2017-08-20 10:27:00

ማርያም በኢየሱስ ሐዋርያዊ ሥራ ዘመን


ማርያም በኢየሱስ ሐዋርያዊ ሥራ ዘመን

ከልደቱ፣ ከሕጻንነቱ እና ከስቅለቱ አጋጣሚዎች ውጪ እመቤታችን ድንግል ማርያም በኢየሱስ ሕይወት ውስጥ ብዙ ቦታ አልተጠቀሰችም፡፡ ነገር ግን ሦስት ዋና ዋና ቦታዎች ላይ ተጠቅሶ እናገኛታለን፤ እነዚህ ሦስቱ ቦታዎች እያንዳንዳቸው በጣም ወሳኝ የሆነ ሚና ነበራቸው፡፡ የመጀመሪያው የቃና ዘገሊላ ሠርግ (ዮሐ.2፡1-11) ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ኢየሱስ በሕዝብ በተከበበ ቤት ውስጥ በማስተማር ላይ ሳለ ነው፤ (ማቴ.12፡46-50) በመጨረሻም በመስቀል ላይ ተሰቅሎ በሞተ ጊዜ ነው፡፡ (ዮሐ.19፡29-27)

የዚህን አስተምህሮ ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር በቃና ዘገሊላ የሠርግ ግብዣ ላይ ሳለ እናቱ ማርያም ወደ እርሱ ቀርባ ‹‹ወይን እኮ የላቸውም›› አለችው፡፡ ሙሽራው እና ሙሽሪቱ ሀብታሞች አልነበሩም ስለዚህ የነበራቸው ወይን ብዙም ሳይቆይ ተዳክሞ አለቀ፡፡ ማርያም ይህንን ቃል በኢየሱስ ፊት ስታቀርብ የሙሽሮቹ በዓል ከተጋረጠባቸው የውርደት አጋጣሚ ታድጋቸዋለች፡፡ ተዓምር በእርግጥም አስፈላጊ ነበር፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ ለማርያም የሰጣት መልስ የተቃውሞ የሚመስል ነበር ‹‹አንቺ ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም››

ኢየሱስ በማርያም ፊት የቆመው እንደ ልጅ ሆኖ ሳይሆን የአባቱን ፈቃድ እንደሚፈጽም አዳኝ ሆኖ ነው፡፡ ማርያምም የአሥራ ሁለት ዓመት ሕጻን ልጇ በቤተ-መቅደስ በቀረ ጊዜ ፈልጋ ብታገኘው ‹‹ስለምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት እሆን ዘንድ እንደሚገባኝ አላወቃችሁምን?›› (ሉቃ.2፡49) እንዳላት እንዲሁ በዚህም ጊዜ መልስ ሳትሰጥ ቀረች፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ ጥያቄዋን እንደመለሰላት አውቃ ነበርና አገልጋዮቹን ጠርታ፡- ‹‹እርሱ የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ›› አለቻቸው፡፡ ከሰጣት መልስ በተቃራኒው ኢየሱስ ተዓምር እንደሚሠራ እርግጠኛ ነበረች፤ ይህም ከውስጧ የነበረው መገለጥ የሰጣት እውቀት ነው፤ ይህም እውቀት ለእግዚአብሔር እና ለልጇ ራሷን ዝቅ አድርጋ በትሕትና መቅረቧ የሚያመጣው ሽልማት ነው፡፡ እንግዲህ በሙግት ሳይሆን ትሕትና በተሞላበት መንፈስ በመቅረቧ ኢየሱስ ተዓምር እንዲያደርግ እና ‹‹ክብሩን እንዲገልጥ›› በዚህም የመጀመሪያዎቹ ሐዋርያት በእርሱ ላይ ያላቸውን እምነት እንዲያጸኑ አደረገች፡፡ ይህ የተዓምራት ሁሉ የመጀመሪያ የሆነው ተዓምር በማርያም ምልጃ ተከናወነ ‹‹ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ››

