2017-05-30 11:45:00

የመቂ ካቴድራል በተመረቀበት ዕለት ብፁዕ አቡነ አብርሃ የመቂ ሀገረ ስበከት ጳጳስ ያስተላለፉት ሐዋርያዊ መልዕክት


የመቂ ካቴድራል በተመረቀበት ዕለት ብፁዕ አቡነ አብርሃ የመቂ ሀገረ ስበከት ጳጳስ  ያስተላለፉት ሐዋርያዊ መልዕክት

 

"እግዚአብሔር ቤትን ካልሠራ ሠራተኞች በከንቱ ይደክማሉ" (መዝ. 127)

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን፡

ብፁዕ ሊቀ ጳጳስ ሉዊጂ ቢያንኮ በኢትዮጰያ የቅድስት መንበር ተወካይ

ብፁዓን ጳጳስት፣ ካህናት፣ ገዳማውያንና ገዳማዊያት ፣ወንድሞች፣ ካቴኪስቶች፣ ምዕመናንና ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች

ከሁሉም በማስቀደም እግዚአብሔር ወዶና ፈቅዶ ለዚህ በተባረከች ቀን ለእርሱ ምሥጋና ለማቅረብ በጋራ ስለሰበሰበን ክብርና ምሥጋና ለእርሱ ይሁን፡፡

ቀድሞ በሐረር ሀገረ ስብከት አስተዳደር ስር የነበረው ከ1963 ዓ. ም. ጀምሮ በኮንሰላታ አባቶች በመቂ ከተማ የተቆረቆረው ይህ የተቀደሰ ቦታ ዋና የሀገረስብከቱ ማዕከል ሆንዋል፡፡ በታህሳስ 1973 ዓ. ም. የመቂ ሐዋርያዊ አስተዳደር በመባል በክቡር አባ ጆን ቦንዛሚኦ የተጀመረው   በ1974 ዓ. ም. ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ የአስተዳደሩ ኃላፊ ተረከቡ፡፡ በጥር 1995 ዓ. ም. ወደ ሀገረ ስብከት ደረጃ በማደግ ብፁዕነታቸው የመጀመሪያው ጳጳስ በመሆን እስከዕለተ ሞታቸው ድረስ ሀገረስብከቱን በመምራት መሰረት አሲያዙት፡፡

ከእኔ ቀድሞ ለነበሩና ሀገረ ስብከቱን ከመጀመሪያው ጀምሮ ለዚህ ያደረሱትን ሁሉ በማሰብ ያለኝን አክብሮት እገልጻልሁ፡፡ ዛሬ  ሀገረ ስብከታችን የተመሰረተበትን 25ኛው የብር ኢዮቤልዩ በማክበር ላይ ይገኛል፡፡  ደረጃ በደረጃ ያቺ ትንሽ ዘር እያደገች ትገኛለች ለብዙሃን ጥላና ተስፋ ብትሆንም ገና ብዙ አገልግሎት ይጠበቅብናል፡፡  ዛሬ በሀገረ ስብከታችን 14 ቁምስናዎችና 82 ቤተ ጸሎቶች በሕንፀተ ክርስትና ላይ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ የካቶሊከ አማንያን ቁጥርም ተስፋ የሚሰጠን ነው፡፡ በእርግጥ ለመናገር የሀገረስብከቱ አገልጋዮች ሁሉ እግዚአብሔር ስላደረገልን ስጦታ እናመሰግናለን፡፡ እኔ ከምገልጸው በላይ ነው እግዚአብሔር በሀገረ ስብከታችን  እየሰራ ያለው፡፡ እግዚአብሔር የወይኑን እርሻ እንድንጠብቅ እንድንከባከብ በምንችለው አቅም፣ እውቀትና ችሎታ ተጠቅመን ለሕዝብ አገልግሎት እንድንሰጥ ነው የተጠራነው፡፡  የመቂ ሀገረ ስብከትን በእረኝነት እንዳገለግል ቤተክርስቲን ካዘዘችን  ጀምሮ በአገልግሎቴ የረዳችሁኝ የደገፋችሁኝ ካህናት፣ ደናግላን፣ ወንድሞች፣ ካቴኪስቶች፣ ምዕመናን በጐ አድራጊ አገር  ድርጅቶችን በዚህ አጋጣሚ ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ብዙውን አገልግሎት ለማበርከት የቻልነው የተሳሰረ ሕብረት በመኖሩ ነውና አገልግሎታችን አጠንክረን እንቀጥል በማለት አደራን አቀርባለሁ፡፡

ይህ በአዲስ መልክ የተገነባው ካቴድራላችን ታሪካዊነት ያለው ቦታ ነው፡፡ በታህሣስ 2004 ዓ. ም. መሠረተ ድንጋይ ከመቀመጡ በፊት አንድ ታላቅ ካቴድራል ለመገንባት ራዕይ  እንዳለኝ ለአንድ ታላቅ የቤተክርስቲያን ወዳጂያችን ስማከር ያለኝ አልረሳም፡፡

