2017-07-31 09:48:00

የሐምሌ 30/2009 ዓ.ም. እለተ ሰንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ በክቡር አባ መብራቱ ኃይለጊዮርጊስ።


የሐምሌ 23/2009 ዓ.ም. እለተ ሰንበት የወንጌል አስተንትኖ

የተወደዳችህ የእግዚኣብሔር ቤተሰቦች እና በጎ ፈቃድ ያላችሁ!

ዳዊት በመዝሙሩ “እግዚአብሔር ቸር እንደ ሆነ ቅመሱ እዩም፤ በእርሱ የሚታመን ሰው ምስጉን ነው” ይላል። እንደ የተግባራችን ሳይሆን በምሕረቱና በቸርነቱ የሚጎበኘን እግዚኣብሔር አምላክችን ቅዱስ ስሙ የተመሰገነ ይሁን። በዛሬው እለተ ሰንበት ለስተንትኖ ይሆነን ዘንድ ቤተክርስቲያናችን የሰጠችን የእግዚኣብሔር ቃል በቀዳሚነት የተወሰደው ሐዋሪያው ጳውሎስ ወደ ቆሮንጦስ ሰዎች ከጻፈው ከሁለተኛ መልእክቱ 9:1-15 ላይ ያለው ሲሆን ይህም ለክርስቲያኖች ስለተደረገው መዋጮ የሚያመልክትና ክርስቲያኖች ለቤተክርስቲያን ወይም ሌሎች በችግር ላይ የሚገኙ ክርስቲያን ወንድሞቻቸውን በግድ ሳይሆን በፈቃደኝነት ሊረዱ ይገባል የሚለውን የሐዋሪያው ጳውሎስን መልእክት የያዘ ነው።

የእዚህን ዜና ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

በዛሬው እለተ ሰንበት በሁለተኛነት ለአስተንትኖ የተሰጠን የእግዚኣብሔር ቃል የተወስደው 1 ጴጥሮስ 3:15-22 ያለው ሲሆን በዚህም መልእክት “ እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ ስለ ተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ!” በማለት ሐዋሪያው ጴጥሮስ ዛሬ ለእኛ ጥሪ ያቀርባል።

የዛሬው ቅዱስ ወንጌል ከማቴዎስ ወንጌል 24፡36-51 የተወሰደ ሲሆን ይህም “ጌታ የሚመጣበት ጊዜ ስለማይታወቅ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ” በሚል ጭብጥ ዙሪያ የሚያጠነጥን ሲሆን ክርስቲያኖች ሁሉ እግዚኣብሔር መቼ እና እንዴት እንደሚጠራን ስለማንውቅ ተዘጋጅተን ምኖር ይኖርብናል በማለት ለእኛ ማሳሰብያ ያቀርባል።

ነቅቶ መጠበቅ

ባለንበት ዘመን የክርስቶስን በቶሎ የመምጣትን ወይም የዓለም ፍፃሜ እንደደረሰ የሚናገሩ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ በተለይም የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 24 ላይ ያለውን መሰረት በማድረግ፣ የተጠቀሱትን ምልክቶች በዋቢነት በመውሰድ ለምሳሌ የጥፋት ውኃ፣ ሁለት ሴቶች በወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዲቱ ትወሰዳለች አንዲቱም ትቀራለች የሚሉትን እና የመሳሰሉትን ምልክቶች በመጥቀስ ሌሎችን ሲያስቱ ይታያል፡፡

