2017-05-01 15:46:00

ር. ሊ. ጳ. ፍራንቸስኮ እና የግብፅ የኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን ር.ሊጳ ቴውድሮስ ዳግማዊ የጋራ የስምምነት ሰነድ ተፈራረሙ።


በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕስ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራቸስኮ እና በግብፅ የኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በሆኑት ቴውድሮስ ዳግማዊ መካከል ለመጀመሪያ ጊዜ አንዱ ቤተ ክርስቲያን በሌላኛው ቤተ ክርስቲያን የሚሰጠውን ምስጢረ ጥምቀት እውቅና ሰጥተው ይህንንም እውቅና በተፈራረሙት የጋራ ሰነድ ማረጋገጣቸው ተገለጸ። ይህም ማለት ለምሳሌ በኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተጠመቀ አንድ ሰው የካቶሊክ ምዕመን ለመሆን ቢፈልግ ወይም አንድ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተጠመቀ ሰው የኮፕቲክ ምዕመን ለመሆን ቢፈልግ አንዱ ቤተ ክርስቲያን በሌላኛው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚፈጸመውን ምስጢረ ጥምቀት እውቅና በመስጠቱ የተነሳ ይህ ሰው በድጋሜ የመጠመቅ ግዴታ የለውም ማለት ነው።

የዚህን ዘገባ ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመቻን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

ይህም የጋራ ስምምነት ይፋ የሆነው በሚያዝያ 20/2009 ዓ.ም. ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ እና የግብፅ የኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የሆኑት ቴውድሮስ ዳግማዊ በግብፅ በተገናኙበት ወቅት ነው። ይህ በሁለት ታላላቅ አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች መካከል የተደረገው ግንኙነት ከዛሬ 44 ዓመታት በፊት እንደ አውሮፓዊያኑ የቀን አቆጣጠር በግንቦት ወር 1973 ዓ.ም. በወቅት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነበሩት በጳውሎስ ስድስተኛ እና በኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነበሩት ሼኑዳ 3ኛ መካከል ከተደረገው ግንኙነት በመቀጠል የተደረገ ግንኙነት በመሆኑ ታሪካዊ ያስብለዋል።

ይህ በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ እና የኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በሆኑት ቴውድሮስ ዳግመኛ መካከል የተደረገው ግንኙነት ለክፍለ ዘመናት በሁለቱ አበይት አብያተ ክርስቲያናት መካከል የነበረውን ልዩነት ለማስወገድ የተደረገ ታሪካዊና ከፍተኛ የሆነ ጥረት ውጤታማ መሆኑን የሚያሳይ ታሪካዊ ግንኙነት እንደ ሆነም ጨምሮ የተገለጸ ሲሆን ይህም በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት የጋራ የስነ መለኮት ኮሚቴዎችን በማዋቀር ከፍተኛ የሆነ ውይይት በማድረግ የተገኘ ውጤት መሆኑም ለመረዳት ተችሉዋል።

የሁለቱ ታላላቅ አባያተ ክርስቲያናት መሪዎች ይህንን የጋራ ስምምነት በተፈራረሙበት ወቅት እንደ ገለጹት ሁሉቱ አብያተ ክርስቲያናት የሚጋሩት መሠረታዊ የሆኑ የእምነት አስተምህሮችን በጸሎት ለማዳበር እንደ ሚፈልጉም ጨምረው ገልጸዋል። በተለይም ጌታ ለሐዋሪያቱ ያስተማረውን “አባታችን ሆይ የሚለውን” ጸሎት ሁለቱም አብያተ ክርስቲያናት በሚያስማማ መልኩ የጋራ የሆነ ትርጉም እንዲኖረው እና የፋሲካን በዓል በተመሳሳይ ቀን ይከበር ዘንድ ሁኔታዎች እዲመቻቹ እና ጥናት እንዲደረግም ጥሪ አቅርበዋል። የካቶሊክ እና የኮፕቲክ አብያተ ክርስቲያናት ጋብቻ እና ቤተሰብ ቅዱስ መሆናቸውን እና ተፈጥሮ ለለገሰችን ስጦታዎች እንክብካቤ ማድረግ የሚሉትን የሰው ልጅ እሴቶችን በተመለከተ የጋራ የሆነ አቋም ያላቸው መሆኑን ጠቁመው እነዚህን የጋራ እሴቶች በጋራ መመስከር እንደ ሚጠበቅባቸውም በስምምነቱ ወቅት ተገልጹዋል። ይህ የጋራ የስምምነት ሰንድ አክሎ እንደ እንደ ሚገልጸው በግብፅ እና በመካከለኝእው ምስራቅ በሚገኙ ክርስቲያኖች ላይ በእምነታቸው ምክንያት ብቻ እየተፈጸመ የሚገኘውን ስደት እና ግድያ በመቃወም የተጀመረውን ጸሎት አጠናክረው መቀተል እንደ ሚኖርባቸውም ያትታል።

ይህ የጋራ የመግባቢያ ሰንድ በካቶሊክ እና በኮፕቲክ አብያተ ክርስቲያናት መካከል የወጥረት ምንጭ ሆነ የቆየውን ከአንዱ ቤተ ክርስቲያን ወደ ሌላኛው እመንት የሚቀይሩ ክርስቲያኖች በድጋሚ ይጠመቁ የሚለውን ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ የነበረው ጉዳይ መቅረፍ የቻለ ሰንድ መሆኑም ተገልጹዋል።

ክቡራን እና ክቡራት ታዳሚዎቻችን  የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕስ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ እና የግብፅ የኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የሆኑት ቴውድሮስ ዳግማዊ በሚያዝያ 20/2009 ዓ.ም. የሁለቱን አብያተ ክርስቲያናት ግንኙነት አስመልክተው የተፈራረሙትን ሰንድ ሙሉ ይዘት ከመጭው ረዕቡ ጀምሮ በተከታታይ ወደ እናንተ እንደርሳለን እንድትከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።








All the contents on this site are copyrighted ©.