ጊዜው ኢየሱስ በገሊላ ክፍለ ሀገር እየተዛወረ የሚያስተምርበት ጊዜ ነበር፤ በአንድ ወቅት በሚያስተምርበት ቤት ዙሪያ እጅግ ብዙ ሕዝብ ተሰብስቦ ትምህርቱን ያደምጥ ነበር፡፡ በእርሱ ላይ የነበረው ተቃውሞም እየጨመረ ነው፤ ሕዝቡም እያመነታ ነበር፡፡ አብርሃም አባታቸው በመሆኑ ብዙ አይሁዳውያን እግዚአብሔር ለእነርሱ የተለየ ፍቅር እንደነበረው እርግጠኛ ነበሩ፡፡ በዚህ መሃል የኢየሱስ እናት ድንገት ‹‹ከወንድሞቹ›› ጋር ብቅ ብላ ሊያነጋግሩት እንደሚፈልጉ ጠቅሰው መልዕክት ላኩበት፡፡

በዚያ ቆመው የነበሩት ኢየሱስ ትምህርቱን አቋርጦ ይወጣል ብለው ነበር፡፡ ግን አልሆነም፡፡ ይልቁንም እጁን ዘርግቶ ወደ ሐዋርያቱ እያመለከተ ‹‹እነሆ እናቴ እና ወንድሞቼ፤ በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ እርሱ ወንድሜ፣ እህቴም እናቴም ነውና›› አለ፡፡ (ማቴ. ) በዚህ ላይ ኢየሱስ በሚመሠርተው አዲሱ የእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ የሥጋ ዝምድና የዘር ሐረግ ዋጋ ቢስ ስለመሆኑ ከአብርሃም ነገድ መሆን ከእንግዲህ እንደማያዘልቅ በግልጽ ለአይሁዳውያን መናገሩ ነው፡፡ ሐዋርያቱም ከዚህ ንግግር ተምረዋል፡፡ የሐዋርያዊ ጥሪው ከደም እና ከሥጋ ወይም ከዘር ሐረግ ግንድ ጋር የተያያዘ እንዳልሆነ ተገንዝበዋል፡፡ ተልዕኮው በጣም አስፈላጊ በመሆኑ ዋናው ነገር የእግዚአብሔርን ፈቃድ መፈጸም ብቻ ነው፡፡

ምናልባትም ወንድሞቹ ኢየሱስ ዕረፍት አልባውን ተግባር ለአፍታ ጋብ እንዲያደርግ ፈልገው ይሆናል፡፡ ለእነርሱ ትርፍ ጊዜ አልነበረውምና፡፡ ማርያም የመጣችው ለራሷ ሌላ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ እናቱን ያዋረዳት ይመስል ይሆናል፤ እዚያ በቆሙት ሰዎች እና በሐዋርያቱ ላይ በጣም የተለየ ስሜት ሊፈጥር ይችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን እናቱ ስለምን እንደሚያወራ ታውቃለች፤ የእርሱ የመሲሕነት ተግባር እናት ልጇ ለማየት ካላት ናፍቆት የበለጠ አስፈላጊ መሆኑን ታውቃለች፡፡ ሌላ እናት ብትሆን ኖሮ በልጇ ንግግር ተከፍታ ፊቷን አዙራ ትመለስ ነበር፡፡ ማርያም ግን በድጋሚ ለእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃድ ራሷን ታዛዥ አድርጋ እናያታለን፤ የልጇ የማዳን ሥራ በሚያስፈልገው መልኩ መሥዋዕትነት መክፈል እንዳለባት በሚገባ ታውቃለች፡፡