እንደ ክርስቲያን ልናስተውላቸው የሚገቡን ነገሮች አሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ የሚከተሰቱት ሰው ሰራሽ አደጋዎች ከሰው ልጅ የአእምሮ እድገት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ነገሮች ሲሆኑ የተፈጥሮ አደጋዎች ለምሳሌም የመሬት መንቀጥቀጥ የመሳሰሉ አደጋዎች ግን ድሮም የነበሩ፣ ዛሬም ያሉ፣ ወደፊትም የሚኖሩ ናቸው፡፡ በብሉይ ኪዳን በተለይም በኖኅ ዘመን የሰው ክፋት በጣም ታላቅ እንደነበረና እግዚአብሔርም በዚያ እንዳዘነ ስለዚህ ሰዎችና ፍጥረታት ሁሉ በምድር ላይ ታላቅ ጐርፍ በመላክ ለማጥፋት ወሰነ፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው እሱም ኖኅ ብቻ ጻድቅ ሆኖ ተገኘ፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ ተወዳጅ ስለነበር እግዚአብሔር ኖኅን አንድ ትልቅ መርከብ ስራ በማለት እርሱንና ቤተሰቡን በመርከብ ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ አዳነ፡፡ የቀሩት ሰዎች በዓለም ይደሰቱ ነበር፣ የእግዚአብሔርን ፍርድ አልፈሩም፡፡ ኖኅም ትልቁን መርከብ በመስራቱ ሳቁበት ተሳለቁበት፡፡ ጐርፍ ይመጣል የሚል እምነት ስላልነበራቸው ጨርሰው አልተዘጋጁም ነበርና ሁሉም ጠፉ ይለናል በኦሪት ዘፍጥረት 7፡6-24፡፡ እያንዳንዳችን ነቅተን የምንጠብቀው እንዴት ነው? ምን ዓይነት ተግባራትን በመሥራት ነው ንቅተን መጠበቅ የሚኖርብን? ክርስቶስ በድንገት በሚመጣበት ወቅት ምን ዓይነት ተግባራትን እየፈጸምን ሊያገኘን ይገባል? የሚሉትን ጥያቀዎች ዛሬ ማንሳት ይኖርብናል። እንደ ክርስቶስ ተከታዮች ልንተገብራቸው የሚገቡን ክርስቲያናዊ ተግባሮች አሉ እነርሱም በእየ እለቱ ሥጋዊ የምሕረት ተግባራትን ማከናውን ይጠበቅብናል ማለት ነው።

እነዚህ ሥጋዊ/አካላዊ የምሕረት ተግባራት ጠንቅቀን የምናውቃቸው ነገር ግን አብዝተን የምንዘነጋቸው መሰረታቸውን በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 25: 31 ጀምሮ በጠጠቀሰው የኢየሱስ አስተምህሮ ላይ የተመረኮዘ ሲሆን ይህም በዓለም መጨረሻ የሚሆነውን የፍርድ ሂደት የሚያመልክትና “ኢየሱስ በመላእክቱ ታጅቦ በፍርድ ወንበር ላይ በመቀመጥ፣ እረኛው በጎችን ከፍዬሎች  እንደሚለይ እርሱም ሕዝቦችን ይለያል፣ በጎቹን በቀኙ ፍዬሎቹን ደግሞ በግራው ያቆማቸዋል” እንደ ሚለው በመጨረሻው ቀን በኢየሱስ ፊት በምንቆምበት ወቅት ለሚያቀርብልን ጥያቄዎች በድፍረት በቂ የሆነ ምላሽ መስጠት እንድንችል እና ከፍየሎቹ ተርታ ሳይሆን ገበጎቹ ጎራ መሰለፍ እድንችል የሚያግዙን ተግባራትን መፈጸም ይገባል። እነዚህ ሥጋዊ/አካላዊ የምሕረት ተግባራት እነማን ናቸው?

