2017-05-30 11:55:00

በድንቅ ኪነ ጥበብ ሥራ የተገነባው የመቂ ኪዳነምሕረት ካቴድራል ተባርኮ አገልግሎት ጀመረ


በድንቅ ኪነ ጥበብ ሥራ የተገነባው

የመቂ ኪዳነምሕረት ካቴድራል ተባርኮ አገልግሎት ጀመረ

"ይህችን ቤት አብ ሠራት፣ ወልድ አነጻት፣ መንፈስ ቅድስ ፈጸማት" (የቅዱስ ያሬድ ድጓ)

 

በአዲስ መልክ የተገነባውና በሥነ ጥበቡ አሰራር እጅግ አስደናቂ የሆነው የመቂ ኪዳነ ምሕረት ካቶሊክ ካቴድራል ግንባታው ተጠናቆ ግንቦት 16 ቀን 2009 ዓ. ም. የቃል ኪዳኑ ታቦት ተቀመጠበት፡፡

በዓሉ ከዋዜማ ጀምሮ በመቁጠሪያ ጸሎት፣ በቃለ እግዚአብሔር ትምህርትና  በዝማሬ የተጀመረ ሲሆን  በምሽት ጧፍ መብራት በመያዝ  በቤተክርስቲያኑ ዙርያ የዑደት ሥነሥርዓት ተደርጋል፡፡ የመቂ ሕዝበ ክርስቲያን ለቤተክርስቲያኒቷ ያለውን አክብሮት  ፣ምስክርነት የገለጸበት ዕለት ነበር፡፡

የዚህን ዜና ሙሉ ይዜት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

ግንቦት 16 ቀን  2009 ዓ. ም. ከማለዳው ጀምሮ በመቂ ሀገረ ስብከት የሚገኙት የሁሉም ቁምስና ተወካዮች እና የአካባቢው ሕዝብ እንዲሁም ከተለያየ ሀገረ ስብከት የመጡ ካቶሊካውያን  ወደ መቂ  ካቴድራል በመጉረፍ  ለበዓሉ መከበር ታላቅ ድምቀት  ሰጥተውታል፡፡ በዓሉን ከማለዳው ጀምሮ በያሬዳዊ ማሕሌት የተጀመረ ሲሆን በመቂ ከተማ ደግሞ በኣሉን አስመልክቶ  በሻሸመኔ የሚገኘው የካቶሊክ ትምህርት ቤት የእስካውት ማርሽ ባንድ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ምስል የያዙ ወጣቶች በማጀብ በዓሉ  ወደ ሚከበርበት የመቂ ኪዳነ ምህርት ካቴድራል የ3 ኪሎ ሜትር ጉዞ በማድረግ  በዓሉን አድምቀውታል፡፡

በበዓሉ ላይ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን፣ ብፁዓን የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት፤ ብፁዕ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሉዊጂ ቢያንኮ፣ በጣሊያን የትሬን ሀገረ ስብከት ጳጳስ፣ ጥሪ የተደገላቸው የሃይማኖት አባቶች የኦሮሚያ ክልል የዞኑ ሀላፊዎችና  ከ3 ሺ በላይ የሚቆጠር ሕዝብ ተገኝቷል፡፡

የበዓሉ ሥነ ሥርዓት ብፁዓን ጳጳሳት በተገኙበትና የቃል ኪዳኑ ታቦት ከቀድሞ ቤተክርስቲያን ተይዞ ወደ አዲሱ ቤተክርስቲያን ሲጓዝ በአካባቢው የነበረው ሕዝብ በእልልታና በዝማሬ ደስታውን ገልጿል፡፡

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን ከብፁዕ አቡነ አብርሃም የመቂ ሀገረስብከት ጳጳስና ከብፁዕ አቡነ ተስፋሥላሴ የአዲግራት ሀገረስብክት ጳጳስ ጋር በመሆን በመስቀል እየተመሩ በስተውጪ የሚገኘውን የቤተክርስቲያን ዙሪያ ያሉትን በሮችና ዓምዶች በቅባተ ሜሮን በመቀባት ባርከዋቸዋል፡፡  ወደ ቤተመቅደሱ ለመግባትም ለመባረክም         “እናንተ መኳንንት ሆይ ደጆችን ክፈቱ የክብር ንጉሥ ይግባ፤ ይህ የክብር ንጉሥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው”  በማለት  በስተውጪ ሆኖ ዲያቆኑ ጥያቄ  ያቀረበ ሲሆን ሶስቱ ብፁዓን ጳጳሳት የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር  ይግባ በማለት የካቴድራሉ በር በመክፈት  ወደ መቅደሱ በመግባት በውስጥ የሚደረገውን ሥርዓት መርተዋል ፡፡

በዚሁ ጊዜ ሕዝቡ የክብር ንጉሥ ይግባ  በማለት የምሥጋና ዝማሬ አቅርበዋል፡፡ ብፁዕ ካርዲናል ከብፁዓን ጳጳሳት ጋር በመሆን መጀመሪያ የቃል ኪዳን ታቦት መሰዊያውን ቦታ ፣ የቅዱስ ቁርባን ማረፊያን ቦታ፣ አራቱን የወንጌላውያን ተምሳሌት የሆኑትን አምድ 12ቱ በነብያትና በ12 ሐዋርያት ተምሳሌት የቆሙትን ዓምዶች በዘይተ ሜሮን ቅባት በመቀባት በየተራ ባርከዋቸዋል፡፡ በመቀጠልም በመላው ዓለም በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ውስጥ ብቻ የሚገኙትን 14ቱን የመስቀል መንገድ ምስልና፣ የትንሣኤ ምስል የሚያሳየውን ባርከዋል፡፡