ከዚህ በኋላ እመቤታችን ከወንጌል ታሪክ ውስጥ ለጥቂት ጊዜ ተሰውራ ትቆያለች፡፡ ነገር ግን ልጇ የዓለምን ኃጢአት ተሸክሞ ራሱን በሚያዋርድበት እጅግ አሳዛኝ ሰዓት ላይ እንደገና እንደ ፀሐይ ብቅ ትላለች፡፡ በጎሎጎታ መንገድ ከልጇ አጠገብ ሆና በመጓዝ የስምዖን መራራ ትንቢት ይፈጸም ዘንድ መሥዋዕት ትሆናለች፡- ‹‹የአንቺን ነፍስ የኀዘን ሰይፍ ሰንጥቆት ያልፋል›› (ሉቃ.2፡35) ማርያም በጎሎጎታ ቆማ ስንመለከታት ልጇ እየሞተእንዳለባት እናት ሳይሆን የዓለም አዳኝ የመድኃኒዓለም እናት ሆኖ ነው፡፡ ኢየሱስም ለሚወደው ደቀ መዝሙር እንዲህ ይለዋል ‹‹እነኋት እናትህ›› ለእናቱም ደግሞ ‹‹እነሆ ልጅሽ›› ይላታል፡፡ ልጇ የመሆን ስጦታን የተቀበለው ሐዋርያ በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከተዋጁት ሁሉ ጋር የማርያም ልጅ ሆኖ እናትነቷን ይጋራል፡፡ ይህ እንግዲህ እርሷ በመጨረሻ ለከፈለችው ፍጹም ምሉዕ የሆነ መሥዋዕትነት እግዚአብሔር የሰጣት መልስ ነው፡፡ በዚያ ጊዜ እነዚህ ቃላት የነበራቸውን ወደር የለሽ አስፈላጊነት የተረዳ ማንም ሰው አልነበረም፡፡ ማርያምም ብትሆን አሥራ ሁለት ዓመት ልጅ በቤተ መቅደስ በቀረ ጊዜ ስለ አባቱ ፈቃድ ሲናገር የተረዳችው በከፊል ነበር፤ ነገር ግን ከሞቱ እና ከትንሣኤው፣ ከዕርገቱ እና ከመንፈስ ቅዱስ ምጻት በኋላ አዲሲቷ ቤተ-ክርስቲያንን ትንሽ በትንሽ ማደግ ስትጀምር፣ ይሄኔ ማርያም ልጇ በመስቀል ላይ የሰጣትን ተልዕኮ በምልዓት ተረዳችው፡፡

ስለመሲሕ ትንቢት ፍጻሜ የሚተርከው የአዲስ ኪዳን መጽሐፍ ስለመሲሑ እናት የጠቀሰው በጥቂቱ ከሆነ በብሉይ ኪዳን እርሷን የተመለከተ በርካታ ነገር ይኖራል ብለን መጠበቅ የለብንም፡፡ ቃል በቃል ስንመለከተው በቀጥታ ስለ እርሷ የተጠቀሰው በሦስት ቦታዎች ላይ ብቻ ነው፡- ኢሳ.7፡14፣ ሚክ.5፡2-3፣ ኤር.31፡22 እዚህ ላይ ብዙ ጊዜ እንደ ማስረጃ የሚጠቀሰውን ዘፍጥረት 3፡15ን መደመር ይቻላል፡፡ ቃል በቃል ስንተረጉመው ሴቲቱ ሔዋን ስትሆን የሰው ልጆችን በሙሉ ትወክላለች፣ እርሷም የእባቡን አናት እንደምትቀጠቅጥ ተነግሯል፡፡ ነገር ግን ይህ ተንቢት ፍጻሜውን የሚያገኘው በሔዋን አንድ ልጅ ነው፤ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ማርያም የእባቡን ራስ ትቀጠቅጣለች፤ ጥንታዊቷ ቤተክርስቲያን ምስክርነቷን እንደምትሰጠው በማርያም እና በእባቡ መካከል ጥንታዊቷ ቤተ-ክርስቲያን ምስክርነቷን እንደምትሰጠው በማርያም እና በእባቡ መካከል ትልቅ ጠላትነት ሰፍኗል፡፡ የእባቡን አናት የሚቀጠቅጠውን ኢየሱስን የወለደች ማርያም ናትና፡፡ ከሰይጣን ጋር የሚደረገው ትግል እና የእርሱን የማታለያ መንገዶች በሙሉ መግለጥ የተፈጸመው በማርያም አማካኝነት ነው፤ የዚህ ትንቢት ፍጻሜ በእውነትም ከሌሎቹ ትንቢቶች ለየት ያለ ነው፡፡

