2017-08-12 16:35:00

የነሐሴ 7/2009 ዓ.ም. እለተ ሰንበት ምንባባት እና አስተንትኖ በክቡር አባ መብራቱ ኃይለጊዮርጊስ


የነሐሴ 7/2009 ዓ.ም. እለተ ሰንበት ምንባባት እና አስተንትኖ በክቡር አባ መብራቱ ኃይለጊዮርጊስ

  1. ቆሮ 81-13   ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ

    ለጣዖት ስለ ተሠዋ ሥጋ ደግሞ ይህን እላለሁ፤ ሁላችንም ዕውቀት እንዳለን እናውቃለን ዕውቀት ያስታብያል፤ ፍቅር ግን ያንጻል። ዐውቃለሁ የሚል ሰው፣ ማወቅ የሚገባውን ያህል ገና አላወቀም። እግዚአብሔርን የሚወድ ሰው ግን በእግዚአብሔር ዘንድ የታወቀ ነው።

    እንግዲህ፣ ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ ስለ መብላት እንዲህ እላለሁ፤ በዚህ ዓለም ጣዖት ከንቱ እንደሆነና ከአንዱ ከእግዚአብሔር በስተቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ እናውቃለን። መቼም ብዙ አማልክትና ብዙ ጌቶች አሉ፤ በሰማይም ሆነ በምድር አምላክ ተብለው የሚጠሩ አማልክት ቢኖሩም፤ ለእኛ ግን ሁሉም ነገር ከእርሱ የሆነ፣ እኛም ለእርሱ የሆን አንድ አምላክ አብ አለን፤ ደግሞም ሁሉም ነገር በእርሱ አማካይነት የሆነ፣ እኛም በእርሱ አማካይነት የሆን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን።

    ነገር ግን ይህን የሚያውቁ ሁሉም አይደሉም፤ አንዳንድ ሰዎች እስከ አሁን ድረስ ጣዖትን ማምለክ ስለ ለመዱ፣ እንዲህ ያለውን ሥጋ ሲበሉ በርግጥ ለጣዖት እንደ ተሠዋ ያስባሉ፤ ኅሊናቸውም ደካማ ስለ ሆነ ይረክሳል። ነገር ግን ምግብ ወደ እግዚአብሔር አያቀርበንም፤ ባንበላ የሚጐድልብን ነገር የለም፤ ብንበላም የምናተርፈው ነገር አይኖርም።

    ነገር ግን ከነጻነታችሁ የተነሣ የምታደርጉት ለደካሞች ዕንቅፋት እንዳይሆን ተጠንቀቁ። አንተ ይህን የመሰለ ዕውቀት ኖሮህ፣ ደካማ ኅሊና ያለው ሰው በቤተ ጣዖት ስትበላ ቢያይህ፣ ለጣዖት የተሠዋውን ምግብ ለመብላት አይደፋፈርምን? ስለዚህ ክርስቶስ የሞተለት ይህ ደካማ ወንድም በአንተ ዕውቀት ምክንያት ጠፋ ማለት ነው። በዚህ መንገድ ወንድሞቻችሁን በመበደልና ደካማ ኅሊናቸውን በማቍሰል፣ ክርስቶስን ትበድላላችሁ። ስለዚህ እኔ የምበላው ነገር ወንድሜን የሚያሰናክለው ከሆነ፣ ወንድሜን ላለማሰናከል ስል ከቶ ሥጋ አልበላም።

     

