2017-06-18 16:17:00

የካቶሊካዊ ተሃድሶ እንቅስቃሴ አጀማመርና ዓላማ አስተምህሮ በክቡር አቶ ዩሐንስ መኮንን


የካቶሊካዊ ተሃድሶ እንቅስቃሴ አጀማመርና ዓላማ

የተወደዳችሁ አድማጮቻችን ባለፈው ሳምንት ባቀረብነው ዝግጅታችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 14 ቁጥር 18 ላይ “እናትና አባት እንደሌላቸው ልጆች ብቻችሁን አልተዋችሁም” ብሎ ለሐዋርያቱ በገባላቸው የተስፋ ቃል መሠረት ከትንሳኤው በኋላ በሃምሳኛው ቀን አጽናኙን መንፈስ ቅዱስ እንደላከባቸው እና በዚህም መንፈስ ቅዱስ በቤተክርስቲያን ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደወረደ ተመልክተን ነበር። ስለመንፈስ ቅዱስ ስጦታ አስመልክተን በተከታታይ ከምናቀርብላችሁ ዝግጅቶቻችን መካከል ቃል በገባንላችሁ መሠረት ዛሬ ስለ ካቶሊካዊ ተሃድሶ እንቅስቃሴ አጀማመር እና ምሥስረታ የሚከተለውን ዝግጅት እናቀርብላችኋለን።

የዚህን አስተምህሮ ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

ካቶሊካዊ ተሃድሶ እንቅስቃሴ የተጀመረው እ.አ.አ. የካቲት ወር 1967 ዓ.ም. በአሜሪካ፣ በፔንሲልቬኒያ ግዛት ውስጥ ነበር። በዚሁ ክፍለ ግዛት የዳክስን ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በየሳምንቱ መጨረሻ ለጸሎት ይሰበሰቡ ነበር። የጸሎታቸው ቀዳሚ ዓላማ የሆነው በተለይ በሁለቱ ምስጢራት ማለትም በምስጢረ ጥምቀትና በምስጢረ ሜሮን በኩል የተቀበሉትን ጸጋ በሕይወታቸው ተለማምደው በተግባር መኖር ይችሉ ዘንድ ከእግዚአብሔር ድጋፍን ለመለመን ነበር። አንድ ቀን ለረጅም ጊዜ በቆየው የጸሎት ሥነ ሥር ላይ የእግዚአብሔር ኃይል ተገለጠላችው። ይህም በመንፈስ ቅዱስ መጠመቅ ነበር። በዚያች ቀን ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከላቸው ድንቅ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ዜና በመላው አሜሪካ በሚገኙት ዩኒቨሲቲዎችና ኮሌጆች  ከዚያም ወደተለያዩ ካቶሊካዊ ቁምስናዎችና ተቋማት ተዳረሰ። ገና ጥንካሬን ያላገኙ ማኅበራት ተደራጁ። በሰባዎቹ አጋማሽ ላይ ከ30,000 በላይ ተሳታፊዎች የተገኙበት ካቶሊካዊ ተሃድሶ ጉቤዎች ተዘጋጁ። እንቅስቃሴው የመላዋ ቤተክርስቲያን ትኩረት የሳበ በመሆኑ እ.አ.አ. 1975 ዓ.ም. የእንቅስቃሴው አስተባባሪዎች ከያሉበት ተሰባስበው ወደ ሮም፣ ቫቲካን በመምጣት በወቅቱ የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ ከነበሩት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ስድስተኛ ጋር በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር ቻሉ። በኋላም ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ ጋር ተገናኝተው ለመወያየት ዕድሎችን አገኙ። የተለያዩ አገሮች ጳጳሳት ጉባኤዎችም ድጋፋቸውን ቸሩላቸው።   