ያለ አዳም ኃጢአት በመጸነሷ እና ያለ ኃጢአት በመኖሯ እንኳን ማርያም ከሰይጣን ንክሻ አላመለጠችም፡፡ ልጇን በከብቶች በረት ውስጥ ትወልድ ዘንድ ግድ ሆነ፣ ከዚህ ግርግም የተሻለ መጠጊያ ሊተባበራት የፈለገ ማንም አልተገኘም፣ ልጇን ከሔሮድስ እጅ ከሞት አደጋ ለማዳን ረጅም እና አስቸጋሪ ጉዞ በግብጽ በረሃ አድርጋለች፡፡ ኢየሱስ እስራኤል እና መላው ዓለም የሚያድንበትን ወንጌል በሚሰብክበት ጊዜ በልጇ ላይ እያደገ የመጣውን ተቃውሞ አስተውላለች፡፡ በመስቀሉ ሥር ቆማ ልጇ እንደ ተራ ወንጀለኛ በግርፋቱ ቆሳስሎ ሊገለጽ በማይችል ስቃይ ለሞት ተላልፎ ሲሰጥ በዓይኗ አይታለች፡፡ እርሷም ያንን ስቃይ እና መሥዋዕትነት ተካፍላለች፡፡ ማርያም የእባቡን ራስ የቀጠቀጠችው አዳኝ በመውለዷ ብቻ ሳይሆን በመላው ሕይወት እና ባሳለፈችው መከራ የምትወደድ እናት እና የሰማዕታት እናት መሆን ጭምር ነው፡፡ በዚህ ሚናዋ በመንግሥተ ሰማይ የክብር አክሊል ደፍታ ለሁላችንም ምሳሌ ሆናለች፡፡

የሆነው ሆኖ የተቀደሰውን ቃል የጻፈው ይህንን (ዘፍ.3፡15) ሲናገር ቀጥታ ማርያምን በማሰብ አልነበረም፡፡ የቀደሙት የቤተ-ክርስቲያን አባቶች ብዙኀኑ ማለትም ቅዱስ ሳሲል (Bazil)፣ የኑሲሱ ቅ.ጎርጎርዮስ፣ የአሌክሳንደርያው ሲርል፣ ከምሥራቅ አባቶችም እንዲሁ ቅ.አምብሮዝዮስ፣ ቅዱስ አጉስጢኖስ፣ ቅ.ጀሮም፣ ታላቁ ቅ.ጎርጎርዮስ ይህ ቃል (ዘፍ.3፡15) ስለ አምላክ እናት የተነገረ ነው ብለው አልተረዱትም ነገር ግን ጥቂቶች ቃሉ ለአምላክ እናት የተነገረ አድርገው ይተረጉሙታል፡፡ ከእነዚህም መካከል፡- የቅዱስ ኤሬንዮስ፣ የቅዱስ ሲፕሪያን፣ የቅዱስ ሊዮ ታላቁ፣ እና ቅዱስ ኢፐፋንዮስ ይገኙበታል፡፡

ቤተ-ክርስቲያን ለአዳኙ እናት የምትሰጠው ከሁሉ የበለጠ ክብር እና ምሥጋና መሠረቱን ያገኘው ስለ መሲሑ እናት ምሳሌ ሆነው በቀረቡት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ግለሰቦች እና መገልገያዎች ላይ ሲሆን ይህም በሥርዓተ አምልኳችን ውስጥ እርሷን በሚመለከት በተለያዩ ሥፍራዎች ተገልጧል፡፡