    ለእግዚአብሔር መኖር

    እንግዲህ ክርስቶስ በሥጋው መከራን ስለ ተቀበለ እናንተም በዚሁ ዐላማ ታጥቃችሁ ተነሡ፤ ምክንያቱም በሥጋው መከራን የሚቀበል ሰው ኀጢአትን ትቶአል። ከዚህም የተነሣ ከእንግዲህ በሚቀረው ምድራዊ ሕይወት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ እንደ ሥጋ ምኞት አይኖርም። አሕዛብ ፈቅደው እንደሚያደርጉት በመዳራት፣ በሥጋዊ ምኞት፣ በስካር፣ በጭፈራ፣ ያለ ልክ በመጠጣት፣ በአስጸያፊ የጣዖት አምልኮ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃል። ይህን በመሰለ ብኩን ሕይወት ከእነርሱ ጋር ስለማትሮጡ እንግዳ ሆኖባቸው በመደነቅ ይሰድቧችኋል። ነገር ግን በሕያዋንና በሙታን ላይ ሊፈርድ ለተዘጋጀው መልስ ይሰጣሉ።

    1. 1 ጴጥሮስ  4:1-5

 ወንጌል 12:38-50ተአምራት ለማየት የቀረበ ጥያቄ

 

ከዚያም አንዳንድ የአይሁድ ሃይማኖት መምህራንና ፈሪሳውያን፣ “መምህር ሆይ፤ ከአንተ ታምራዊ ምልክት ማየት እንፈልጋለን” አሉት። እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይጠይቃል፤ ነገር ግን ከነቢዩ ዮናስ ምልክት በስተቀር ሌላ ምልክት አይሰጠውም። ዮናስ በዓሣ ዐንበሪ ሆድ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ቈየ፣ እንዲሁ የሰው ልጅ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት በምድር ሆድ ውስጥ ይቈያል። የነነዌ ሰዎች በፍርድ ዕለት ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ እነርሱ በዮናስ ስብከት ንስሓ ገብተዋልና። እነሆ፤ ከዮናስ የሚበልጥ እዚህ አለ። በፍርድ ዕለት የደቡብ ንግሥት ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥታ ትፈርድበታለች፤ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳርቻ መጥታለችና። እነሆ፤ ከሰሎሞን የሚበልጥ እዚህ አለ።

“ርኩስ መንፈስ ከሰው ከወጣ በኋላ ዕረፍት ለማግኘት ውሃ በሌለበት ደረቅ ቦታ ይንከራተታል፤ የሚሻውን ዕረፍት ግን አያገኝም። ከዚያም፣ ‘ወደ ነበርሁበት ቤት ተመልሼ ልሂድ’ ይላል፤ ሲመለስም ቤቱ ባዶ ሆኖ፣ ጸድቶና ተዘጋጅቶ ያገኘዋል። ከዚያም ይሄድና ከራሱ የባሱ ሌሎች ሰባት ክፉ መናፍስት ይዞ ይመጣል፤ እነርሱም ሰውየው ውስጥ ገብተው ይኖራሉ። የዚያም ሰው የኋለኛው ሁኔታ ከፊተኛው የከፋ ይሆናል። በዚህ ክፉ ትውልድም ላይ እንዲሁ ይሆንበታል።”

ኢየሱስ ለሕዝቡ ሲናገር ሳለ፣ እናቱና ወንድሞቹ ሊያነጋግሩት ፈልገው በውጭ ቆመው ነበር። አንድ ሰውም፣ “እነሆ፣ እናትህና ወንድሞችህ ሊያነጋግሩህ ፈልገው በውጭ ቆመዋል” አለው። ኢየሱስም፣ “እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው?” ሲል መለሰለት። በእጁም ወደ ደቀ መዛሙርቱ እያመለከተ እንዲህ አለ፤ “እናቴና ወንድሞቼ እነዚህ ናቸው፤በሰማይ ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፣ ወንድሜ፣ እኅቴና እናቴም ነው።”

 

አስተንትኖ

የተወደዳችሁ የእግዚኣብሔር ቤተሰቦች እና በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!

