2017-05-15 15:52:00

በዓለማችን የሚታዩ ጦርነቶች እና ግጭቶች ይወገዱ ዘንድ የመቁጠሪያ ጸሎት ማድረግ ያስፈልጋል።


በሳምንት ሁለቴ ዘወትር ረዕቡ እና እሁድ እለት በቅድሱ ጰጥሮስ አደባባይ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን እና የሀገር ጎብኝዎች በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ አማካይነት የተቅላላ አስተምህሮ እና በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ አስተንቶኖ እንደ ሚሰጥ ይታወቃል። የዚህ መርሀግብር አንድ ክፍል በሆነው በትላንትናው እለት ማለትም በግንቦት 6/2009 ዓ.ም. ቅዱስነታቸው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ያደረጉት አስተንትኖ ትኩረቱን አድርጎ የነበረው ባሳለፍነው ሳምንት ማገባደጃ በግንቦት 4 እና 5/2009 ዓ.ም. በፖርቱጋል ሀገር ፍጢማ ተብሎ በሚጠራው ልዩ ስፍራ የሚገኘውን የመቁጠሪያይቱ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ቤተ መቅደስ ለሁለት ቀናት ያህል አድርገውት የነበረውን 19ኛው ሐዋሪያዊ ጉዞዋቸው ላይ ያተኮረ እንደ ነበር ለመረዳት ተችልዋል።

የዚህን ዜና ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

ቅዱስነታቸው “የሰማይ ንግሥት ሆይ ደስ ይበልሽ፣ እንደ ተናገረው ከሙታን ተንሰቱዋልና” የሚለውን ጸሎት ከምዕመናን ጋር በመቀባበል ከመድገማቸው በፊት በፋጢማ የመቁጠሪያይቱ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ቤተ መቅደስ ያደረጉትን የሁለት ቀን ቆይታ አስመልክተው እንደ ገለጹት “በፋጢማ በነበረኝ ቆይታ አማኝ በሆኑ ቅዱሳን ምዕመናን ጸሎት ውስጥ ተጥለቅልቄ ነበር” ካሉ ቡኃላ ይህም ለአንድ መቶ አመታት እንደ ወንዝ ውሃ ይፈስ የነበረው ጸሎት የማሪያምን እናታዊ ጥበቃን ለዓለም ያስገኘ ነበር” ማለታቸው ተገልጹዋል።

በእለቱ ቅዱስነታቸው ያሰሙት አስተንትኖ በተለየ ሁኔታ ትኩረቱን አስድርጎ የነበረው በፋጢማ የመቁጠሪያይቱ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ቤተ መቅደስ በወቅቱ የነበረውን “የሱባሄ እና የአስተንትኖ መንፈስ” ላይ ያደረገ እንደ ነበረም ተወስቱዋል። በእነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች ውስጥ  አሉ ቅዱስነታቸው “ከሙታን የተነሣው ጌታ በቃል እና በቅዱስ ቁርባን አማክይነት በጣም ብዙ ሊባሉ በሚችሉ የፋጢማ የመቁጠሪያይቱ ማሪያም ወዳጆች መካከል ነበር” ብልመዋል።

ቅዱስነታቸው የፋጢማን የመቁጠሪያይቱ እመብቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያምን ቤተ መቅደስ በጎበኙበት ወቅት በግንቦት 5/2009 ዓ.ም. በእርሳቸው መሪነት ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ የቅድስትና ማዕረግ የተሰጣቸው ሁለት አዳጊ ሕጻናት ወንድም እና እህት የሆኑት ቅዱስ ፍራንቸስኮ እና ዣሽንታ ማርቶ በተመለከተ “በወቅቱ የነበራቸውን ለክርስቶስ የመገዛት ስሜት እና ወንጌላዊ ምስክርነት በዓለም ውስጥ የሚገኙ አብያተ ክርስትያናት ሁሉ ይህንን አብነት ይከተሉ ዘንድ ጥሪ አደርጋለሁ፣ በተጨማሪም ሁሉም አብያተ ክርስትያናት ሕጻናት ያላቸው ዓይነት ልብ ይኖራቸው ዘንድም በድጋሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ” ብለው እንደ ነበረም ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል። 

የእነዚህ ሁለት ሕጻናት ቅድስና “የማሪያምን ግልጸት ተከትሎ የመጣ አይደልም” በማለት አስተንትኖዋቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ነገር ግን በወቅቱ ለግልጸቱ አሳይተውት ለነበረው ታማኝነት እና በመንደሩ የነበሩ ሰዎችን በማሳመን እና ጉጉት እንዲኖራቸው በማድረግ የማሪያምን ግልጸት የመንደሩ ነዋሪዎችም ጭምር እንዲቋደሱ በማድረጋቸውና በዚህም ረገድ ከፍተኛ የተባለ ሥራ በመሥራታቸው ጭምር ነው” ብለዋል።

እነዚህ የማሪያም ራእይ ወይም ግልጸት ተቋዳሽ የነበሩ ሦስት አዳጊ ሕጻናት ማሪያም ከተገለጸችላቸው ቡኃላ አዘውትረው የመቁጠሪያ ጸሎት ይደግሙ ነበር፣ ንስኃ በመግባትም የመጀመሪያ የዓለም ጦርነት ያበቃ ዘንድ መስዋዕት ያቀርቡ እንደ ነበረም በመግለጽ አስተንትኖዋቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው በተለይም ደግሞ የእግዚኣብሔር መለኮታዊ ምሕረት እጅግ ለሚያስፈልጋቸው ነብሶች ሁሉ ሳያቋርጡ ጸሎት ያደርጉ ነበር ብለዋል። “አሁንም ቢሆን በእኛ ዘመን መንፈሳዊ የሆነ ለውጥ ይመጣ ዘንድ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ጸሎት እና ሱባዔ ማድረግ ያስፈልጋል” በማለት አስተንትኖዋቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው በተጨማሪም አሁን በምንገኝበት ዘመን በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚታዩት የሰውን ልጅ ሕይወት የሚያጠፉ እና የሚያጠለሹ እጅግ ክፉ የተባሉ ብዙ ጦርነቶች ማብቂያ ያገኙ ዘንድ ጸሎታችንን እና ሱባዔን አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በስተንትኖዋቸው ማጠቃለያ ላይ እንደ ገለጹት “ከፋጢማ የመቁጠሪያይቷ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም የሚመነጨው ብርሃን ሕይወታችንን ይመራው ዘንድ እንፍቀድለት” ካሉ ቡኃላ “የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማሪያም ንጹሕ የሆነ ልብ መጠጊያችን፣ መሸሸግያችን እና ወደ ክርስቶስ የሚመራን እንዲሆን እጸልያለው” ካሉ ቡኃላ ለእለቱ ያዘጋጁትን አስተንትኖ አጠናቀዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.