተ እንድትድኑ እንደሆነ አስቡ፤ እንዲሁም ወንድማችን ጳውሎስ እንደ ተሰጠው ጥበብ መጠን ጻፈላችሁ፤ እርሱ ስለ እነዚህ ነገሮች በመልእክቶቹ ሁሉ ጽፎአል፤ በመልእክቶቹም ውስጥ በቀላሉ ለመረዳት የሚያዳግቱ ነገሮች አሉ። ዕውቀት የጐደላቸውና ጽናት የሌላቸው ሰዎች ሌሎችን ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ፣ እነዚህንም ደግሞ ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ።

እንግዲህ ወዳጆች ሆይ፤ ይህን አስቀድማችሁ ስላወቃችሁ፣ ጸንታችሁ ከቆማችሁበት መሠረት በዐመፀኞች ስሕተት ተስባችሁ እንዳትወድቁ ተጠንቀቁ። ነገር ግን በጌታችንና በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ዕውቀት እደጉ፤ ለእርሱ አሁንም፣ ለዘላለምም ክብር ይሁን፤ አሜን።

3. ወንጌል 1፡44-51

ፊልጶስም እንደ እንድርያስና እንደ ጴጥሮስ ሁሉ የቤተ ሳይዳ ከተማ ሰው ነበረ። ፊልጶስ ናትናኤልን አግኝቶ፣ “ሙሴ በሕግ መጻሕፍት፣ ነቢያትም ስለ እርሱ የጻፉለትን የዮሴፍን ልጅ የናዝሬቱ ኢየሱስን አግኝተነዋል” አለው። ናትናኤልም፣ “ከናዝሬት በጎ ነገር ሊወጣ ይችላልን?” አለ። ፊልጶስም፣ “መጥተህ እይ” አለው።

ኢየሱስም፣ ናትናኤል ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ፣ “እነሆ፤ ተንኮል የሌለበት እውነተኛ እስራኤላዊ” አለ። ናትናኤልም “እንዴት አወቅኸኝ?” ሲል ጠየቀው።

ኢየሱስም፣ “ከበለስ ዛፍ ሥር ሳለህ፣ ገና ፊሊጶስ ሳይጠራህ አየሁህ” ሲል መለሰለት። ናትናኤልም መልሶ፣ “ረቢ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ” አለ።

ኢየሱስም፣ “ያመንኸው ከበለስ ዛፍ ሥር አየሁህ ስላልሁህ ነውን? ገና ከዚህ የሚበልጥ ነገር ታያለህ” አለው፤ ጨምሮም፣ “እውነት እላችኋለሁ፣ ሰማይ ተከፍቶ፣ የእግዚአብሔርም መላእክት በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ” አለው።

የታህሣሥ 8/2010 ዓ.ም. የመጀመሪያው የስብከተ ገና ሰንበት ቃለ እግዚኣብሔር በክቡር አባ ግርማቸው ተፋዬ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ካህን

በክርሰቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም መልካም ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ ዛሬ እንደ ቤተክርስቲያናችን አቆጣጠር ዘስብከተ ገናን 1ኛ ሰንበትን እናከብራለን ፡፡ ዛሬም እግዚአብሔር በቤቱ ሰብስቦናል በቃሉም ያስተምረናልና የእግዚአብሔር ስም የተመሰገነ ይሁን፡፡

በመጀመሪያው መልዕክት ሲነበብ እንደሰማነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ መሆኑን ይናገራል፡፡ ይህ አንድያ ልጅ ወደ ምድር ከመምጣቱ አስቀድሞ ስልጣንና ኃይል ሁሉ የእርሱ እንደነበረ በማቴ. 28፡ 18 ይገለፃል፡፡ እግዚአብሔር ዓለምን ሁሉ የፈጠረው ከዚህ ከአንድያ ልጁ ጋር መሆኑን የዩሐንስ ወንጌል ም.1 ይናገራል፡፡ “በመጀመሪያ ቃል ነበር ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበር ቃልም እግዚአብሔር ነበር፡፡  ሁሉ በእርሱ ሆነ ከሆነውም አንዳች እንኳን ያለ እርሱ አልሆነም፡፡”

ነቢያቶች አስቀድመው የተነበዩለት መላእክትም በፊቱ ቅዱስ፣ ቅዱስ እያሉ የሚያገለግሉት ይህንኑ አምላክ መሆኑን ዳዊት በመዝሙር 27፡7 ላይ ተናግሮታል፡፡ ስለዚህ በምድር ላይ የተፈጠረው ሁሉ የእርሱ ነው እኛንም በአምሳሉ የፈጠረን እርሱ ነው፡፡ ለዚህ ለፈጠረን ላዳነነ አምላካችን እኛም የድርሻችንን ክብርና አምልኮ ልናቀርብለት ይገባል፡፡ ለእግዚአብሔር አምላካችን የምናቀርበው ክብርና አምልኮ አይሁዳውያን ያቀርቡ እንደነበረው  የሚቃጠል መስዋት ሳይሆን በእርሱ ቃል የሚኖር፣ በእርሱ ተስፋ የሚኖር የተፀፀተና ከኃጢያት የነፃ ልባችንን ሊሆን ይገባል፡፡