 “እግዚአብሔር ለቍጣ የዘገየ፣ ፍቅሩ የበዛ፣ ኀጢአትንና ዐመፃን ይቅር የሚል፣ በደለኛውን ግን ሳይቀጣ የማይተው” አምላክ ነው ይለናል ዘኁልቍ 14:18። በሰላም ጠብቆን፣ መተላለፋችንን በትዕግስት አሳልፎ ለሠራናቸው ኃጢያቶች ሁሉ ይቅርታን እንጠይቅ ዘንድ ጊዜ ሰጥቶን፣ ተስፋ ስንቆርጥ ተስፋ ሆኖን፣ በምንፈራበትና  በምንሸበርባቸው ወቅቶች  ሁሉ አይዞህ/ አትፍራ/ በማለት ብርታትን ሰጥቶን ለዛሬው ቀን ያደረሰን እግዚኣብሔር ቅዱስ አባታችን  ስሙ የተመሰገነ ይሁን።እንደ ሚታወቀው እንደ አገራችን ሥርዓተ አምልኮና መንፈሳዊ ልማድ በእመቤታችን በኩል እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ስለገለጠው ተስፋና በእርስዋም ጸጋ መሞላት ላደረገልን ቸርነት በተለየ ሁኔታ በየዓመቱ ለ16 ቀናት የሚዘለቀወን ጾምና ምህለላ የምናደርግበት የፍልሰታ ዘመን ላይ እንገኛለን። እግዚአብሔር አብ በእርሱ ለኖሩት ሁሉ ሊያደርግላቸው ቃል የገባውን እውነታ እርሱ በፈቀደው መልኩ በእመቤታችን የተገበረበትን ጸጋ እንወድሳለን፤ ለእኛም ይሆንልን ዘንድ “ማርያም ሆይ! ቸር፣ የሰው ልጆች ሁሉ አዳኝ ወደ ሆነው ልጅሽ ለምኝልን/ በማለት የእናትነት አማላጅነቷን በምንማጽንበት በዚህ የፍልሰታ ወቅት በጾም፣ በጸሎትና በምዕለላ እግዚኣብሔርን የምንማጸንበት እና መልካም ፍሬ የምናፈራበት ወቅት ሊሆን የገባል።

የዚህን አስተንትኖ ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

በዛሬው እለተ ሰንበት ቤተክርስቲያናችን እንድናስተነትን፣ በሕይወታችን ውስጥ በማስረጽ ጸጋ እና በረከት እንድናገኝ  ከእህት  ወንድሞቻችን ጋር በሰላም እንድንኖር  ይረዳን ዘንድ የሚከተሉትን ምንባባት ሰጥታናለች።

በዛሬው የመጀመሪያ ምንባብ ላይ ቅዱስ ሐዋሪያ ጳውሎስ ለጣዖት የተሠዋ ሥጋን በተመለከተ ሲናገር እንሰማለን። በዚያን ወቅት አረማዊያን ለጣዖቶቻቸው ሥጋን በመስዋዕትነት ካቀረቡ ቡኃላ የተረፈውን ሥጋ የጣዖቱ ካህናት፣ መስዋዕት አቅራቢውና ከእርሱ ጋር የነበሩ ሰዎች ይበሉታል ወይም ደግሞ ወደ ገበያ አውጥተው ይሸጡት ስለነበረ አንድ አንድ ክርስቲያኖች ደግሞ በዚህ መልክ የቀረበውን ሥጋ ገዝተው መብላት ጣዖትን እንደ ማምለክና በክርስቶስ ላይ ካላቸው እምነት እንደ አፈገፈጉ ይቆጠር ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ለሌሎች ግን ያንን ሥጋ ገዝቶ መመገብ ምንም ችግር አያስከትልም የሚል ክርክር አስነስተው ስለ ነበረ ጳውሎስ ለዚሁ ክርክር መልስ ለመስጠት ፈልጎ የጻፈው መልእክት ነው።