የማርያም ተምሳሌት የነበሩ ግለሰቦች

ሔዋን፡- በአዳም እና በክርስቶስ መካከል ያለው ሁነኛ ግንኙነት ወይም ትሥሥር ግልጥ ነው፡፡ ከጥንት ጊዜ ጀምሮ እንዲሁ በማርያም እና በሔዋን መካከል አብሮ ሊሄዱ የሚችሉ ሁኔታዎች ተለይተዋል፡፡ ሔዋን እባቡን አደመጠች፤ ማርያም የመልአኩን የገብርኤል ቃል ተቀበለች፤ በዚህም ሔዋን የሠራችውን ኃጢአት እርሷ አልደገመችም፤ በትዕቢት ምክንያት ሔዋን በልጆችዋ ሁሉ ላይ ሞትን አመጣች፡፡ ማርያም ግን በትህትና እና ለእግዚአብሔር ፈቃድ በመታዘዝ በመዳናችን ውስጥ ሱታፌ አደረገች፡፡ ሞት በሔዋን ሕይወት በማርያም የሔዋን የመጀመሪያ ልጅ ኃጢአተኛ እና ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ የማርያም ልጅ ግን አዳኝና መድኃኒት ሆነ፡፡ ሔዋን የሰው ዘር ሁሉ እናተ ናት፤ ማርያም ደግሞ በኢየሱስ ክርስቶስ የዳኑት ሁሉ እናት ናት፡፡

ሜሪያም ወይም ማርያም የተባለችው የሙሴ እህት፡- እስራኤል ቀይ ባሕርን በደረቅ መሬት ከተሻገሩ በኋላ ለእግዚአብሔር የምስጎና መዝሙር ዘመረች፤ ይህ ተዓምር የእሰራኤልን ሕዝብ ከግብጽ ባርነት ነጻ ያወጣ ነበር፡፡ ማርያም ደግሞ የሰው ልጆች ከገቡበት የመንፈሳዊ ባርነት ቀንበር ነጻ ይወጡ ዘንድ እርሷ ‹‹ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች›› ስትል ዘመረች፡፡

ኢያኤል፡- ሲሣራ የተባለው ንጉሥ እስራኤልን ክፉኛ ሲጨቁን ኢያኤል እርሱን ገድላ እስራኤልን በነጻነት ካስጌጠች በኋላ ዲቦራ ስለ እርሷ ዘመረች ‹‹የዌሃዊው የሔቤር ሚስት ኢያኤል ከሴቶች ይልቅ የተባረከች ትሁን፤ በድንኳን ውስጥ ከሚኖሩ ቤቶች ይልቅ የተባረከች ትሁን››፡፡ ማርያምም አዳኙን ወልዳ ሰይጣንን በማሸነፏ ‹‹ከሴቶች ሁሉ የተባረከች›› ሆናለች፡፡

የዮፍታሔ ሴት ልጅ፡- እስራኤል በአሞናውያን ክፉኛ ጥቃት እና ብዝበዛ ከደረሰበት በኋላ የእስራኤል መስፍን የነበረው ዮፍታሔ መሃላ አደረገ፡- ‹‹በእውነት የአሞንን ልጆች በእጄ አሳልፈህ ብትሰጠኝ ከአሞን ልጆች ዘንድ በደህና በተመለስሁ ጊዜ ሊገናኘኝ ከቤቴ ደጅ የሚወጣው ማንኛውም (ነገር) ለእግዚአብሔር ይሆናል፤ ለሚቃጠል መሥዋዕትም አቀርበዋለሁ››፡፡ ዮፍታሔ ጦርነቱን አሸንፎ ወደ ቤቱ በደህና ተመለሰ፡፡ በመጀመሪያ እርሱን ለመገናኘት ከቤቱ የወጣችው የሚወዳት ብቸኛ ሴት ልጁ ሆነች፡፡ ዮፍታሔ ልቡ በኀዘን ቢሰበርም ምን ቀን ነው እንዲህ ያለውን ቃል የገባሁት ብሎ ቢቆጭም ቃልኪዳኑን ለመፈጸም ግዴታ እንዳለበት አመነ፡፡ ልጄ እንዲህ ትሆናለች የሚል ሐሳብ ጨርሶ አልነበረውም፡፡ ነገር ገን እርሷ ቆራጥ ሆና የአባቷ ፈቃድ በእርሷ ላይ ይሆን ዘንድ ፈቀደች፡፡ የጠየቀችው ብቸኛ ጥያቄ ስለ ድንግልናዋ ከወይዛዝርቱ ጋር ወደ ተራራራ ወጥታ የምታዝንበት እና የምታለቅስበት የሁለት ወር ጊዜ ብቻ ነበር፡፡ ይህ ጊዜ ባለቀበት ወቅት አባቷ ‹‹የገባውን ቃል ፈጸመ››፡፡

