2017-04-19 16:59:00

ብፁዕ ካርዲናል ማራዲያጋ፥ ሙስናና ምግባረ ብልሽት ይብቃ ወደ እግዚአብሔር እንመለስ


በሆንዱራስ የተጉሲጋልፓ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ኦስካር ሮድሪገዝ ማራዲያጋ እ.ኤ.አ. ሚያዝያ 16 ቀን 2017 ዓ.ም. በበዓለ ፋሲካ ምክንያት ባሳረጉት መሥዋዕተ ቅዳሴ፤ በሆንዱራስ በመታየት ላይ ያለው ዓመጽና ምግባረ ብልሽት አገሪቱ ማኅበራዊ ኅብረ ህዋስ ውስጥ እጅግ ሰርጾ ሰብአዊና ማኅበራዊ ቸነፈር ሆኖ ያለው እንዲያበቃለት፡ ያስተሳሰብ ያኗኗር ትንሣኤ ያለው አስፈላጊነት ገልጠው፥ “በዚህ ዓይነቱ በሙስናና በግብረ ብልሽት በጨቀየው ሕይወት ውስጥ ተነክረን መኖሩ ያብቃለት። ዓመጽና ምግባረ ብልሽት ተለማምዶ መኖር ያብቃለት” እንዳሉ ፕረንሳ የተሰየመው የአገሪቱ ዕለታዊ ጋዜጣ ባወጣው ኅትመቱ አስነብቧል።

የሰማይ ሃብትን እንጂ ምድራዊ ሃብት ከመሻት መቆጠብ

የተጉሲጋልፓ ሊቀ ጳጳስ ባስደመጡት ስብከት፥ ሁሉም የሰማይ ሃብትን እንጂ ምድራዊ ሃብትን ከመሻት እንዲቆጠብ አደራ ሲሉ፥ “ምክንያቱም ወደ ዘለዓለማዊ ሕይወት የሚገባ ሰው በምድር ያከማቸው ሃብት ይዞ አይገባም፡ ስለዚህ ንብረት ሃብት በማካበት እግዚአብሔን በመርሳት ተምሳያችን የሆነውን ሁሉ ዘንግተን በአመጽ ይሁን በሙስና በምግባረ ብልሽት ሃብት ማካበት ብሎ ይኸንን መንገድ መርጦ መኖር ጥፋት ነው። ወደ እግዚአብሔር እንመለስ። ካልሆነ ወደ ስርዓት አልቦነት ወደ ጥላቻ ወደ ቂም በቀልና ወደ ሞት መመለስ ነው የሚሆነው፡ ወደ አዲስ ሕይወት እንነሣ” እንዳሉ ጋዜጣው ዘግቧል።

የፍጻሜው ቃል የሞት ስልጣን ሳይሆን የዚያ ሕይወት የሆነው የእግዚአብሔር ነው

“ክርስቶስ በሞት በሐጢአትና በኢፍትሓዊነት ላይ ድል ነስቶ ተነሣ” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ማራዲያጋ አክለው፥

“የፍጻሜው ቃል ኃይለ ሞት የሐጢአት የእኔነትና ለእኔ ባይነት የሙስና የምግባረ ብልሽት ሌላው የማግለል ድኾችን ጨርሶ የማጥፋት ኃይል ሳይሆን የትንሣኤ ኃይል ነው። ኃይሉም የዚያ የሕይወት ጌታ የሆነው የህያው እግዚአብሔር ቃለ ምህረትና የተስፋ ቃል ነው። የእኛ ኃላፊነት በዚያ የጭለማ ሥፍራ ሁሉ የክርስቶስ ብርሃን በዚያ የተነጠሉት በሚገኙበት አዘቅት ሁሉ የክርስቶስ ትንሣኤ ማወጅ ነው”

በማለት ያስደመጡት ስብከት ማጠቃለላቸው የሆንዱራስ ፕረንሳ የተሰየመው ዕለታዊ ጋዜጣ አስነብቧል። 

 







All the contents on this site are copyrighted ©.