ሐዋሪያው ጳውሎስ ለጣዖት የተሰዋ ሥጋ መብላት ምንም ጉዳት እንደማያመጣበት ቢያውቅም ደካማ የሆነ ወንድሙን የሚያሰናክል ነገር መስሎት ከታየው ግን ለዘለዓለም ሥጋ ሳይበላ መቆየት እንደ ሚመርጥ ይናገራል። ለጳውሎስ ዋናው ቁምነገር የነበረው ጉዳይ የመብላት እና ያለመብላት ጉዳይ ሳይሆን “ምግብ ወደ እግዚኣብሔር አያቀርበንም፣ ባንበላ የሚጎልብን ነገር የለም፣ ብንበላም የምናተርፈው ነገር የለም ይለናል። ለጳውሎስ በጣም አስፈላጊ የነበረው ቁምነገር ግን በምንም ዓይነት ሁኔታ የምናደርጋቸው ማንኛውም ዓይነት ድርጊቶች ለደካሞች ዕንቅፋት ሊሆን አይገባ የሚለው ነው። ስለዚህም ለወንድሞቻችን እና ለእህቶቻችን ዕንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ማንኛውንም ዓይነት ተግባሮቻችንን ማቆም ይኖርብናል ማለት ነው።

በወንጌል ውስጥ ኢየሱስ ይህንን በተመለከተ “ሰውን የሚያረክሰው ከአፉ የሚወጣው እንጂ ወደ አፉ የሚገባው አይደለም” (ማቴዎስ 15:11) በማለት ይናገራል። ነገር ግን ለማንም ሰው መሰናክል መሆን እንደ ማይኖርብን በሚገልጸው የኢየሱስ መልእክት ላይ “ይህ ሰው ከእነዚህ ከታናናሾች አንዱን ከሚያሰናክል፣ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣል ይሻለው ነበር” (ሉቃስ 17:2) በማለት በምንም ዓይነት መልኩ ለሌሎች እንቅፋት መሆን እንደ ማይገባን ያስተምረናል።

በሁለተኛ ደረጃ በተነበበው ምንባብ ላይ ሐዋሪያው ጴጥሮስ “ከእንግዲህ በሚቀረው ምድራዊ ሕይወት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ እንደ ሥጋ ምኞት አይኖርም። አሕዛብ ፈቅደው እንደሚያደርጉት በመዳራት፣ በሥጋዊ ምኞት፣ በስካር፣ በጭፈራ፣ ያለ ልክ በመጠጣት፣ በአስጸያፊ የጣዖት አምልኮ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃል” ይህ እውነታ እኛ ዛሬ ባለንበት ዘመን በከፍተኝ ሁኔታ የሚታይ ተግባር ነው። ሰለዚህም እነዚህን ከንቱ የሆኑ ነገሮች በመተው፣ በተለይም በዛሬው ወቅት ጣዖታችን እየሆኑ የመጡትን ከልክ በላይ ገንዘብ እና ንብረት የማካበት ፍላጎቶቻችን ከእግዚኣብሔር መንገድ የሚያርቁን፣ እዚሁ ጊዜያዊ በሆነ ዓለም ጥለነው የምንሄደው ነገር በመሆኑ የተነሳ ዘላቂውን የእግዚኣብሔር ምሕረ በመሻት ተመጣጣኝ የሆነ የአኑኗር ዘይቤን በመከተል ካለን ለድኾች በማካፈል መኖር እንደ ሚገባን ሐዋሪያው ጴጥሮስ ዛሬ ያሳስበናል። በተጨማሪም ምድራዊ የሆነ ደስታን ብቻ ሊያጎናጽፉን የሚችሉ ተግባራትን በተለይም ደግሞ ከልክ በላይ የሆኑ ነገሮችን በቅድሚያ ለጤናችን ጥሩ ባለመሆናቸው የተነሳ፣ በማስከተል ደግሞ ከሰዎች እና ከራሳችን ጋር ብሎም ከእግዚኣብሔር ጋር ሊያጋጩን የሚችሉ የኃጢኣያት ምክንያቶች እንዳይሆኑብን ሁሉንም ነገሮች በመጠን ማድረግ ይገባናል ማለት ነው።    