ከቅዳሴ በፊት ብፁዕ አቡነ አብርሃ እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን ስለ ቤተክርስቲያኑ ሕንጻ አሰራር ሕንጻውን የሰሩትን ኢንጂነር  ክቡር አቶ-------         ገለጻ እንዲያደርጉ በጋበዙዋቸው ጊዜ  የቤተክርስቲያኒቱ ሕንጻ ንድፍ ኢትዮጵያዊ ኪነ ጥበብን  በአብዛኛው የያዘ መሆኑን  በመግለጽ በቦታው ለተገኘው ሕዝብ ስለ ሕንፃው አሰራር ገለጻ አድርገዋል፡፡

በመቀጠልም ሥርዓተ ቅዳሴውን ብፁዕ ካርዲናል እንዲያስጀምሩ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ጠይቀዋል፡፡ በቅዳሴው ላይ ብፁዕ ካርዲናል ባቀረቡት ቃለ ምዕዳን እግዚአብሔር የሰውን ልጅ የማዳን  የቃል ኪዳኑ ተስፋ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ፍጹም ትብብር እውን እንደሆነ  ገልጸው እመቤታችንን የሚወድና የእርሷን አብነት የሚከተል  ሁሉ ፍጽም የእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ አብሳሪና መስካሪ  መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመቀጠልም የመቂ ሀገረ ስብከት አባቶችን በማመስገን በሀገረ ስብከቱ በጊዜው እያደገ የመጣውን ሐዋርያዊና ማሕበራዊ ልማት ምን ያህል የእግዚአብሔር ሥራ ማሳያ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ ቤተክርስቲያን መገንባት ቀላል ባይሆንም በፊታችን ያሉትን ተግዳሮቶች በጸሎት፣ በመተባበር፣ በመቻቻል በእግዚአብሔር ጸጋ ብቻ በአሸናፊነት መወጣት እንደምንችል ገልጸዋል፡፡ በስብከታቸው መጨረሻም የመቂን ሀገረስብከት ዳግም አመስግነው መላው ካቶሊካውያን ሕብረት ከጎናቸው እንደማይለያቸው ገልጸዋል፡፡

በቅዳሴው መጨረሻ ቤተክርስቲያን ሕንጻ ተባርኮና ተቀደሶበት አገልግሎት በመጀመሩ የተደሰቱትን የመቂ ሀገረ ስብከት ቁምስናዎች ሁሉ፣ መላው ካቶሊካዊት ሀገረ ስብከት፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ጽ/ቤት ካህናት፣ ደናግላን፣ ምዕመናን፣ የካቶሊክ አጋር ድርጅቶች በመንበረ ታቦት ፊት አመሃቸውን ለብፁዓን ጳጳሳት በማስረከብ የተሰማቸውን አጋርነት ገልጸዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ አብርሃም በበኩላቸው የመቂ ሀገረ ስበከት ባለፈው ዓመት ብዙ ፈተናዎችን አልፎ ለዚህ መብቃቱ ሁሌም ቢሆን እግዚአብሔርን ይዞ ከእርሱ ጋር በእምነት የሚጓዝ ሁሉ አሸናፊ እንደሆነ የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡ ይህ ካቴድራል ግንባታው ከ6 ዓመታት በፊት ሲጀመር ምንም የተያዘ በጀት ያልነበረው መሆኑንም አስታውሰው የሀገረ ስብከቱ ካህናት፣ ገዳማውያን/ያት፣ ምዕመናንና በሀገር ውሰጥና ውጭ ያሉ ወገኖችን ሁሉ ላበረከቱት አስትዋፅኦ አመስግነዋል፡፡ "ዛሬ በፊታችሁ ቆሜ ይህንን ካቴድራል ሳይ የሚሰማኝን ደስታ ለመግለጽ ቃላቶች ያጥሩኛል፡፡ እግዚአብሔር አሁንም ዘወትርም የተመሰገነ ይሁን" ብለዋል፡፡

በዚሁ ጊዜ የመቂ ሀገረ ስብከት ፍሬ የሆኑትን በብፁዕ ወቅዱስ ርዕቀ ሊቀ ጳጳስ ፍራንቼስኮስ የጵጵስና ማዕረግ የተሰየሙትን አባ ስዩም ፍራንሷን በሕዝብ ፊት በማቅረብ የሆሳዕና ሀገረስብከት ጳጳስ ሆነው መሰየማቸውን ሲገልጹ በስፍራው የተገኘው ሕዝብ ደስታውን በእልልታና በጭብጨባ ገልጸዋል መላ ሕዝበ እግዚአብሔር በጸሎት እንዲረዳቸው ጠይቀዋል፡፡ እንዲሁም  ከጣሊያን ከትሬንት ሀገረ ስብከት የተገኙ ጳጳስና ተወካዮች ለካቴድራሉ አማሐቸውን  አበርክተዋል፡፡ በመጨረሻም በብፁዓን አባቶች ቡራኬ ሥርዓቱ ተፈጽምዋል፡፡ በበዓሉ ላይ ብዙ ሺህ ሕዝብ የተካፈለ ሲሆን  የነበረው ሥነ ሥርዓት እጀግ አስገራሚ ነበር፡፡  የመቂ ሀገረ ስብከት በአሁኑ ሰዓት 14 ቁምስናዎች 82 ቅርንጫፍ ጸሎት ቤቶች አሉት፡፡

 








All the contents on this site are copyrighted ©.