2017-06-23 09:47:00

“የቅዱሳን ሕይወት የክርስትና አስተሳሰቦች ገቢራዊ ሊሆኑ አይችሉም የሚለው አስተሳሰብ ፉርሽ ያደርጋል"።


ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በሳምንት አንድ ቀን በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ረፋዱ ላይ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን እና የሀገር ጎብኚዎች ሰፋ ያለ የጠቅላላ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። የዚሁ አጠቃላይ አስተምህሮ አንድ አካል በሆነው በሰኔ 14/2009 ዓ.ም. አስተምህሮዋቸው ከዚህ በፊት የክርስቲያን ተስፋ በሚል አርዕስት ስያደርጉት የነበረው አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን በእለቱ በተነበበው እና ወደ ዕብራዊያን በተጻፈው መልእክት ላይ ምዕራፍ 11:40 ላይ በተጠቀሰው “እግዚኣብሔር ለእኛ የተሻለ ነገር አቅዶልናል፣ እንደ ደመና በዙሪያችን የከበቡን እነዚህ ሁሉ ምስክሮች አሉን” በሚለው ሀረግ ዙሪያ ያጠነጠነ እንደ ነበረም ለመረዳት ተችሉዋል።

የዚህን ዜና ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማደመጥ ትችላላችሁ!

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ! እኛ በተጠመቅንበት ቀን ለእኛ የሚጸልዩ የቅዱስን ልመና ወደ እግዚኣብሔር አስተጋብቱዋል” በማለት አስተምህሮዋቸውን የጀመሩት ቅዱስነታቸው “ከዚህ በፊት የጀመርነው እና የክርስቲያን ተስፋ በሚል ጠቅለል ባለ አስተሳሰብ ስናደርገው የነበረው አስተምህሮ፣ በዛሬው እለት ደግሞ “ከእኛ በፊት የነበሩ እና በእምነት ማህተም አትመውን ከዚህ ዓለም የተለዩትን ቅዱሳን ላይ ያተኮረ ትምህርት ይሆናል” ያሉት ቅዱስነታቸው በእለቱ በተነበበው እና ወደ ዕብራዊያን በተጻፈ ምልእክት ላይ ተመርኩዘው “እንደ ደመና በዙሪያችን የከበቡን እነዚህ ሁሉ ምስክሮች አሉን፣ እነዚህም እንደ ሸክም የሆነብንን ነገር ሁሉ አስወግደን በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግስ መሮጥ እንድንችል ይርዱናል” ብለዋል። “ምስጢረ ጥምቀት፣ ምስጢረ ተክሊል እና ምስጢረ ክህነት በሚሰጡባቸው ወቅቶች ሁሉ የቅዱሳን ሱታፌ እና አማላጅነታቸው ከእኛ ጋር ይሆን ዘንድ በማሰብ እና በማመን የቅዱሳንን ስም የያዘ የመማጸኛ ሊጣኒያ” እንደ ሚደገም በማስታወስ አስተምህሮዋቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ይህም የእነርሱ አማላጅነት እያንዳንዳችን የተሰጠን ጥሪ በአግባቡ መወጣት እንችል ዘንድ ያግዘናል ብለዋል።

“የቅዱሳን ሕይወት የክርስትና አስተሳሰቦች ገቢራዊ ሊሆኑ አይችሉም የሚለው አስተሳሰብ ፉርሽ” እንደ ሚያደርገው በመግለጽ አስተምህሮዋቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ምንም እንኳን ሰዎች በመሆናችን የተነሳ ድክመቶች ቢኖሩብንም በእግዚኣብሔር ጸጋ እና በቅዱሳን አማላጅነት፣ በእመንታችን እንድንጸናና ተስፋ እንዳንቆርጥ በማድረግ ይህ የምንኖርበት ዓለማችን መንፈሳዊ ለውጥ እንዲያመጣ እና ክርስቶስ የሰጠን ተስፋ ሁሉ ምልአት እንዲያገኝ ያግዛል ብለዋል።

ሁላችንም ቅዱሳን እንድሆን ዘንድ እግዚኣብሔር እንዲረዳን መማጸን ያስፈልጋል ያሉሉት ቅዱስነታቸው በእዚህ ዓለም ሕያው የክርስቶስ ምስክሮች እንድንሆን፣ በጥንካሬ የተሞላ የእርሱ ምስክሮች እንድንሆን እና ቅዱስ ወንጌልን ለሁሉም ወንድሞች እና እህቶቻችን ማሰራጨት እንድንችል በተለይም ደግሞ በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ የሚገኙትን እና ተስፋቸው እየደመዘዘ የሚገኙ ሰዎችን መርዳት እንድንችል ጸጋውን እንዲሰጠን እግዚኣብሔርን መማጸን ያስፈልጋል ካሉ ቡኃል የእለቱን አስተምሮ አጠናቀዋል።

 








All the contents on this site are copyrighted ©.