"ሕልም ታላቅ ከሆነ ያሰብኩውን ለመፈጸም ከተጋህ በጽናት ከተጓዝህ መድረስ እንደሚቻል፤   በእግዚአብሔር ጸጋ ተደገፍ ያሰብከውን ለፈጽም በርታ” በማለት ያበረታታኝ  ለመግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ ይህ ያለኝ ታላቅ የቤተክርስቲያናችን ወዳጅ በመካከላችን ይገኛሉ፡፡

በዚህ የተቀደሰ ሃሳብ መነሻ ነው ይህን ሕንጻ ጅማሬው፡፡ ሥራ ስንጀምር ምንም ገንዘብ ኖሮ አይደለም የጀመርነው፡፡ እግዚአብሔር በመታመን የእግዚአብሔር ሕዝብ በጊዜ ሂደት ፍጻሜ ደርሰዋል  በሚል ጽኑ አቋም በመያዝ ተነሳስተን ተጀመረ፡፡

በሚያስገርም ሁኔታ ሁሉም ወገን በአቅሙ ድጋፍ መስጠት የድርሻውን  አሻራ ለማሳረፍ ባደረገልን ድጋፍ መነሻነት ሥራው ቀጠለ፡፡  በተለይ ማመስገን የምፈልገው  የጀርመን፣ ኦስትሪያ፣ የጣሊያን፣ የእስፔን  ቤተክርስቲያኖች ድጋፋቸው ለጀመርነው ግንባታ ታላቅ እገዛ አድርጎልናል፡፡  ለግንባታው ከውጪ አገር  ሆነ ከሀገርም ውስጥ ከወዳጆቻችን የተደረግልን ድጋፍ ም እንዳልዘረዝር ብዙ ስለሆነ ላደረጋችሁልን ሁለንተናዊ ድጋፍ እግዚአብሔር ምኞታችሁን ፣መሻታችሁን ይሙላላችሁ በማለት ምስጋናየን አቀርባለሁ፡፡

ካቴድራላችን በኪዳነ ምሕረት ቅድስት ቅዱሳን፣ ንጽህት ንፁሐን ስም ከተሰየመ ጀምሮ ብዙ ድንቅ ነገሮች ተደርጎልናል፡፡  ዛሬም የምንሰባሰብበት ቤተመቅደስ ታንጾ ምሥጋና ለማቅረብ ዕድል አግኝተናል፡፡ መቂ በመሃል የአገራችን ክፍል ሰለምትገኝ የመቂ ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን ቅዱስ ቦታ በመሆንዋ የነጋደያን ቦታ እንደምትሆን ተስፋችና እምነቴ  ነው፡፡ እንደቀድሞው ዛሮም ወደፊትም ለብዙዎች  ተስፋና ማረፊያ መሆንዋን ትቀጥላለች፡፡

በሌላም በሀገረ ስብከታችን የተለያዩ ተግዳሮቶች አሉብን፡፡ ይህንን ማሸነፈ የምንችለው ተግተን በመፀለይና በሃይማኖት ፀጽናታችን በምናሳየው ቁርጠኝነት መሆኑን  ከሐዋርያዊ አገልግሎታችን ተምረናል፡፡

በአለፈው ዓመት የምህረት ዓመትን አክብረናል፡፡ በዚያው ዓመት በሀገረስብከታችን የሚያሳዝን ነገረ ተከስቶ ነበር፡፡ በርግጥ የደረሰው ጥፋት ከቤተክርስቲያናችን አቅም ከባድ ቢሆንም  የቤተክርስቲያናችን ዋና ተልኮ  ምሕረትና ይቅርታ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ   ሐዋርያዊ ሥራ ከህዥቡ ጋር በመሆን   አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡ እኛ የእግዚብሔር አገልግሎት ፈጻሚዎች እንጂ  ባለቤቱ ራሱ እግዚአብሔር በመሆን ካለፈው ተምረን ወደፊት መጓዝ አለብን በማለት ተስፋችንን አጠንክረን ተነስተናል፡፡

በመጨረሻም በድጋሚ በቤተክርስቲያን ውስጥም በውጪም ያላችሁ ሁሉ በመካከላችን ጥሪያችንን አክብራችሁ ተገኝታችሁ ይህን የመሰለ የጸጋ በዓል ሕይወት እንዲኖረው  ስላደረጋችሁልን  አመሰግናለሁ፡፡ እግዚአብሔር ያክብራችሁ ፤ኪዳነ ምህረት ምኞታችሁን ሃሳባችሁን ትሙላላችሁ፡፡

 








All the contents on this site are copyrighted ©.