2017-07-24 09:26:00

የሐምሌ 16/2009 ዓ.ም. እለተ ሰንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ በክቡር አባ መብራቱ ኃይለጊዮርጊስ።


የሐምሌ 16/07/2017 ሰንበት ቃለ አስተንትኖ

እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ቸርነትህ መጠን፣ ምሕረት አድርግልኝ፤ እንደ ርኅራኄህም ብዛት፣መተላለፌን ደምስስ” (መዝ. 51:1)

የተወደዳችሁ የእግዚኣብሔር ቤተሰቦችና በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ።

ምሕረት ይቅርታን ያስገኛል። ባሳለፍነው ሳምንት ውስጥ ለእለታዊ ኑሮዋችን አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች በመሥራት፣ ለራሳችንና እና ለቤተሰቦቻችን አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ስናከናውን ቆይተናል። በዚህም ውጣ ውረድ ውስጥ በአጋጣሚ ይሁን ሆን ብለን እህት ወንድሞቻችንን ያስቀየምናባቸው፣ የበደልናቸው ወቅቶች እንደ ሚኖሩ እሙን ነው። ለእዚህ ነው ታዲያ የዛሬው እለት ሰንበት አስተንትኖዋችን “እግዚኣብሔር ሆይ ምህረትህን አድርግልኝ” በሚለው በዳዊት የመማጸኛ ጸሎት የጀመርነው። ዳዊት በዚሁ በመዝሙር 51 ላይ እግዚኣብሔርን እና እግዚኣብሔር በቅንነት እንዲያገለግል የሰጠውን ሕዝብ በመበደሉ የተነሳ እግዚኣብሔር ምሕረት እንዲያደርግለት ሲማጸን እንሰማለን። በዚሁ ምዕራፍ ውስጥ ዳዊት ምሕረት፣ የማይናወጥ ፍቅር፣ ታላቅ ርኅራኄ፣ ደምስስ፣ እጠብ፣ አንጻ፣ መተላለፍ፣ በደል፣ ኅጢአት የሚሉትን ቃላት በተደጋጋሚ ሲጠቀም እናያለን።

የዚህን አስተንትኖ ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

ከበደሉ ሁሉ እግዚኣብሔር ያነጻው ዘንድ ዳዊት ከፍተኛ የሆነ ሮሮ ወደ እግዚኣብሔር እንዳቀረበ ሁሉ እኛም በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ከሠራነው ኅጢአት ያነጻን እና ያጥበን ዘንድ ወደ እግዚኣብሔር መጮኽ ይገባናል። “ሰማይ ከመሬት ከፍ እንደ ሚል” ሐሳቡ ከሐሳባችን መንገዱ ከመንገዳችን ልዩ የሆነው እግዚኣብሔር በምሕረቱ ይጎበኘን ዘንድ በርትተን ልንጸልይ ይገባናል ማለት ነው።

በዛሬው እለተ ሰንበት እኛ እናስተነትንበት ዘንድ ቤተክርስቲያናችን የሰጠችን የእለቱ ምንባባት በቀዳሚነት የተወሰደው ቅዱስ ሐዋሪያው ጳውሎስ ወደ ቆሮንጦስ ከጻፈው ሁለተኛ መልእክቱ 10:1-18 ላይ የተወሰደው ጳውሎስ ሰለአገልግሎቱ ያቀረበው መከላከያ የሚያመልክት ሲሆን ጳውሎስ በዚሁ መልእክቱ “ጌታ በሰጠኝ ሥልጣን እጅግ ብመካም በዚህ አላፍርም፤ ሥልጣኑን የተቀበልነው እናንተን ለማነጽ እንጂ ለማፍረስ አይደለምና” በማለት እኛ ክርስቲያኖች ይነስም፣ ይባዛም/ በቤተሰብ ውስጥ ይሁን በሥራ ቦታ የተሰጠንን ኃላፊነት ሰዎችን ለማነጽ እንጂ ለማፍረስ ማዋል እንደ ሌለብን ሐዋሪያው ጳውሎስ ዛሬ ያሳስበናል።