የዛሬው ቅዱስ ወንጌል ውስጥ አንዳንድ የአይሁድ ሃይማኖት መምህራንና ፈሪሳውያን፣ “መምህር ሆይ፤ ከአንተ ተአምራዊ ምልክት ማየት እንፈልጋለን” ብለው ኢየሱስን በጠየቁት ጊዜ እርሱ ግን መልሶ  “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይጠይቃል፤ ነገር ግን ከነቢዩ ዮናስ ምልክት በስተቀር ሌላ ምልክት አይሰጠውም” ይለናል። ፈሪሳዊያኑ ይህንን ጥያቄ ያነሱበት ምክንያት ኢየሱስ በእውነት መሲህ መሆኑንና አለመሆኑን ለመረጋገጥ ከነበራቸው ፍላጎት የመነጨ ሲሆን እርሱም በሰማይ ላይ ጉልህ በሆነ መልኩ የሚታይ ምልክት ለማየት ፈልገው ነበር። ነገር ግን ኢየሱስ ጥያቄአቸውን የመለሰው እነርሱ በፈለጉበት መንገድ ሳይሆን በታሪካቸው ውስጥ ስለተከሰተው አንድ ምልክት በመጥቀስ ነበር። ይህም “ይህ አመንዝራ ትውልድ” (ማቴ. 12:39) የሚለው ነው።

በዚህ በዛሬው ወንጌል ውስጥ የተጠቀሰው አመንዝራ የሚልው ቃል የሚያመልክተው መንፈሳዊ ባል ለሆነው እግዚኣብሔር የእርሱ ትውልድ ወይም ሕዝቦች ታማኝ ሆነው አለመገኘታቸውን ነው እንጂ በሥጋ ማምንዘርን አያመለክትም። ዛሬ ይህንን የቅዱስ ወንጌል ቃል በጥልቀት መመልከት እና ሕይወታችንን መመርመር ይኖርብናል። ዛሬም ቢሆን ኢየሱስ ጌታ መሆኑን በተለዩ ምክንያቶች ልንጠራጠር እንችል ይሆናል። ምናልባት ታመን በአልጋ ላይ በምንሆንበት ሰዓት በቶሎ ለመዳን ካለን ጉጉት የተነሳ እግዚኣብሔር ቅጽበታዊ በሆነ መልኩ እንዲያድነን በመሻት ምልክት እንፈልግ ይሆናል። ምናልባት ልባችን በዚህ ዓለም ሃብትና ምቾት አብጦ በመደንደኑ የተነሳ እግዚኣብሔር የለም አያስፈገኝም፣ በሃብቴ እና በራሴ ጉልበት መኖር እፈልጋለሁ በማለት በምድራዊ ነገሮች በመመካት እርሱ መኖሩን እና አለመኖሩን ለማመን ተጨባጭ ምልክት እንፈልግ ይሆናል።  በእነዚህ እነዚህን በመሳሰሉ ምክንያቶች ከእግዚኣብሔር በመራቅ ምድራዊ የሆኑ ነገሮችን በመመካት በምንኖርበት ወቅት በእግዚኣብሔር ላይ ላይ እናመነዝራለን ማለት ነው።

በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ እግዚኣብሔር ብዙ ምልክቶችን እንዳሳየ ተጠቅሶ እናገኛለን። ለምሳሌም ሙሴ እግዚኣብሔር ከሁሉም አማልክት በላይ መሆኑን ለፈርዖን ለማሳየት በፈለገበት ወቅት እግዚኣብሔር ታላላቅ የሆኑ ተአምራትን ማድረጉን እንውቃለን። ሙሴ በዚሁ ተግባሩ እግዚኣብሔር ከሁሉም በላይ እንደ ሆነ፣ በዚህ ምድር ካሉ ነገሮች ሁሉ የሚስተካከለው ወይም የሚወዳደረው እንደሌለ ለፈርዖን አሳይቱዋል። ይህንምም ያደርገው እጁን በባሕር ላይ በዘረጋበት ወቅት ባሕሩ ለሁለት ተከፈለ እግዚኣብሔር የሁሉም የበላይ መሆኑን አሳየ። በዚሁ መልኩ በእግዚኣብሔር ኃይል እየተመራ ሕዝቡን ከባርነት ነጻ አወጣ።