ካቶሊካዊ ተሃድሶ እንቅስቃሴን ልዩ የሚያደርገው እና በግልጽ መታወቅ ያለበት ነጥብ ቢኖር እንደ ሌሎች በቤተክርስቲያኒቱ ሥር እንደሚገኙ ዓለም ዓቀፍ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ራሱን ችሎ በግሉ የሚንቀሳቀስ አለመሆኑ ነው። ካቶሊካዊ ተሃድሶ እንቅስቃሴ በስም የሚታወቅ መሥራች፣ ወይም በቡድን የሚታወቁ መስራች ግለሰቦች የሉትም። የአባላቱ ስም ዝርዝርና ቁጥራቸውን የሚገልጽ መረጃ የለውም። ምንም እንኳን ተመሳስይ ግብ ቢኖራቸውም እጅግ ሰፊ ልዩነት ያላቸው ግለሰቦችን፣ ማኅበራትን፣ የትምህርት እና የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን፣ ንዑሠ ክርስቲያንና ቁምስናዎችን እና በርካታ ሐዋርያዊ አገልግሎቶችን በውስጡ ያቀፈ እንቅስቃሴ ነው። እንቅስቃሴው የሚታወቅበት የጋራ ምልክት በመንፈስ ቅዱስ መጠመቅ ሲሆን አባላቱ በሕይወታቸው ታላቅ መታደስን ወይም መለወጥን ሊያመጡ የሚችሉት ምንም እንኳን አስቀድመው በምስጢረ ጥምቀት በኩል የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ የተቀበሉ ቢሆንም ሕይወት በመንፈስ ቅዱስ የተሰኘውን ልዩ የማነቃቂያ ስልጠና ከተቀበሉ በኋላ በመንፈስ ቅዱስ የመታደስ ጥምቀትን ይቀበላሉ።

የቅዱስ ወንጌል ተልዕኮ በአዲስ ዘመን በተሰኘው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ስድስተኛ ሐዋርያዊ ድንጋጌ ቁጥር 75 የሚከተለውን ትዕዛዝ እናገኛለን፥ ቤተክርስቲያን የመንፈስ ቅዱስን ሥራ እና ጥበብ በሚገባ ለማወቅ በምትችልበት ዘመን ላይ እንገኛለን። በመሆኑም ሕዝቦች በሚኖሩበት ሥፍራ ሁሉ፣ እንደ ቅዱስ ቃሉ መሠረት ስለ መንፈስ ቅዱስ የበለጠ ለማወቅ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ራሳቸውን በእርሱ ለማስገዛት ይሻሉ፣  በእርሱ ስም መሰብሰብን እና በእርሱ መመራትን ይፈልጋሉ ይላል።

ካቶሊካዊ ተሃድሶ እንቅስቃሴ ባሁኑ ጊዜ ከሁለት መቶ አገሮች በላይ የሚገኝ ሲሆን የአባላቱ ቁጥር ከአንድ መቶ ሃያ ሚሊዮን በላይ ደርሷል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአንዳንድ አገሮች የአባላቱ ቁጥር መቀነስ ቢታይበትም በሌሎች አገሮች በተቃራኒው እጅግ በሚያስደንቅ ሁኔታ መጨመሩን የእንቅስቃሴው ድረ ገጽ www.iccrs.org ያስረዳል   ።

ካቶሊካዊ ተሃድሶ እንቅስቃሴ ዋና ጽ/ቤቱ በቫቲካን ከተማ የሚገኝ ሲሆን ምክር ቤቱ አምስቱን አህጉራት የሚወክሉ እና በተለያዩ ሐዋርያዊ አገልግሎቶች የተሰማሩ ከካህናት፣ከገዳማዊያን እና ከምዕመናን ወገን የተወጣጡ 15 አባላት ያሉት ሲሆን በአንድ ወይም በሁለት አማካሪዎቻቸው ይታገዛሉ።

የተወደዳችሁ አድማጮቻችን ሳምንት በምናቀርብላችሁ ዝግጅታችን የእንቅስቃሴውን ዓላማ እና ይዘት የሚገልጽ ዝግጅት ይዘን እንመለስበታለን፤ እንዳያመልጣችሁ ከወዲሁ እንጋብዛችኋለን።

(በክቡር አቶ ዮሐንስ መኰንን የተዘጋጀ)

 








All the contents on this site are copyrighted ©.