  1. የተራበን ማብላት፡- ብዙዎቻችን በልተን ጠግበን ስናድር ምን ያህል ሌሎችን እናስባለን፣ ሐዋርያው ያዕቆብ በመልዕክቱ “ወንድሞቼ ሆይ አንድ ሰው እምነት አለኝ ቢል ሥራ ግን ባይኖረው ምን ይጠቅመዋል? አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት የሚለብሱት ልብስም ሆነ የሚመገቡት አጥተው ከእናንተ መካከል አንዱ በሰላም ሂዱ፣ አይብረዳችሁ፣ ጥገቡ” ቢላችሁ ለሰውነታችው ግን የሚያስፈልጋቸውን ባየሰጣቸው ምን የምንጠማቸዋል እንዲሁም “በስራ የሌለው እምነት በራሱ የሞተ ነው” ያዕቆብ 2፡14-17 ዛሬ የምንጠራቸው ነገ የሚጠሩንን እንጂ ነገ የማይጠሩንን ዛሬ አንጠራቸውም ይህ ሊሆን አይገባም፡፡ ዛሬ ድሆችን ብንጠራ ነገ እግዚአብሔር በመንግስቱ የጠራናል፡
  2. የተጠማን ማጠጣት፡- የተጠማን ማጠጣት ከፍተኛ ዋጋ እንዳለው ጌታችን መድኃኒታችንን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል ውስጥ ያስተምረናል፡፡ “ማንም ከነዚህ ከታናናሾች አንዱ ቀዝቃዛ ውሃ ብቻ በደቀመዝሙር ስም የሚያጠጣ እውነት እላችኋለሁ ዋጋውን አያጣም” ማቴ. 1ዐ፡42።
  3. እንግዳን መቀበል፡- እንግዳን ያልተቀበለ በእንግዳነት በእግዚአብሔር ዘንድ ለመሄድ እንዴት ይደፍራል ታናናሾችንም ታላላቆችንም በእንግድነት በክርስቶስ ስም መቀበል ይገባል፡፡ በብሉይ ኪዳን እንግዶችን በቀበል የተመሰገኑ አሉ ለምሳሌ አብርሃም /በኦሪት ዘፍጥረት 18፡1-15/ ሎጥ /ኦሪት ዘፍጥረት 19፡1-3/ በክርስትና ሕይወታችን እንግዶችና ምፃተኞች እንግዶችን በመቀበል ታላቅ ዋጋ እናገኛለን፡፡ ሐቅ ጳውሎስ “እንግዶችን ለመቀበል ትጉ” ሮሜ 12፡13 በማለት ይመክረናል፡፡ እንግዶቻችንን ለመቀበል የልባችንን ይሁን የቤታችንን በሮች ወለል አድርገን እንክፈት፡፡
  4. የታረዘን ማልበስ፡- መታረዝ በልብስ መራቆት ነው ሰው በልብሱ ከተራቆተ ሰውነቱ በብርድ ቁር በፀሐይ ሐሩር ስለሚጠቃ ጤናው የታወከ ነው የሚሆነው፡፡ እኛ ግን ዮሐንስ ሲሰብክ “ሁለት ልብስ ያለው ለሌላው ያካፍል” /ሉቃስ 3፡11/ በማለት የምክረናል፡፡ አይደለም ሁለት ከሃያ አንድ ማካፈል ይከብደናል፡፡ ነገር ግን ወደዚህ ዓለም የመጣነው እራቁታችን እና የምንሄደውም ራቁታችንን መሆኑን እናስብ፡፡ እኛ ስላለን የታረዙትን ድሆች ምድራዊ ልብስ ስናለብስ የሁሉም አምላክ የሆነው ፈጣሪያችን ደግሞ ሰማያዊ ፀጋውን ያለብሰናል፡፡
  5. የታመመን መጠየቅ፡- በዘመናችን በየቤታችን፣ በጐረቤቶቻችን፣ በየሆስፒታሉ ወዘተ የታመሙ ወይም -የጤና መታወክ የደረሰባቸው ወገኖች ብዙ ናቸው፡፡ ታሞ ለተኛ ጠያቂ፣ አይዞህ ባይ፣ የሚያፅናና ያስፈልገዋል፡፡ ብንችል እግዚአብሔር በሰጠን መጠን በገንዘባችን መደገፍ፣ ጊዜያችንን መስጠት፣ እግዚአብሔር ይማራችሁ በሚል የማፅናኛ ቃል ልግፅናናቸው ያስፈልጋል፡፡ ያስፈልጋል። የተማሙትን ለመርዳት ምን ምን ተጨባጭ የሆኑ ተግባሮችን መፈጸም ይገባና?

6 የታሰረን መጐብኘት፡- ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች፣ አውቀውም ሆነ ሳያውቁ በሰሩት ጥሩ ባልሆነ ተግባር ወይም በግፍ ዘብጥያ ወይም ወኅኒ ሊገቡ ወይም ሊታሰሩ ይችላሉ፡፡ የሚታሰሩ ሁሉ ጥፋተኞች ናቸው ማለት ግን ስህተት ነው፡፡ ምክንያቱም ያለበደላቸው የሚታሰሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ ሐዋርያትም ለምሳሌ ጳውሎስና ሲላስ የኢየሱስን ስም ስለጠሩ ብዙ ግዜ ታስረዋል፡፡ /የሐ.ሥራ 16፡ 23-4ዐ/ የዕብራውያን ፀሐፊ “እስረኞችን አስቡ ይለናል” አስቡ ሲለን ሄደን መጠየቅና መገዝን ያጠቃልላል፡፡ ነቅቶ መጠበቅ ማለት ይህ ነው፡፡

7. የሞተን ምቅበር (መ. ጦቢት 1.17-19)

የተወደዳችሁ የእግዚኣብሔር ቤተሰቦች እና በጎ ፈቃድ ያላችሁ በሙሉ!

በዛሬው ቅዱስ ወንጌል ላይ እንደ ተጠቀሰው ኢየሱስ “ጊዜውን እና ወቅቱን ሰለማታውቁ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ” ይለናል። ከላይ የተጠቀሱትን መልካም ነገሮችን በመፈጸም ነቅተን እርሱን መጠበቅ እንችል ዘንድ የእግዚኣብሔር ጸጋ እና ድጋፍ ያስፈልጋል። ሁልጊዜ ነቅተን መልካም ተግባራትን እየፈጸምን ያገኘን ዘንድ የክርስቲያኖች ረዳት የሆነችሁ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያ በአማልጅነቷ ትርዳን። አሜን!

(አባ መብራቱ ኃይሌጊዮርጊስ)

 

 
All the contents on this site are copyrighted ©.