2017-08-16 09:36:00

የካቶሊካዊ ተሃድሶ እንቅስቃሴ አጀማመርና ዓላማ ክፍል 9 አስተምህሮ በክቡር አቶ ዩሐንስ መኮንን


የካቶሊካዊ ተሃድሶ እንቅስቃሴ ክፍል 9

እንደሚታወቀው ካቶሊካዊ ተሃድሶ እንቅስቃሴ፣ ምዕመናን በያሉበት ሥፍራ ሆነው በምስጢረ ጥምቀት ጸጋ አማካይነት የተቀበሉት የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚለው፣ ተዳፍኖ ወይም ተዳክሞ እንዳይቀር በጋራ ጸሎት፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ ኃይልን እንዲያገኙ የሚያስተባብርና የሚመክር እንቅስቃሴ ነው። ይህ በመሆኑ ከብዙ ዓመታት ወዲህ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ከጳጳሳት፣ ከካህናትና ከምዕመናን የተለያዩ መንፈሳዊና ቁሳዊ ድጋፍን ሲያገኝ ቆይቶአል፣ በማግኘትም ላይ ይገኛል። ባለፉት ዝግጅቶቻችን የሁለቱን የቀድሞ ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳት ማለትም የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ስድስተኛ እና የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ለካቶሊካዊ ተሃድሶ እንቅስቃሴ የላኩትን የማበረታቻ መልዕክቶችን ማቅረባችን ይታወሳል። በዛሬው ዝግጅታችን የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክት 16ኛ፣ ለእንቅስቃሴው አባላትና አስተባባሪዎች የላኩትን ሐዋርያዊ መልዕክት እናቀርባለን።

የዚህን አስተምህሮ ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

“በአዲስ ኪዳን መጽሐፍ ውስጥ ተጽፎ የምናገኘው፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እና ሐዋርያት ለጸሎት በተሰበሰቡበት ሥፍራ መንፈስ ቅዱስ በእያንዳንዳቸው ላይ የመውረዱ ሁኔታ በታሪክ መልክ በየጊዜው እየተነገረ የሚዘልቅ አንድ አጋጣሚ ብቻ ሳይሆን ያው አንዱ መንፈስ ቅዱስ እስከ ዛሬ ድረስ በቤተክርስቲያን ላይ እየወረደ መሆኑ እና ወደ ፊትም ሳያቋርጥ እንደሚወርድ መዘንጋት የለብንም። ይህ የቤተክርስቲያን ሕይወት የሆነው እና አምላካዊ ኃይል ያለው መንፈስ ቅዱስ በዘመናት ሁሉ እንዲሁም በዘመናችንም የሚያስደንቁ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን በግልጽ የምናየው ነው። በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ውስጥ የሚገኙ እንቅስቃሴዎችና ማኅበራት እየተበራከቱ መምጣት በእርግጥም መንፈስ ቅዱስ በቤተክርስቲያንና በኅብረተሰባችን ላይ መውረዱን እንዳላቋረጠ ያረጋግጥልናል።” በማለት እ.አ.አ ጥቅምት ወር 2008 ዓ.ም. በሮም ለተሰበሰቡት ካቶሊካዊ ተሃድሶ እንቅስቃሴ አባላት ሐዋርያዊ መልዕክታቸውን አስተላልፈው ነበር። ቀጥሎም እ.አ.አ ግንቦት ወር 2012 ዓ.ም. ባስተላለፉት ሐዋርያዊ መልዕክታቸው “ውድ በመንፈስ ቅዱስ የመታደስ እንቅስቃሴ አባላት በሙሉ፥ መላው ዓለም ከምን ጊዜም በላይ የእናንተን የጸሎት እገዛ ይፈልጋል። ምድራዊውን ሳይሆን ሰማያዊውን ጸጋ በመመኘት ወደ እግዚአብሔር ምስጋና የሚያቀርቡትን ሰዎች ጸሎት ይፈልጋል፤ ዘወትር ደስ ይበላችሁ፤ የተሃድሶ እንቅስቃሴአችሁ እንዲያድግና እንዲስፋፋ ወደ እመቤታችን ቅድስት ማርያም ዘንድ አደራ እላለሁ። ከእርሷ ጋር በጸሎት ተባበሩ። ከመንፈስ ቅዱስ በምታገኙት ብርሃን በመመራት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ለዓለም አብስሩ።” ማለታቸው ይታወሳል።

የክርስትና ሕይወታችን በውስጣችን ሕይወትን የሚያገኘው ከመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ነው። አዲስ ሕይወት ማለትም አብንና ከእርሱ የተላከውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ ማለት ነው። በዮሐ. ወንጌል ምዕ. 17 ቁጥር 3 ላይ እንዲህ የሚል ተጽፎአልና፥ “የዘለዓለም ሕይወትም፣ ብቻህን እውነተኛ አምላክ የሆንከውን አንተንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ ነው።” መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ ጋር አብሮአቸው ስለሚኖር ኢየሱስ ክርስቶስን የምናምን ሁላችን መንፈስ ቅዱስንም እናምናለን እናውቀዋለንም። ስለዚህ እንደ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክት 16ኛ ሐዋርያዊ መልዕክት መሠረት ሰላምና ፍቅር ለጎደለው፣ ርኅራሄና ኅብረት ለጎደለው ለዚህ ለምንኖርበት ዓለም የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ አጥብቀን በኅብረት መለመን ያስፈልጋል።

የተወደዳችሁ አድማጮቻችን ካቶሊካዊ ተሃድሶ እንቅስቃሴን በማስመልከት ያቀረብነውን ዝግጅት በዚህ እንፈጽማለን። ሳምንት በተመሳሳይ ርዕስ እስክንገናኝ ከመንፈስ ቅዱስ የሚገኝ ሰላምና ፍቅር እንዲሁም አንድነት ከሁላችን ጋር ይሁን። አሜን።

በአቶ ዮሐንስ መኰንን የተዘጋጀ

 








All the contents on this site are copyrighted ©.