2017-12-02 16:04:00

የኅዳር 24/2010 ዓ.ም. የእለተ ሰንበት የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት


የኅዳር 24/2010 ዓ.ም. የእለተ ሰንበት የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት

1. ዕብራዊያን 1225-29

የሚናገረውን እርሱን እምቢ እንዳትሉት ተጠንቀቁ። እነዚያ ከምድር ሆኖ ሲያስጠነ ቅቃቸው የነበረውን እምቢ ባሉ ጊዜ ካላመለጡ፣ እኛ ከሰማይ የመጣው ሲያስጠነቅ ቀን ከእርሱ ብንርቅ እንዴት ልናመልጥ እንችላለን? በዚያን ጊዜ ድምፁ ያናወጠው ምድርን ነበር፤ አሁን ግን፣ “ምድርን ብቻ ሳይሆን፣ ሰማያትንም አንድ ጊዜ ደግሜ አናውጣለሁ” ብሎ ቃል ገብቶአል። አንድ ጊዜ “ደግሜ” የሚለው ቃል የሚያመለክተው የማይናወጡት ጸንተው ይኖሩ ዘንድ፣ የሚናወጡት ይኸውም የተፈጠሩት የሚወገዱ መሆናቸውን ነው።

ስለዚህ ከቶ የማይናወጥ መንግሥት ስለምንቀበል እግዚአብሔርን እናመስግን፤ ደግሞም ደስ በሚያሰኘው መንገድ በአክብሮትና በፍርሀት እናምልከው፤ 29አምላካችን የሚያጠፋ እሳት ነውና።

2. የዕቆብ መልእክት 34-12

እያንዳንዱ ቤት የራሱ ሠሪ አለው፤ ነገር ግን ሁሉን የሠራ እግዚአብሔር ነው። ሙሴ ወደ ፊት ስለሚነገረው ነገር እየመሰከረ፣ በእግዚአብሔር ቤት ሁሉ ላይ እንደ አንድ ታማኝ አገልጋይ ነበር፤ ክርስቶስ ግን በእግዚአብሔር ቤት ላይ እንደ ታማኝ ልጅ ነው። እኛም የምንተማመንበትንና የምንመካበትን ተስፋ አጥብቀን ብንይዝ ቤቱ ነን።

ስለ አለማመን የተሰጠ ማስጠንቀቂያ

ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ እንደሚል፣

“ዛሬ ድምፁን ብትሰሙ፣

በምድረ በዳ በፈተና ቀን፣

በዐመፅ እንዳደረጋችሁት፣

ልባችሁን አታደንድኑ።

አባቶቻችሁ በዚያ ተፈታተኑኝ፤

መረመሩኝ፤ ያደረግሁትንም ሁሉ ለአርባ ዓመት አዩ።

በዚያም ትውልድ ላይ የተቈጣሁት ለዚህ ነበር፤

እንዲህም አልሁ፤ ‘ልባቸው ሁል ጊዜ ይስታል፤

መንገዴንም አላወቁም፤’

ስለዚህ በቍጣዬ እንዲህ ብዬ ማልሁ፤

“ወደ ዕረፍቴ ከቶ አይገቡም።”

ወንድሞች ሆይ፤ ከእናንተ ማንም ከሕያው እግዚአብሔር የሚያስኰበልል፣ ኀጢአተኛና የማያምን ልብ እንዳይኖረው ተጠንቀቁ። 

3.የማቴዎስ ወንጌል 8፡23-34

ኢየሱስ ማዕበሉን ጸጥ አደረገ

ከዚያም ኢየሱስ ወደ ጀልባ ገባ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከትለውት ገብተው ሄዱ። ድንገት ኀይለኛ ማዕበል በባሕሩ ላይ ተነሥቶ ጀልባዪቱን እስኪሸፍን ድረስ አወካቸው፤ በዚህ ጊዜ ግን ኢየሱስ ተኝቶ ነበር። ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው ቀሰቀሱትና፣ “ጌታ ሆይ! ጠፋን፤ አድነን” አሉት።

ኢየሱስም፣ “እናንተ እምነት የጐደላችሁ፤ ለምን ይህን ያህል ፈራችሁ?” አላቸው፤ ከዚያም ተነሥቶ ነፋሱንና ማዕበሉን ገሠጸ፤ ወዲያውም ጸጥታ ሰፈነ። ሰዎቹም፣ “ነፋስና ባሕር እንኳ የሚታዘዙለት፣ ይህ እንዴት ያለ ሰው ነው?” እያሉ ተደነቁ።

ከርኩሳን መናፍስት ስለ ተፈወሱ ሁለት ሰዎች

ባሕሩን ተሻግሮ ጌርጌሴኖን ወደሚባል አገር እንደ ደረሰ፣ አጋንንት ያደሩባቸው ሁለት ሰዎች ከሚኖሩበት የመቃብር ቦታ ወጥተው ተገናኙት። በዚያ መንገድ ሰው ማለፍ እስከማይችል ድረስ እጅግ አደገኞች ነበሩ። እነርሱም “የእግዚአብሔር ልጅ ሆይ፤ ከእኛ ምን ጕዳይ አለህ? ጊዜው ሳይደርስ ልታሠቃየን መጣህን?” እያሉ ጮኹ።

ከእነርሱ ትንሽ ራቅ ብሎ፣ የብዙ ዐሣማ መንጋ ተሰማርቶ ነበር። አጋንንቱም ኢየሱስን፣ “የምታስወጣን ከሆነ ዐሣማዎቹ መንጋ ውስጥ እንድንገባ ፍቀድልን” ብለው ለመኑት። ኢየሱስም፣ “ሂዱ!” አላቸው። አጋንንቱም ከሰዎቹ ወጥተው ዐሣማዎቹ ውስጥ ገቡ፤ ዐሣማዎቹም በሙሉ ከነበሩበት አፋፍ እየተጣደፉ ባሕሩ ውስጥ በመግባት ውሃው ውስጥ ሰጥመው ሞቱ። የዐሣማዎቹ ጠባቂዎችም ሸሽተው ወደ ከተማ በመሄድ፣ የሆነውን ሁሉና በአጋንንት ተይዘው በነበሩት ሰዎች ላይ የተደረገውን ነገር አወሩ። እነሆም፤ መላው የከተማ ነዋሪ ኢየሱስን ለመገናኘት ወጣ፤ ባዩትም ጊዜ አገራቸውን ለቅቆ እንዲሄድ ለመኑት

 

 

 
All the contents on this site are copyrighted ©.