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ዛሬ በተነበበው በእብራውያን መልእክቱ የሚያስተምረን ይህን ነው ፤ ከሁሉ አስቀድመን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፈጣሪያችን መሆኑን እንድናውቅና ወደን እንድንቀበል ከዛም ለእርሱ ትዕዛዝ ተገዝተን በቃሉ እንድንኖር ለማድረግ ነው፡፡

2ኛ የጴጥ. 3፡1-9 ላይም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  ዳግመኛ የሚመጣበት ጊዜ ስለዘገየ ከእንግዲህ አይመጣም የዓለም ፍጻሜ የማባል ነገር አይኖርም በማለት አንዳንድ የሐሰትን ትምህርት የሚየስተምሩ ነበሩ፡፡ ነገር ግን የእርሱ መዘግየት እኛ ልጆቹ ከክፉ ሥራችን የምንመለስበትንና ከኃጢያታችን ፀድተን እንዲያገኘን በመፈለጉ ብቻ ነው፡፡ ደጋጋመን በምንሰራው ኃጢያታችን ምክንያት የቆሸሸውን ልባችንን ሕሊናችንን እንድናፀዳ ጊዜ ስለሰጠን ብቻ ነው፡፡ ጊዜና ቦታ በእኛ በሰዎች አመለካከት እንጂ እግዚአብሔር በጊዜ አይወሰንም፣ እግዜአብሔር መጀመሪያና መጨረሻ የለውም፣ እግዚአብሔር በቦታ አይወሰንም፤ ስለዚህ ነው በቁ.8 ላይ በጌታ ዘንድ አንድ ቀን አንደ ሺ ዓመት ሺ ዓመት ደግሞ እንደ አንድ ቀን ይቆጠራል የሚለው፡፡

የክርስቶስ መምጣት ለእኛ የዘገየ ቢመስለንም ጥቅሙ ግን ለእኛው ነው በደንብ ተዘጋጅተን ከኃጢያታችን ጸድተን የዘለዓለም ሕይወት ወራሾች በመሆን የዘለዓለዊ ደስታን እንድንገኝ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰዎች አንድ እንኳ እንዲጠፋ አይፈልገም ለዚህም ጊዜ ሰጥቶናል፡፡  በዚህ ጊዜ ውስጥ እንድንዘጋጅ ያስፈልጋል፣፣  ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደንገት በሚመጣበት ጊዜ ለመዘጋጀት ጊዜ አይኖርም፡፡ የኖህ መርከብ  በሩ ከተዘጋ በኃላ እንዳልተከፈተና በመርከቡ ያልገቡት ሁሉ እንደጠፉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በድንገት በሚመጣበትም ጊዜ እኛም እንዳንጠፋ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰጠን ጊዜ ውስጥ መዘጋጀቱ ተገቢ ነው፡፡

በዮሐንስ ወንጌል 1፡44-51  ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንድርያስን እና ስምኦንን እንደጠራ ሁሉ ፊሊጶስንና ናትናኤልንም ጠራቸው የእርሱን ሕይወት መስካሪ አደረጋቸው፡፡ ይህ የሚመሰክሩት ሕይወት ምንድን ነው?  ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማይ ወርዶ ሰው ሆኖ ስለ እኛ መዳን ሲል ተሰቃይቶ ተሰቅሎ ሞቶ ተቀብሮ በ3ኛው ቀን ከሙታን በመነሳት አንዳዳነን  ከኃጢያት ቀንበር ነፃ እንደወጣን የመሰክራሉ፡፡ እነዚህ ሐዋርያቶች ይህንን ምስክርነት ሲሰጡ በሕይወታቸው ብዙ መከራና ሥቃይ ደርሶባቸዋል፡ አብዛኞቹም ሰማዕታት ሆነዋል፡፡

ዛሬም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን ጥሪ ለእያንዳዳችን  ይልካል ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንድንመሰክር ይፈልጋል፡፡ ምን አልባት ልክ እንደጥንቱ ክርስቲያኖችና ነቢያቶች የደም ምሥክርነት ባይሆንም የሕይወት ምሥክርነት እንዲኖረን ይፈልጋል፡፡ እንደ እውነተኛ ክርስቲያኖች እንድንኖር ይፈልጋል፡፡ በዚሁ ወንጌል ላይ ናትናኤል ወደ ክርስቶስ በቀረበ ጊዜ ጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እርሱ ምስክርነቱን ሰቷል “እነሆ ተንኮል የሌለበት እውነተኛ እስራኤላዊ” ቁ47፣ ይህም የሚያሳየን እግዚአብሔር ምንም እንኳን ደካሞች ብንሆንም የልብ ቅንነት ያላቸውን ሰዎች ይወዳል፣ ለተንኮል ራሳቸውን የማያዘጋጁትን ሰዎች ያቀርባል፣ ለንስሃ የተዘጋጁትን ልቦች የፈውሳል፣ ምስክሮቹም ያደርጋቸዋል ስለዚህ እኛም ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ እንዳለው እንደ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በእግዚአብሔር ጸጋ በመታመን እንደ እርሱ ፈቃድ ለመኖርና ለመመላለስ ምስክሮቹም ለመሆን እንድችል በረከቱን በልባችን ይሙላልን፡፡

እመቤታችን ኪዳነ ምሕረት የክርስቲያኖች ረዳት የሆነች ጸጋና በረከቱን ከልጇ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ታሰጠን፤የሰማነውን በልባችን ያኑርልን፡፡

 








All the contents on this site are copyrighted ©.