በዛሬው እለተ ሰንበት በሁለተኛነት ለአስተንትኖ ይሆነን ዘንድ የተሰጠን የእግዚብሔር ቃል የተወሰደው ቅዱስ ሐዋሪያው ያዕቆብ ከጻፈው መልእክቱ ከምዕራፍ 3:10-8 ላይ የተጠቀሰው አደበትን መግታት በሚል አርእስት የተቀመጠው ሲሆን “ፈረሶች እንዲታዘዙልን ልጓም በአፋቸው ውስጥ ስናስገባ፣ መላ ሰውነታቸውን መምራት እንችላለን። ወይም መርከቦችን ተመልከቱ፤ ምንም እንኳ እጅግ ትልቅና በኀይለኛ ነፋስ የሚነዱ ቢሆኑም የመርከቡ ነጂ በትንሽ መሪ ወደ ሚፈልገው አቅጣጫ ይመራቸዋል። እንዲሁም ምላስ ትንሽ የሰውነት ክፍል ሆና ሳለ በታላላቅ ነገሮች ትኵራራለች፤ ትልቅ ጫካ በትንሽ እሳት እንዴት ተቃጥሎ እንደሚጠፋ አስተውሉ፤ ምላስም እንደ እሳት ናት፤ በሰውነት ክፍሎቻችን መካከል የምትገኝ የክፋት ዓለም ናት፤ ሰውነትን ሁሉ ታረክሳለች፤ ደግሞም የፍጥረትን ሩጫ ታቃጥላለች፤ ራሷም በገሃነም ትቃጠላለች” የሚለው ነው። ይህም መልእክት ምንም እንኳን ሁል ጊዜ ምላሳችንን መቆጣጠር አስቸጋሪ የሆነ ነገር ቢሆንም ቅሉ፣ ምላሱን የሚቆጣጠር ፍጹም የሆነ ሰው ካለ ግን ያሰው ሕይወቱን መቆጣጠር ይችላል ማለት ነው። ከምላስ የሚመነጭ ክፉ ነገር፣ ሁልጊዜም ቢሆን ምንጩ ዲያቢሎስ ነው። በምላሳችን እግዚኣብሔርን እናመሰግናለን፣ በምላሳችን ለእግዚኣብሔር እንዘምራለን፣ በምላሳችን ሰዎችን እናወድሳለን፣ በተቃራኒው ግን በምላሳችን ብዙ ክፉ የሚባሉ ነገሮችን እንፈጽማለን።

ለዚህም ነው እንግዲህ ነብዩ ኢሳያስ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ይህ ሕዝብ በአፉ ወደ እኔ ይቀርባል፤ በከንፈሩም ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው፤ የሚያመልከኝም፣ ሰው ባስተማረው ሰው ሠራሽ ሥርዐት ብቻ ነው” (ኢሳያስ 29:13) በማለት እግዚኣብሔር በሰው ልጆች የይስሙላ ተግባር እንዳልተደሰት ይናጋራል። በዛሬው ሰንበትም አንደበታችንን መግራት የሚያስችለን ጥበብ እግዚኣብሔር ይሰጠን ዘንድ ልንማጸን ያስፈልጋል፣ ምክንያቱ አንደበታችን ሁል ጊዜም ከሰው ጋር ያጋጨናል፣ ከእግዚኣብሔርም እንድንርቅ ያደርገናልና።

በዛሬው ወንጌል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትልቅ ተአምራትን ሲሰራ ያሳየናል፡፡ ተአምር ማለት አስደናቂ ሥራ ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ በብሉይ ኪዳን ለሕዝቡ ማንነቱን ለማሳየትና ለማስተማር የተለያዩ ተአምራትን አድርጓል፡፡ ለምሳሌም በሙሴ በእያሱ በኤልያስ በመሳሰሉት ነብይት ተአምራትን አሳይቷል፡፡ በአዲስ ኪዳንም ጌታችንን መዳኃኒታችን ብዙ ተአምራትን እንዳደረገ አይተናል፡፡ ለምሳሌ በእናታችን ምልጃ ውሃን ወደ ወይን ለወጠ ፣ በውሃ ላይ ተራመደ ፣ ንፋስን ፀጥ በማድረግ ስልጣኑን አሳየ፡፡ አጋንንትን አወጣ ፣ ሰዎችን ከብዙ ደዌዎችና በሽታዎች ፈወሰ፡፡ ሦስት ሰዎችን ከሞት አስነሳ፡፡ ተአምራዊ ስራዎቹ እጅግ ብዙ ናቸው፡፡

የሰው ልጅ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ የማይገጥመው የኑሮ ውጣውረድ ፣ የኑሮ ማዕበል ውሽፍርና ሞገድ የለምና የዚህ አይነት መከራ በራሱም በቤተሰቡም ይመጣበታል ፤ በሽታ ፣ ችግር ፣ የኑሮ ውድነት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ የሰው ልጅ በነዚህ ችግሮች ሲወድቅ ሊመካበት ችግሩን ሊቋቋምበት የሚችልበትን ሀብት ፣ወገን ሊሻ የግድ ይለዋል፡፡በዚህ ወቅትም የራሱ ወገንም ሆነ ሀብት ይሸሹታል በዚህ ችግር ወቅት አይዞህ ባይ በርታ ባይ ያስፈልገዋል፡፡ በዚህ ችግር ወቅት አይዞህ ባይ በርታ ባይ ሲያጣ ተስፋ ይቆርጥል ፤ ራሱንም ይጠላና ራሱን ለማጥፋት ያስባል ምክንያቱም በዚህ ችግርና መከራ ውስጥ አይዙህ ባይ ከማጣቱም ባሻገር የራሱ የሆነ ጉልበት ሁሉ ይክደወል፡፡