ዮፍታሔ ከዮርዳኖስ ወንዝ ማዶ ያሉት ሕዝቦች የጐሣ መሪ ሆኖ ከመሾሙ በፊት ክፉ ገዢ እና በውንብድና ይኖር የነበረ ነው፡፡ ነገር ግን ጽሑፉ በግልጽ አንዳሳየው እዚህ ላይ ለእግዚአብሔር ከነበረው ክብር የተነሣ አንዲቷን ልጁን እንደሰዋ ጥርጥር የለውም፡፡ ነገር ግን ከዚህ ባሻገር ልጅቱ ስለ ድንግልናዋ ለማልቀስ በመውጣትዋ እና ታሪኩም ‹‹እርሷም ወንድ አላወቀችም ነበር›› ብሎ መዝጋቱ አንዳንድ ሊቃውንት ዮፍታሔ ቀድሞውኑ ልጁን ለእግዚአብሔር ለዘለዓለሙ በድንግልና ትኖር ዘንድ ሰጥቷን ነበረ በማለት ይጠቅሳሉ፡፡ ይህ ክፍል ከዚህም በላይ ባለው ትርጓሜ በዚህች ሴት ምስል ውስጥ የማርያምን ዘለዓለማዊ ድንግልና ያሳያል፡፡

ዮዲት፡- ሆሎፎርኒስ ቤጤልዋን በጦር በከበበ ጊዜ ዮዲት የከተማዋ እና የእስራኤል አዳኝ ሆና ተነሣች፡፡ ለናቡከደነጾር ራሳቸውን ሊያስገዙ ከጫፍ የደረሱትን ወገኖቿን አበረታች፡፡ ወደ ጠላት የጦር ሰፈር ሄዳ የጦር አዛዥን አንገድ ትቀላ ዘንድ ምቹ ጊዜ ትጠብቅ ነበር፡፡ በዚያ ጊዜ እስራኤል በጠላቶቹ ላይ አደጋ ጥሎ አሽሽቷቸው ነበር፡፡ በተመሳሳይ ማርያም ዘንዶውን በማሸነፍ የሰው ልጆችን ከዘንዶው ኃይል አድናለች፡፡ ዮዲት ድል አድርጋ ስትመለስ ባለሥልጣናቱ እና ሕዝቡ ሁሉ የክብር ሰላምታ ሰጥተው ተቀበሏት፤ ኤልሳቤጥም ማርያምን ‹‹አንቺ ከሴቶች ሁሉ የተባረክሽ ነሽ›› በሚል የክብር ሰላምታ ተቀበለቻት፡፡ ዮዲትም ላደረገችው ነገር ሁሉ ተገቢ ምሥጋና የሚገባው ለእግዚአብሔር እንደሆነ ገለጠች፤ ማርያም በምሥጋና ጸሎትዋ ዝቅተኛይቱን፣ አገልጋይቱን ስለተመለከተ እና ታላቅ ነገር ስላደረገላት ለእግዚአብሔር የምሥጋና መዝሙር ትዘምራለች፡፡ ዮዲት ጥረቷን እና ልፋቷን ሁሉ በጸሎት እያጠናከረች ወደ እግዚአብሔር ትለምን ነበር፤ ማርያም ‹‹መንፈሳዊ ጽዋ›› ናት፡፡ ዮዲት በኖረችው መልካም ሕይወት በጊዜው ለነበሩት ሰዎች አብነት ሆናለች፤ ማርያም ደግሞ የጽድቅ መስታወት ናት፡፡ የማርያምን ቅድስት ጽንሰታ ስታከብር በምሽት ጸሎታችን ላይ ማርያምን ለዮዲት በተነገሩት የምሥጋና ቃላት እናወድሳታለን፡- ‹‹በእስራኤልም ላይ አንቺ እመቤት ነሽ፣ የእስራኤልም ክብራቸው ገናናነታቸው አንቺ ነሽ፡፡ የወገኖቻችንም መመኪያ አንቺ ነሽ››፡፡