በአንጻሩ ግን ኢየሱስ ወደ ዚህ ምድር የመጣው እስራኤላዊያን እንዳሰቡት ከሮማዊያን ቅኝ ግዛት ሊያወጣቸው ፈልጎ ሳይሆን የመጣው ነገር ግን የዚህ ዓለም የሞት ምንጭ የሆነውን ኃጢያትን ድል ለማድረግና  እያንዳንዱ ሰው ንስሐ በመግባት መንፈሳዊ ለውጥ በማምጣት በእምነት እና በእርሱ ቃል በመመመራት ኃጢያትን ያሸንፍ ዘንድ ሊያበቃቸው ነው የመጣው። እርሱ በመንፈስ ቅዱስ ከቅድስት ድንግል ማሪያ መወለዱ፣ በሽተኞችን ማዳኑ ከተቸገሩት ጋር አብሮ መቸገሩ በራሱ ከእግዚኣብሔር ዘንድ የመጣ መሆኑን ያረጋግጣሉ። ነገር ግን እርሱ ያሳየቸው የነበሩ ምልክቶች ዓለም እንደ ሚፈልገው ዓይነት ታላቅነቱን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያሳዩ ምልክቶችን ሳይሆን ያሳይ የነበረው ነገር ግን በታላቅ ትህትናና ንጹህ በሆነ መልኩ ፍቅሩን አሳይቶናል። በፍቅር ታላላቅ ተግባራትን በመፈጸም እግዚኣቤሔር ከእርሱ ጋር እና እርሱ ከእግዚኣብሔር ጋር መሆኑን አሳይቱዋል ዛሬም ቢሆን እያሳየ ይገኛል።

በተጨማሪም ኢየሱስ አባቱ እና እናቱ እንዲሁም ወንድሞቹ እና እህቶቹ ሊሆኑ የሚችሉ ሰዎች የእርሱን ቃል ሰምተው በተግባር የሚያውሉ ሰውች ብቻ መሆናቸውን በመግለጹ ታላቅ መሆኑ አሳይቱዋል። ወገንተኛነቱን የገለጸው የእርሱን ቃል ሰምተው በተግባር የሚያውሉ ሰዎች መሆናቸውንም በተግባር አሳይቶናል።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!

በዛሬው ሰንበት ቀን እግዚሐብሔር በእየለቱ በሕይወታችን ውስጥ እያከናወነ የሚገኘውን ምልክቶች በመረዳት፣ በዚህ ዓለም በምንኖርበት ወቅት በመጠን እንድንኖር እንዲረዳን፣ ለወንድሞቻችን እና ለእህቶቻችን እንቅፋት ሳንሆን በመልካም አብነት እንድንመራቸው እና ወደ እግዚኣብሔር ቤት እንድናቀርባቸው የሚያስችለንን መንፈሳዊ ለውጥ እንድናመጣ በጸጋው እንዲረዳን፣ የእርሱን ቃል ሰምተን በተግባር ላይ በማዋል ፍሬያማ የሆነ ሕይወት እንድንኖር ይረዳን ዘንድ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማሪያም አማላጅነት ልንማጽነው ይገባል።

 የሰማነውን በልቦናችን ያሳድርልን። አሜን! 

በአባ መብራቱ ኃይለጊዮርጊስ የተዘጋጀ። 

 








All the contents on this site are copyrighted ©.