2017-06-04 18:18:00

ቅድስት ድንግል ማርያም የጽኑ እምነት አስተማሪ ናት።


ቅድስት ድንግል ማርያም የጽኑ እምነት አስተማሪ ናት።

የተወደዳችሁ አድማጮቻችን ይህ ዝግጅት የሚደርሳችሁ ከቫቲካን ሬዲዮ የአማርኛ ቋንቋ ስርጭት ነው።  የግንቦት ወር ከቅድስት ድንግል ማርያም ጋር በጸሎት የምንገናኝበት እና ከእርሷ ሕይወት ለመማር ተጨማሪ አጋጣሚን ይፈጥርልናል። በዛሬው ዝግጅታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን እምነት የተመለከተ አጭር መልዕክት ከዚህ ቀጥሎ እናቀርብላችኋለን፣ ቆይታችሁን ከዝግጅታችን ጋር እንድታደርጉ አስቀድመን እንጋብዛችኋለን።

የዚህን አስተምህሮ ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

እግዚአብሔር አምላካችን በፍቅሩ ብዛት ለእያንዳንዳችን የዘለዓለምን ሕይወት እንድንወርስ፣ የመንፈስ ቅዱስን፣ የምሕረትን፣ የእምነትንና ሌሎችንም የጸጋ ስጦታዎችን ሰጥቶናል። እምነት እግዚአብሔር ለሰው ዘር የለገሰው፣ ሙሉ በሙሉ ነጻ የሆነ ስጦታ እንደሆነ በቤተ ክርስቲታናችን ትምህርተ ክርስቶስ፣ በሦስተኛው ምዕራፍ ቁጥር 162 ላይ ተጠቅሶ እናገኘዋለን። እግዚአብሔር የእምነት ጸጋን ከሰጠን በኋላ እርሱን በመንፈስና በእውነት እንድናገለግለው ሳያስገድደን ከጊዜ ወደ ጊዜ ይጠራናል። የሚያምኑ ሁሉ አባት የሆነው አብርሃም በርስትነት ወደሚረከበው ስፍራ እንዲሄድ በተጠራ ጊዜ፣ ምንም እንኳን ወዴት እንደሚሄድ ባያውቅም ትዕዛዙን በእምነት ተቀብሎ ሄደ። ስለ እምነት ትርጉም ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ዕብራውያን በላከው መልዕክቱ በምዕራፍ 11 ቁጥር 1 ላይ፥ “እምነት ማለት በተስፋ የምንጠባበቃቸውን ነገሮች እንደምናገኝ የሚያረጋግጥ፥ የማናያቸውን ነገሮች ስለመኖራቸው የሚያስረዳ ነው” በማለት ይናገራል።

መልአኩ ገብርኤል ማርያም በቀላሉ ልትረዳቸው የማትችላቸውን የምሥራች እና የተስፋ መልዕክቶችን አምጥቶላት ነበር። ይህም በሉቃስ ወንጌል በምዕራፍ 1 ቁጥር 30 ላይ እንዲህ የሚለው ተጽፎ እናገኛለን፦ “ማርያም ሆይ! በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ አግኝተሻልና አትፍሪ፤ እነሆ ትጸንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ” ባላት ጊዜ ማርያም መልአኩን “እኔ ድንግል ነኝ፤ ታዲያ ይህ ነገር እንዴት ሊሆን ይችላል?” አለችው። መልአኩም መልሶ “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑል እግዚአብሔር ኃይል በአንቺ ላይ ይሆናል” አላት። ቅድስት ድንግል ማርያም መልአኩ ገብርኤል የነገራትን መልዕክት እንዲሁ በቀላሉ መረዳት ስለከብዳት፥ እንዴትስ ተግባራዊ ሊሆን እንደሚችል በሚገባ ለመረዳት በመፈለጓ መልሳ ጠየቀችው። መንፈስ ቅዱስ በእርሷ ላይ እንደሚመጣ፤ የልዑል እግዚአብሔር ኃይል በእርሷ ላይ እንደሚሆን አስረዳት።  ይህ የቅድስት ድንግል ማርያም ጥያቄ ለእምነታችን አካሄድ ጥሩ መንገድ ጠቋሚ ሊሆን ይገባል። በእምነት ጎዳና ላይ ስንጓዝ የሚነገረንን ወይም የሚሰበክልንን ሁሉ በጭፍኑ እንድንቀበል አልተጠራንም። ለእምነታችን ያለንን ግንዛቤ ከጊዜ ወደ ጊዜ ለማሳደግ ከፈልግን ሰፊ ማብራሪያ ሊሰጡን፣ እምነታቸውን ጠንቅቀው የሚያውቁና በተግባር መኖር ወደቻሉ ታማኝ ሰዎች ዘንድ መቅረብ ያስፈልጋል። ምክንያቱም እምነትን ከሌሎች ተቀብለን ለሌሎች የምናስተላልፈው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው። ማንም ብቻውን መኖር እንደማይችል ሁሉ ማንም ብቻውን ማመን አይችልም።

ቅድስት ድንግል ማርያም እግዚአብሔር የወደደውን ለማድረግ ምንም እንደማሳነው አመነች። ስለዚህ በሕይወት ዘመኗ ሁሉ የእርሱ ፈቃድ እንዲቀድም ልቧን ለእርሱ ክፍት አደረገች። “እነሆ እኔ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነኝ፤ አንተ እንዳልክ ይሁንልኝ” በማለት የእግዚአብሔርን ፈቃድ አስቀደመች። ኤልሳቤጥም ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም እምነት እንዲህ ብላ ተናገረች፦ “አንቺ እግዚአብሔር የተናገረውን የሚፈጽም መሆኑን በማመንሽ ምንኛ የታደልሽ ነሽ።” (የሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 1 ቁጥር 45) ቅድስት ድንግል ማርያም በእያንዳንዷ የሕይወት ጉዞ የእግዚአብሔርን ፈቃድ በማስቀደሟ የመልካም እምነት ምሳሌ ሆናልናለች። በእምነት ለማደግና ለመጠንከር በምናደርገው ጥረት ውስጥ ቅድስት ድንግል ማርያምን ቀዳሚ አርአያ እናድርጋት። እኛም በእምነታችን መካከል ልቦናችንንና ምኞታችንን ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሔር እንድናስገዛ ቅድስት ድንግል ማርያም ትርዳን። አሜን።

ከዮሐንስ መኰንን








All the contents on this site are copyrighted ©.