2017-07-17 11:42:00

የካቶሊካዊ ተሃድሶ እንቅስቃሴ አጀማመርና ዓላማ ክፍል ስድስት አስተምህሮ በክቡር አቶ ዩሐንስ መኮንን


 

ካቶሊካዊ ተሃድሶ እንቅስቃሴ

አድማጮቻችን ስለ ካቶሊካዊ ተሃድሶ እንቅስቃሴ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማድረግ፣ ከእንቅስቃሴው ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የተላኩትን መልዕክቶች ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያዊ ምክሮች ጋር በማድረግ በተከታታይ ስናቀርብላችሁ ቆይተናል። እንደሚታወቀው የካቶሊካዊ ተሃድሶ እንቅስቃሴ ዓላማ በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማያቋርጥ መታደስን እንድናመጣ መርዳት በመሆኑ በምስጢረ ጥምቀት እና በምስጢረ ሜሮን የተቀበልነው የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ተዳክሞ እንዳይቀር፣ የክርስትና ሕይወታቸንን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እየኖርን፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ መልካም ፍሬን ማፍራት እንድንችል የመንፈስ ቅዱስን ድጋፍ መለመን ነው። ይህ ታዲያ ጥቂት ክርስቲያኖችን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን በምስጢረ ጥምቀት ጸጋ አማካይነት ኢየሱስ ክርስቶስ በመሠረታት ቤተክርስቲያን ውስጥ አባል የሆንን በሙሉ የጸጋው ተካፋዮች እንድንሆን ተጠርተናል። ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያንን ሲመሠርታት በእርሱ ለምናምን ከአብ የተቀበለውን የመንፈስ ቅዱስ ጸጋዎች ሳያቋርጥ ወደ ዓለም በመላክ ዘወትር ይቀድሰናል።

የዚህን አስተምህሮ ጠቅላላ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

 

ሐዋርያው ጳውሎስም በዚህ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ እንድንመራ እና በእርሱ እንድንኖር እንዲህ በማለት ይመክረናል፦ “እንግዲህ በመንፈስ ኑሩ፤ የሥጋንም ምኞት አትፈጽሙ እላለሁ። ምክንያቱም የሥጋ ምኞት ከመንፈስ ምኞት ጋር ተቃራኒ ነው፤ መንፈስ እና ሥጋ እርስ በእርሳቸው ይቃረናሉ፤ ስለዚህ እናንተ የምትፈልጉትን ማድረግ አትችሉም፤ በመንፈስ ብትመሩ ግን የሕግ ተገዥዎች አትሆኑም። የሥጋ ሥራዎች የታወቁ ናቸው፤ እነርሱም ዝሙት፥ ርኲሰት፥ መዳራት፥ ጣዖትን ማምለክ፥ ሟርት፥ ጠላትነት፥ ንትርክ፥ ቅንአት፥ ቁጣ፥ ራስ ወዳድነት፥ መለያየት፥ አድመኝነት፥ ምቀኝነት፥ ስካር፥ ዘፋኝነት፥ እና እነዚህን የመሳሰሉ ናቸው። ከዚህ በፊት እንዳስጠነቀቅኋችሁ አሁንም ደግሜ አስጠነቅቃችኋለሁ። እንደእነዚህ ያሉትን ነገሮች የሚያደርጉ ሰዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።

ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በመታገዝ የምናፈራቸውን ፍሬዎች እንደሚከተለው ይዘረዝራቸዋል፦ የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ደግነት፥ በጎነት፥ ታማኝነት፥ ገርነት፥ ራስን መግዛት፥ ነው። እንደእነዚህ ያሉትን ነገሮች የሚቃረን ሕግ የለም። የኢየሱስ ክርስቶስ የሆኑት ሰዎች ሥጋን ከፍትወቱና ከምኞቱ ጋር ሰቅለውታል። በመንፈስ የምንኖር ከሆነ በመንፈስ እንመራ። አንዱ ሌላዉን ለጥል በማነሣሣት እርስ በእርሳችን እየተቀናናን በከንቱ አንመካ።” (ገላቲያ  5፡16–26)

