2017-08-16 10:59:00

የካቶሊክ እምነታችን ምንነት ከፍል 1 አስተምህሮ


የካቶሊክ እምነታችን ምንነት

  1. ለምን ቤተክርስቲያናችንን ካቶሊካዊት እንላታለን?

“ካቶሊክ” ማለት አጠቃላይ፣ ዓለም አቀፋዊ፣ ለሁሉም ሰውና ለሁሉም ዓለም የሚሆን ማለት ነው። ስለሆነም ቤተክርሲያናችን ሁሉንም ዓለም፣ ሁሉንም ሀገር፣ ሁሉንም ዘር፣ ሁሉንም ባህልና፣ ሁሉንም ትውልድ የምያቅፍ ስለሆነች ካቶሊክ ቤተክርስቲያን እንላታለን።

  1. ለምንድነው የካቶሊክ ቤተክርስቲያንን ሮማዊት የምንለው?

ቤተክርስቲያናችን ሮማዊት ነች፣ ምክንያቱም የቤተክርስቲያናችን የመጀመሪያ እረኛ ቅዱስ ጴጥሮስ በሮማ ስለኖረ፣ ስለሞተና በዚያው ስለተቀበረ ነው። ቅዱስ ጴጥሮስ የመጀመሪያው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ነው። አሁኑም ታዲያ የሮም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ልክ እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ የመላው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የበላይ እረኛ ነው። እርሱ የክርስቶስ ተከታዮችን በአንድ ላይ የሚጠብቅና የመላው ቤተክርስቲያን አንድነት ምሳሌ ነው። በሮም ያለው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳችን ክርስቶስ ቤተክርስቲያንን የመሠረተበት የቅዱስ ጴጥሮስ ዓለት ነው። ከዚህ እረኛዋ ጋር ሆና በምታደርገው ትግል ቤተክርስቲያን ምን ጊዜም የዓለም ኃያላት ሊያሸንፋት አትችሉም፣ ይህ ደግሞ ክርስቶስ ራሱ የገባላት ቃል ነው (ማቴ. 16,18)።

  1. ለምንድነው ቤተክርስቲያናችን አንዲት ናት እንላለን?

ቤተክርስቲያናችን አንዲት ናት የምንልበት በርካታ ምክንያቶች አሉን።

  1. ከሰው ዘር ሁሉ የተውጣጡ በመላው ዓለም የሚገኙ ካቶሊካዊያን ሁሉ እኩል የሚያከብሩትና የሚናገሩት አንድ ቅዱስ ቁርባን ያላት በመሆኑ የተነሳ ነው። በዚህ እጅግ ቅዱስ በሆነው ምስጢር አማካይነት ክርስቶስ በዚህ ማዕዱ ዙሪያ እንደ አንድ ቤተሰብ ስብስቦን በግልጽ የሚያስተሳስረን እስርሱ ነው።

  2. እኛ ካቶሊኮች በዓለም ዙሪያ ሁሉ ተመሳሳይ የአምልኮ ስርዓት ያለን ሲሆን ካቶሊኮች ሁሉ ከሮም ጳጳስ ጋር በጠበቀ እምነት ሲኖሩ ምን ጊዜም በማንኛውም የተሳሳተ አስተምህሮ ሳይነቃነቁ ከጴጥሮስ ዓለት ጋር በፍጹም አንድነት ይኖራሉ። (የካቶሊክ እምነታችንን ምንነት ግጽ 12) ራዲዮ ቫቲካን --የሰማ ላልሰማ ያሰማ!

4. የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ለምንድነው ሐዋሪያዊት ተብላ የምትጠራው?

የካቶሊክ ቤተክርስቲያንን “ሐዋሪያዊት” ነች ብለን የምንጠራበት ሁለት ዋነኛ ምክንያቶች አሉ፣

በመጀመሪያ ደረጃ ባልተቆራረጠ ሰንሰልት ከሐዋሪያት ዘመን ጀምሮ በጳጳሳትና በአቡናት መተካካት እስከ ዛሬ ድረስ የዘለቀች በመሆኗ ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ቤተክርስቲያናችን በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት እና በአቡናት አመራር ሥር ሆና የሐዋሪያትን ትምህርትና እምነት የምትኖር፣ የምታስተምርና የምትጠብቅ በመሆኗ የተነሳ ነው።

5. ለምንድነው የካቶሊክ ቤተክርስቲያናችንን ቅድስት ናት ብለን የምንጠራው?

ቤተክርስቲያን ማለት የእግዚኣብሔር ሕዝቦች የሚሰበሰቡበት ቦታ ማለት ነው፣ የጌታ የሆኑ ሁሉ ማለትም ነው። ቤተክርስቲያንን ቅድስት የሚያደርጋት ጌታ ራሱ ነው። እርሱ ሙሽራው ሙሽራይቱን እንደሚወድ ቤተክርስቲያንን ይወዳታልና። እኛ ካቶሊኮች ኃጢያተኛ መሆናችች እንናዘዛለን፣ ነገር ግን የክርስቶስ ፍቅር እንደ ሚቀድሰንና የቅድስት ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አካል እንደ ሚያደርገን እንናገራለን/እናውጃለን።

ምንጭ፣-የካቶሊክ እምነታችንን ምንነት፣ የኢትዮጲያ ካቶሊካዊት ጠቅላይ ጽህፈት ቤት ሐዋሪያዊ ሥራዎች ኮሚሽን በ2007 ዓ.ም. ካሳተመው መጽሐፍ ከገጽ ግጽ 11, 12 የተወሰደ!

 








All the contents on this site are copyrighted ©.