2017-08-16 11:04:00

የካቶሊክ እምነታችን ምንነት ከፍል 2 አስተምህሮ


የካቶሊክ እምነታችን ምንነት ከፍል 2 አስተምህሮ

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ታዳሚዎች የካቶሊክ እምነታችን ምንነት፣ በካቶሊክ እምነትና ባህል ውስጥ የምናደርገው ቤተሰባዊ ጉዞ በሚል አርእስት የኢትዮጲያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ጽህፈት ቤት ሐዋሪያዊ ሥራዎች ኮሚሽን ካሳተመው መጽሐፍ ላይ ያገኘውን አስተምህሮ በተከታታይ ወደ እናንተ በማቅረብ ላይ እንገኛለን። እነሆ በዛሬው እለት ዝግጅታችን ደግሞ “እኛ ካቶሊኮች በሮም ያለውን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳትን እንደ የጴጥሮስ ተተኪና የቤተክርስቲያናችን ራስ አድርገን ለምን እንደ ምንቀበል አጠር ባለ መልኩ ምክንያቶቹን እናቀርብላኃለን አብራችሁን ቆዩን።

ቅዱስ ጴጥሮስ የመጀመሪያው የሮም ጳጳስ ነው።

ቅዱስ ጴጥሮስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያኑን የመስረተበት ዓለት ነው። (ማቴ. 16:18)። ቅዱስ ጴጥሮስ የሐዋሪያት ሁሉ እንደራሴ እንደመሆኑ የመላይቱ ቤተክርስቲያን ራስ/የበላይ ነው። ኃላፊነቱ ክርስቶስ 3 ጊዜ ደጋግሞ እንዳስጠነቀቀው የክርስቶስን መንጋ መጠበቅ ነው (ዩሐንስ 21:15-17)። ቅዱስ ጴጥሮስ ስለ ክርስቶስ ሲል በንጉሥ ኔሮን ዘመን መንግሥት በሮም ከተማ በሰማዕትነት ሞቷል (በ64 ወይም 67 ዓ.ም.) የሞተውም እንደ ክርስትስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ የነበረ ሲሆን የተሰቀለው ግን ከክርስቶስ ስቅለት በተቃራኒው ጭንቅላቱን በማዘቅዘቅ ነበር፣ ይህም የሆነበት ምክንያት “እንደ ጌታዬ ቀጥ ብዬ ለመሰቀል የተገባው አይደለሁም” በማለቱ ነው። በሮም የሚገኘው ታላቁ “ባዚሊካ” (ቤተክርስቲያን) በዚሁ የመጀመሪያው የሮም ጳጳስ በነበረው በቅዱስ ጴጥሮስ  መቃብር ላይ የታነጸ ቤተክርስቲያን ነው።

የሮማው አቡን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በመባል የሚታወቁ ሲሆን ትርጓሜውም የመላዋ ቤተክርስቲያን አባት ማለት ነው። የመጀመሪያው የቅዱስ ጴጥሮስ ተከታይ ጳጳስ ሊኖስ ይባላሉ፣ ሁለተኛው ደግሞ አናክሊቱስ የሚባሉ እንደ ነበሩ ከታሪክ የምንረዳ ሲሆን በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ቄለመንጦስ የሚባሉ ነበሩ። በ180 ዓ.ም. ቅዱስ እረኔዎስ መናፍቃንን በመቃወም በጻፉት መጽሐፍ ውስጥ እስከ ራሳቸው ዘመን ድረስ ቤተክርስቲያንን የመሩዋትን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳትን መጥቀሳቸው ከታሪክ መዝገብ ለመረዳት የሚቻል ሲሆን ከዚያም ጊዜ አንስቶ እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ ያሉትን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮን ጨምሮ 266 ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን አስተዳድረዋታል፣ በዚህም ዓይነት ያልተቋረጠ መተካካት ቤተክርስቲያናችን እስከ ዛሬው እለት ዘልቃለች።

ሰለዚህም የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ከሮማው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ባላቸው አንድነት የተነሳ ከቅዱስ ጴጥሮስ ዓለት ጋር ያልንን ያልተቋረጠ ግንኙነት ይመሰክራሉ። ስለሆነም መላው የካቶሊክ ማኅበረሰብ የሮማን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በጣም ያውዳሉ ያከብራሉም።

ይህም የካቶሊክ እምነታችን ነው። የሮማው ጳጳስ የቅዱስ ጴጥሮስ ቀጥተኛ ተከታይ ናቸው፣ ስለዚህም “ፓፓ” ወይም የመላይቷ ቤተክርስቲያን አባት እያልን እንጠራቸዋለን። የሮም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳስ ቅዱስ ጴጥሮስ በክርስቶስ አፍ “ዓለት” በተባለው መሠረት የጴጥሮስ “ዓለት” ናቸው። ዋና ተግባራቸውም የቤተክርስቲያኑዋን አንድነት መጠበቅ እና የክርስቶስን መልእክት ከሐሰተኛ መልእክቶች መከላከል ነው።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አይሳሳቱ ብለን እናምናለን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አይሳሳቱም ማለት ግን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት እንደማንኛውም ሰው ኃጢኣት አይሠሩም ማለት ወይም የግል የሆነ ኃጢኣት የላቸውም ማለታችን አይደለም። እንደ ማንኛውም የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመን “በእኔ ክፍት በድዬኃለሁን ይቅር በለኝ” እያሉ የግል ኃጢኣታቸውን ይናዘዛሉ።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አይሳሳቱም ስንል በማንኛውም በሚናገሩትና በሚሰሩት ነግሮች ሁሉ አይሳሳቱም ማለታችንም አይደለም። እርሳቸው የማይሳሳቱት ከጴጥሮስ መንበር ላይ ሆነው በይፋ ታላቅ ሃይማኖታዊ አዋጆችን ሲያውጁ፣ ለምሳሌም “ማሪያም በሥጋ እና በነፍስ ወደ ሰማይ የፈለሰችበትን አንቀጸ-ሃይማኖት ወይም ዶግባ ሲያስተላልፉ አይሳሳቱም። እንዲህ ዓይነቱ ታላቅ ሃይማኖታዊ ድንጋጌዎችን “ዶግማ” ወይም አንቀጸ-ሃይማኖት እንላቸዋለን። ካቶሊኮች በሙሉ እንዲህ ዓይነቱን አስተምህሮ እውነት ነው ብለው ይቀበላሉ።

ምንጭ፣-የካቶሊክ እምነታችንን ምንነት፣ የኢትዮጲያ ካቶሊካዊት ጠቅላይ ጽህፈት ቤት ሐዋሪያዊ ሥራዎች ኮሚሽን 2007 .. ካሳተመው መጽሐፍ ከገጽ ግጽ 14, 15 የተወሰደ! የዚህን አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል በሚቀጥለው ረዕቡ እናቀርብላችኃለን።

 

 

 








All the contents on this site are copyrighted ©.