እያንዳንዳችን ከእግዚአብሔር በተሰጠን ልዩ ልዩ ስጦታዎች በመታገዝ፣ እግዚአብሔር ደስ የሚሰኝበት መልካም ሥራዎቻችንን በፍቅር እና በቅንነት ማበርከት እንድንችል የመንፈስ ቅዱስ እገዛ ያስፈልገናል። ማንኛውንም አገልግሎት ማበርከት እንድንችል ከሁሉ አስቀድሞ የስጦታዎች ሁሉ የመጀመሪያ ስጦታ የሆነው የእግዚአብሔር ፍቅር ልባችን ውስጥ እንዲሞላ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ኅብረት መፍጠር ያስፈልጋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ሮም ሰዎች በላከው መልዕክቱ በምዕራፍ 5 ቁጥር 5 ላይ “በተሰጠን በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ስለ ሞላ ተስፋው አያሳፍርም።”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ካቶሊካዊ ተሃድሶ እንቅስቃሴን በማስመልከት እ. አ. አ. ኅዳር 15 ቀን 1986 ዓ. ም. ለኢጣሊያ ካቶሊካዊ ተሃድሶ እንቅስቃሴ ባስተላለፉት ሐዋርያዊ መልዕክታቸው በመንፈስ ቅዱስ የመታደስ ዋናው ምክንያት፥ እንደ መንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ለመኖርና የማያቋርጥ መንፈሳዊ እድገትን ማምጣት፣ ሥጋዊ ምኞቶችን በመቋቋም ለእግዚአብሔር ፍቅር ራስን ክፍት ማድረግ ነው ብለው ነበር። ይህን ውስጣዊ መለወጥ፣ የሕይወት መፈወስን እና አዲስ መንፈሳዊ አስተሳሰብ ማስፋፋትን እንደ ክርስቲያናዊ ጥሪ በመውሰድ ሐዋርያዊ ምስክርነትን ለመግለጽ ለሚሹ ምዕመናን መንፈሳዊ ተሃድሶ የሕይወታቸው ዋና መመሪያ እንዲሆን ያስፈልጋል በማለት ምክራቸውን ለግሰው ነበር።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ሐዋርያዊ መልዕክታቸውን በመቀጠል፥ ዛሬ ካቶሊካዊ ተሃድሶ እንቅስቃሴ በቤተክርስቲያናችን ላበረከተው አስተዋጽዖ እና ላስገኛቸው በርካታ ፍሬዎች በሙሉ እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ። ሁለተኛውን የቫቲካን ጉባኤ ተከትሎ የመጣው ይህ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ለቤተክርስቲያናችን ልዩ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ነው። በዘመናችን የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ቁሳዊነት እና ዓለማዊነት እጅግ ገንኖ፣ ለመንፈስ ቅዱስ ተገቢውን ምላሽ እንዳይሰጡ የብዙዎችን ሕይወት ባዳከመበት ጊዜ፣ ካቶሊካዊ ተሃድሶ እንቅስቃሴ ብዙ ክርስቲያኖችን ከጥፋት በመታደግ ብዙዎችን ወደ እግዚአብሔር የፍቅር ጥሪ በማምጣት ትልቅ ሚናን በመጫወት ላይ ይገኛል ብለዋል።

የተወደዳችሁ አድማጮቻችን ካቶሊካዊ ተሃድሶ እንቅስቃሴን አስመልክተን ያቀረብነውን አጭር ዝግጅት በዚህ እንፈጽማለን። ሳምንት በተመሳሳይ ዝግጅት እስክንገናኝ የመንፈስ ቅዱስ አንድነት ከሁላችን ጋር ይሁን። አሜን።

በክቡር አቶ ዩሐንስ መኮንን የተዘጋጄ

 

 
All the contents on this site are copyrighted ©.