ታዲያ ለዚህ መድኃኒቱ ምን ሊሆን ይችላል? ምንም ቢባል መልሱ አንድና አንድ ብቻ ነው፡፡ የሰናፍጭን ቅንጣት የምታክል እምነት ካለን በቂ እንደሆነ ንፋስም ባሕርም የሚታዘዙለት ፤ ባሕሩንም ሞገዳችንንም ፣ ችግሮቻችንንም ፣ በሽታዎቻችንንም ሁሉ ፀጥ ለጥ ብለው የሚገዙለት አምላክ ከእኛ ጋር  ነውና ለሱ መንገር ብቻ ነው፡፡

ዛሬ ቀደም ሲል ሲነበብ የሰማችሁት ቅዱስ ወንጌል ከማቴዎስ ወንጌል 8:1-34 ላይ የተወሰው “በመጀመሪያ ከለምጽ ስለ ነጻ ሰው፣ በሁለተኛ ደረጃ የመቶ አለቃው የነበረውን ከፍተኛ እምነት እየሱስ ማድነቁ፣ በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ኢየሱስ ብዙ ሰዎችን መፈወሱን የሚገልጽ ምልእክት ያለው የወንጌል ክፍል ነው።

በዛሬው ቅዱስ ወንጌል ውስጥ በቅድሚያ ከለምጽ የነጻውን ሰው ታሪክ እናገኛለን፣ ለምጽ የሚለው ቃል በግሪክ ቋንቋ የሚያመለክተው የለምጽ በሽታን ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም ዓይነት የቆዳ በሽታን ያመለክታል። ይህ ሰው ኢየሱስን በትህትና ቀርቦትና ተንበርክኮ “ጌታ ሆይ! ብትፈቅድስ ልታነጻኝ ትችላልህ?” በማለት ሲጠይቀው እንሰማለን።

በለምጻሙ ሰው እና በኢየሱስ መካከል በተደረገው ውይይት ውስጥ ሁሉት አስገራሚ እውነታዎችን እናገኛለን። በቅድሚያ ፈውስ የሚገኘው ሁሉን ቻይ በሆነው በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መልካም ፈቃድ ብቻ መሆኑን ያሳያል። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የዚህን ለምጻም ሰው እርጠኛ፣ ጠንካራና ጽናት ያለው እምነት እናገኛለን።  የእኛ የሰው ልጆች ሕይወት በብዙ ነገሮች ውስጥ በእየለቱ ያልፋል። በበሽታ፣ በመከራ፣ በጭንቀት፣ የአእምሮ ረፍት በማጣት፣ የመሳሰሉት ነገሮች ሕይወታችንን እያመሱት ይገኛሉ። ስለዚህም የእግዚኣብሔር ፈውስ ያሻናል ማለት ነው።

በዛሬው ቅዱስ ወንጌል ውስጥ የተጠቀሱት ተአምራት ከለምጽ በሽታ ከተፈወሰው ሰው አንስቶ፣ የመቶ አለቃው አገልጋይ፣ የጴጥሮስ አማትና በተለያዩ እርኩስ መናፍስት ተይዘው የነበሩ ሰዎች የተፈውስት የእግዚኣብሔር በጎ ፈቃድ እና እነዚህ ሰዎች በነበራቸው ጠንካራ እምነት የተነሳ መሆኑን ከዛሬው ቅዱስ ወንጌል ለመረዳት እንችላለን።

ታዲያ ይህንን የእግዚኣብሔር ፈውስ በምንሻበት ወቅቶች ሁሉ ይህ መሻታችን እውን ይሆን ዘንድ ቀደም ሲል የተጠቀሱትን ሁለት መስፈርቶች ሟሟላት ይገባናል፣ ሁሉን ቻይ የሆነውን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መልካም ፈቃድ መጠየቅና በእኛ በኩል ደግሞ ጠንካራና ጽናት ያለው እምነት ሊኖረን ያስፈልጋል ማለት ነው። በተለይም ደግሞ በጊዜው ትልቅ የሚባል ወታደራዊ ስልጣን የነበረው የመቶ አለቃ የነበረው ሰው በስልጣኑ ሳይመካ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝ እንደ ሆነ በማመኑና እርሱና ቤቱ ለጌታ የተገቡ አለመሆናቸውን በትህትና በመግለጹ የተነሳ ያሰበውና የጠየቀውን ፈውስ መግኘቱን ሰምተናል።

ሁል ጊዜም ቢሆን ራሳችንን ዝቅ አድርገን በእምነት  በጌታ ፊት በምንቀርብበት ጊዜ ሁሉ እርሱ የልባችንን መሻት የሰጠናል ማለት ነው።

ሁላችንም ኃጢአት በመሥራታችን የተነሳ የእግዚኣብሔር ክብር ጎሎናል። ለጌታ ክብር የተገባን አይደለንም። ብዙን ጊዜ እመነት ይጎለናል። በእመነታችንን ጠንክረን፣ ከኃጢኣት ነጽተን፣ በምላሳችን ሳይሆን በሕይወታችን የእግዚኣብሔርን ክብር በመግለጽ የእርሱን ፈቃድ ፈጻሚዎች እንሆን ዘንድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያ በአማላጅነቱ ትርዳን። አሜን!

 

አባ መብራቱ ኃይለጊዮርጊስ

 








All the contents on this site are copyrighted ©.