አስቴር፡- በፐርሺያ ግዛት ሥር ይጨቆኑ ለነበሩት እና በሞት ይታደኑ ለነበሩት አይሁዳውያን ወገኖቿ መዳንን ያመጣች ሴት ናት፡፡ በተፈጥሮ ውበቷ የተነሣ አስቴር ለንግሥትነት ታጨች፤ በመንፈሳዊ ውበቷ ምክንያት ማርያም የመሲሑ እናት እና የሰማይ ንግሥት ሆነች፡፡ በልዩ ትዕዛዝ ካልሆነ በስተቀር ወደ ንጉሥ አዳራሽ ለመግባት ክልክል መሆኑ የማይሠራው ለአስቴር ብቻ ነበር፡፡ ሕዝቡ ሁሉ ይሄ ነጻነት አልነበራቸውም ነበር፡፡ ማርያም ደግሞ ሕዝቡን ሁሉ ከበከለው የአዳም ኃጢአት ነጻ ሆናለች፡፡ እጅግ በጣም ስለተወደደች አስቴር ወደ ንጉሡ ገባች፤ ማርያም ደግሞ በነፍሷ ንጽሕና የተነሣ በእግዚአብሔረ ፊት ታበራለች፡፡ አስቴር ይጠፋ ዘንድ ሞት ለተፈረደባቸው ሕዝቦች ማለደች፤ ማርያም ደግሞ ለሚሰቃዩ እና በጭቆና ቀንበር ሥር ላሉት ሁሉ ማለደች፤ ምልጃዋም ለዘለዓለም የጸና ነው፡፡

ከብሉይ ኪዳን የጥበብ መጽሐፍ ውስጥ የምናገኛቸው ሁለት አምሳል ሊዘነጉ አይገባም፡፡ በመዝሙር 45 የምናገኘው የጋበቻ በዓል በጥንት ጊዜ የመሲሑ እና በሐሳብ የተገነባችው እስራኤልን ፍቅር ያሳያል፤ ኢየሱስ ከቤተ-ክርስቲያን ጋር፡፡ በሁለተኛው የመዝሙሩ አንጓ ላይ የሙሽሪቷ ሚና ማርያምን የሚወክል በመሆኑ በእመቤታችን ድንግል ማርያም በዓላት ላይ በቅዳሴ እና በሰዓታት ውስጥ እንጠቀምበታለን፡፡ ማርያም በልጇ አጠገብ በወርቅ ያጌጠ ልብስ ለብሳ ንግሥት ሆና በቀኙ ቆማለች (ወትቀውም ንግሥት በየማነከ በአልባሰ ወርቅ ዑጽፍት ወሕብርት)፡፡ ጸጋ የሞላሽ ማርያም ሆይ ሰላምታ ለአንቺ! እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነው የሚለው የገብርኤል ሰላምታ መዝሙረኛው ሙሽሪቱን ካወደሰባቸው ቃላት ጋር ተመሳስሎ ሊቀመጥ ይችላል፡፡ ‹‹ ›› (መዝ.45፡12)

ምንጭ: በኢትዮጲያ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የሲታዊያን መነኮሳት ማኅበር ድዕረ ገጽ www.ethiocist.org ከሰፈረው በወጣት / ሳምሶን ደቦጭ - ከቅዱስ ዮሴፍ ቁምስና .. ማርያም በኢየሱስ ሐዋርያዊ ሥራ ዘመን በሚል አርእስት ከሰፍረው አስተምህሮ ያገኘነው ምሆኑን ከወዲሁ ለመግለጽ እንወዳለን።

 

 








All the contents on this site are copyrighted ©.