2017-05-28 17:11:00

“ካንቺ የሚወለደው ሕጻን እርሱ ታላቅ ይሆናል፤ የልዑል እግዚአብሔር ልጅም ይባላል..."


የተወደዳችሁ አድማጮቻችን በመከታተል ላይ የምትገኙት ከቫቲካን ሬዲዮ የሚተላለፍላችሁን የአማርኛ ቋንቋ ዝግጅት ነው። ይህ የያዝነው የግንቦት ወር ከቅድስት ድንግል ማርያም ጋር በጸሎት የምንገናኝበት፣ ለእርሷ ውዳሴንና ምስጋናን የምናቀርብበት እንዲሁም ከእርሷ ሕይወት በስፋት ለመማር ጥሩ አጋጣሚ የሚፈጥርልን ወር እንደሆነ በበርካታ የክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ይታወቃል። ይህን በማሰብ ከዝግጅት ክፍላችን የተሰናዳ አጭር መልዕክት አለን፣ ቆይታችሁን ከእኛ ጋር በማድረግ እንድትከታተሉ እንጋብዛችኋለን።

የዚህን ዝግጅት ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

እግዚአብሔር የሰጠን የተስፋ ቃል፣ ይህም ለዘመናት በነቢያት አፍ ሲነገር የቆየውና በመጨረሻም ታላቅ ደስታ የሆነን መልካም ዜና የኢየሱስ ክርስቶስ መሲህ ወደ ዓለም መምጣት ነበር። ይህም  በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እውን ሆኖ አዳኛችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ። በእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ላመንን ሁላችን መዳን የምንችልበት መንገድ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ። ይህ የሚሆንበትን መንገድ አስቀድሞ በእግዚአብሔር አብ ዕቅዶች ውስጥ ስለነበር ከሴቶች ሁሉ መካከል ድንግል ማርያምን መርጧት፣ የእግዚአብሔርም ኃይል የሆነው መንፈስ ቅዱስ በእርሷ ላይ እንደሚሆንና የዓለም መድኃኒት ከእርሷ እንደሚወለድ በመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በኩል ነገራት። የቅድስት ድንግል ማርያምም መልስ፣ በሉቃስ ወንጌል፣ በምዕራፍ 1 ቁጥር 38 ላይ እንደተገለጸው፥ “እነሆ እኔ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነኝ፤ አንተ እንዳልክ ይሁንልኝ” በማለት እግዚአብሔር ይህን ለማድረግ ሃይልም፣ ስልጣንም፣ ጥበብም እንዳለው አመነች። “እኔ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነኝ” ባለች ጊዜ በእግዚአብሔር ጌትነት፣ በእግዚአብሔር ሃያልነት፣ በንጉሥነቱም  ሙሉ በሙሉ ስላመነች እንጂ ስለፈራችው አይደለም። ምንም ቢሆን ከእግዚአብሔር ዘንድ ለሚመጣ ነገር ሁሉ፣  ለእርሱ ፈቃድ ራሷን አስገዛች ወይም አዘጋጀች። በሉቃስ ወንጌል፣ በምዕራፍ 1 ቁጥር 32 ላይ መልአኩ ገብርኤል ያበሰራትን ስናነብ፥ “ካንቺ የሚወለደው ሕጻን እርሱ ታላቅ ይሆናል፤ የልዑል እግዚአብሔር ልጅም ይባላል፤ ጌታ አምላክ የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል።” በተባለች ጊዜ ከእግዚአብሔር ዘንድ የምታገኘውን ሞገስ፣ እግዚአብሔር የሚሰጣትን ክብር በእምነት ልብ ተቀበለች። ይህ ሁሉ ከሆነና ሕፃኑም ከተወለደ በኋላ የደስታ እና የምስጋና ጊዜ ሆነ።

የተወለደውን ልጇን በመልካም ሁኔታ የምታሳድግበትን መንገድ እያሰበች ሳለ ባልታሰበ መልኩ የይሁዳ ክፍለ ሀገር ንጉሥ የነበረው ሄሮድስ የሥልጣኑ ተቀናቃኝ ተወለደ ብሎ በማሰብ ኢየሱስንና ከእርሱ ጋር ሌሎችንም ሕፃናት ሊያስገድል በመነሳቱ ማርያም ከዮሴፍ ጋር ልጇን ይዛው ተሰደደች። ነገሮች ተለውጠው፣ ምንም እንኳ ወደ ቀድሞ መንደሯ መመለስ ባትችልም መኖሪያዋን በናዝሬት አደረገች። ኢየሱስም አድጎ፣ ሌላው ቢቀር በአናጺነት ሞያ ተሰማርቶ ቢረዳኝ ብላ ማርያም ብታስብም እንዳሰበችው ሳይሆን ቀርቶ፣ ኢየሱስ እናቱን ትቶአት ለማስተማር አገልግሎት ወጥቶ ሄደ። በማስተማር አገልግሎት ላይ እያለ በጠላቶቹ ተያዘና ለፍርድ ቀረበ። ለሞት የሚያበቃው ጥፋት ባይገኝበትም በግርፋት ተሰቃይቶ፣ የሚሰቀልበትን ግንድ ተሸክሞ ሲወድቅ ሲነሳ፣ በመጨረሻም ተሰቅሎ እንዲሞት ተደረገ። ይህ ሁሉ ሲሆን ማርያም በቅርብ ሆና ትመለከተው ነበር። መልአኩ ገብርኤል ባበሰራት ጊዜ “እኔ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነኝ” በማለት የእግዚአብሔርን ፈቃድ ስታስቀድም ደስታንም ቢሆን ሐዘን፣ ስደትም ቢሆን መከራ ማንኛውንም ነገር ለመቀበል ዝግጁ እንደሆነች አረጋግጣለች። መከራን፣ ስደትንና ሐዘንን በትዕግስት ልትቀበል የበቃችው፣ መጽናናትንም ያገኘችው በእግዚአብሔር ላይ ባላት የእምነት ጽናት ነው።

በመከራ፣ በስደት፣ በሐዘንና በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ስንገኝ መጽናናት እንዳለብን ከቅድስት ድንግል ማርያም እንማራለን። በፈተና ጊዜ እንዳንሸነፍ በእምነት መበርታት እንዳለብን ከቅድስት ድንግል ማርያም እንማራለን። ቅድስት ድንግል ማርያም ለእግዚአብሔር መለኮታዊ እቅድ ልባችንን ክፍት እንድናደርግ ታስተምረናለች። እግዚአብሔር አምልካችን በቸርነቱ በእርሱ ፈቃድ የምንመራበትን ልብ እንዲሰጠን፣ እንደ ቅድስት ድልግል ማርያም በእርሱ የምንመካበትን እምነት እንዲያበዛልን እንለምነዋለን።

 

ከ ዮሐንስ መኰንን








All the contents on this site are copyrighted ©.