2017-07-03 18:04:00

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የተሃድሶ ዓላማ ክፍል አራት አስተምህሮ በክቡር አቶ ዩሐንስ መኮንን።


ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ስድስተኛ እና ካቶሊካዊ ተሃድሶ እንቅስቃሴ

የተወደዳችሁ አድማጮቻችን ይህ ከቫቲካን ሬዲዮ የሚተላለፍላችሁ የአማርኛ ቋንቋ አገልግሎት ነው። ባለፉት ሁለት ተከታታይ ሳምንታት ስለ ካቶሊካዊ ተሃድሶ እንቅስቃሴ አጀማመር እና የእንቅስቃሴውን ዋና ዓላማ የተመልከቱ ዝግጅቶችን ማቅረባችን ይታወሳል። ወደ ዛሬው ዝግጅታችን ከመሄዳችን አስቀድመን የእንቅስቃሴውን አጀማመርና ዓላማ ባጭሩ እናስታውሳችሁ።

የዚህን አስተምህሮ ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

ካቶሊካዊ ተሃድሶ እንቅስቃሴ እ.አ.አ. የካቲት ወር 1967 ዓ.ም. በአሜሪካ፣ ፔንሲልቬኒያ ግዛት ውስጥ የተጀመረ ሲሆን በዚሁ ክፍለ ግዛት የዳክስን ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በሳምንቱ መጨረሻ በኅብረት ሆነው ለጸሎትና እና የመጽሐፍ ቅዱስን መልዕክት ለመካፈል ይሰበሰቡ ነበር። የጸሎታቸው ቀዳሚ ዓላማ በተለይ በሁለቱ ምስጢራት በኩል፥ በምስጢረ ጥምቀትና በምስጢረ ሜሮን የተቀበሉት የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በሕይወታቸው ውስጥ መልካም ፍሬ እንዲያፈራ ለማድረግ ከእግዚአብሔር ድጋፍን ለመለመን ነበር። የእንቅስቃሴው ዓላማ እላይ የተጠቀሱትን የቤተክርስቲያን ምስጢራት የተቀበሉትን በሙሉ፣ የጾታና የዕድሜ ገደብ ሳያስቀምጥ የሚጋብዝ በመሆኑ ዛሬ በመላው ዓለም በሚገኙ ካቶሊካዊ ተቋማት፣ በቤተ ክኅነት፣ በገዳማት፣ በሃገረ ስብከቶች፣ በቁምስናዎች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በመንፈሳዊ ማኅበራት እና በመላው ምዕመናን መካከል ተስፋፍቶ ይገኛል። እንቅስቃሴው በስም የሚታወቅ መስራች ግለ ሰብ እንደሌለው የሚታወቅ ሲሆን ምስጢረ ጥምቀት ባጎናጸፈን የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ አማካይነት ኢየሱስ ክርስቶስ በመሠረታት ቤተክርስቲያን ውስጥ አባል ያደረገን፣ ቤተ ክርስቲያን እንድትታነጽ፣ እንድትቀደስ እና ሁላችንንም አንድ አድርጎን ወደ አንድ የእውነት መንገድ የሚመራን፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከልን መንፈስ ቅዱስ ብቻ የእቅስቃሴው ጠባቂና መሪ እንደሆነ የእንቅስቃሴው አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ያስገነዝባል።

የቅዱስ ጴጥሮስ እንደራሴ በመሆን መላዋ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያንን ከመሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መካከል ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ስድስተኛ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በተለያዩ ዓመታት እንቅስቃሴዉን የሚያበረታቱ ሐዋርያዊ መልዕት ማስተላለፋቸው ይታወሳል። በዛሬው ዝግጅታችን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ስድስተኛ ካስተላለፉት ሐዋርያዊ መልዕክቶች መካከል የሚከተለውን እናቀርብላችኋለን።

ወዳጆቼ ሆይ! በተለያዩ ክፍለ ዓለማት፣ በብዙ መልኩ የቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ ሕይወት እየታደሰ መምጣቱን በማየታችን ደስታ ይሰማናል። ይህ ሁሉ ሲሆን የመንፈስ ቅዱስ ድንቅ የሆነ ምስጢራዊ ሥራ ለቤተ ክርስቲያን ኃይልን እና ሕይወትን እንደሚሰጥ እናምናለን። ስለዚህም መንፈሳዊ ተሃድሶ ለቤተክርስቲያን እና ለመላው ዓለም እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ እንገነዘባለን። ታዲያ ይህ ተግባራዊ እንዲሆን የሚጠበቅብንን ተሳትፎና አገልግሎት ማበርከት ያስፈልጋል። ዛሬ ከምን ጊዜም በላይ እጅግ በተመሰቃቀለው ዓለም መካከል ከመንፈስ ቅዱስ የሚገኘውን መታደስ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በገሃድ ማሳየት ያስፈልጋል። የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች ብዙ ናቸው። መንፈስ ቅዱስ በምዕመናን መካከል የጠበቀ ግንኙነት እንዲኖር ያደርጋል፣ ከምስጢረ ጥምቀት የተቀበልነውን መንፈሳዊ ስጦታን በታማኝነት አጥብቀን እንድንይዝና ከእግዚአብሔር ጋር የማያቋርጥ ግንኙነት እንዲኖረን ያደርጋል፣ በምዕመናን የሕብረት ጸሎት ወቅት እያንዳንዱ ምዕመን የሚያቀርበው ጸሎት የመላው ምዕመናን ጸሎት አካል በመሆን መንፈስዊ ለውጥን ለማምጣት ተጨማሪ ድጋፍ እንዲሆን ያግዛል፣ የዚህ መለወጥ ዋና መሠረቱ እምነታችን ብቻ ሳይሆን የሰው ልጅ በዕለታዊ ኑሮ መካከል ያለ እግዚአብሔር ድጋፍ ምንም ማከናወን እንደማይችል፣ ነገር ግን ከእግዚአብሔር ጋር ከሆነ ሁሉንም ማድረግ ይችላል። በማለት እ. አ. አ. ግንቦት 19 ቀን 1975 ዓ. ም. ሮም ላይ ለተሰበሰበው የካቶሊካዊ ተሃድሶ እንቅስቃሴ አስተባባሪዎች፣ ሁለተኛ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ባስተላለፉት ሐዋርያዊ መልዕክታቸዉ ገልጸዋል።

የተወደዳችሁ አድማጮቻችን ካቶሊካዊ ተሃድሶ እንቅስቃሴን በማስመልከት ያቀረብነውን ዝግጅት ከማጠቃለላችን አስቀድመን የሚከተለውን የሐዋርያው ጳውሎስ መልዕክት እናነባለን፥በክርስቶስ አማካይነት ሁላችንም በአንድ መንፈስ ተመርተን ወደ አብ እንቀርባለን።(የሐዋርያው ጳውሎስ መልዕክት ወደ ኤፌሶን ሰዎች ምዕራፍ 2 ቁጥር 18)

 








All the contents on this site are copyrighted ©.