2017-04-03 15:54:00

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ "ክርስቲያኖች የሕይወት እና የተስፋ ምስክሮች መሆን ይገባቸዋል" ማለታቸው ተገለጸ።


ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በትላንትናው እለት ማለትም በመጋቢት 24/2009 ዓ.ም. በሰሜናዊ ጣሊያን በሞደና ክልል በምትገኘው በካፕሪ ከተማ ተገኝተው የአንድ ቀን ሐዋሪያዊ ጉብኝት ማድረጋቸው ተገለጸ። ቅዱስነታቸው የአንድ ቀን ሐዋሪያዊ ጉብኝት ለማድረግ ወደ ሥፍራው የተጓዙት ከዛሬ አምስት አመት በፊት በኤሚሊአ ሮማኛ ክልል ከፍተኛ የሆነ የመሬት መቀጥቀጥ አደጋ ደርሶ ከፍተኛ የሆነ ጉዳት አስከትሎ የነበረ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን በአደጋው ምክንያት የፈራረሱትን የመሰረተ ልማት እና የምኖሪያ ቤቶችን ለመጠገን እየተደረገ ያለውን ከፍተኛ ጥረት ለመጎብኘት ታስቦ የተደረገ ጉብኝት መሆኑም ጨምሮ ተገልጹዋል።

የዚህን ዜና ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

በእለቱ ቅዱስነታቸው በካርፒ ከተማ አደባባይ ለተሰበሰቡ ከሰባ ሺ በላይ ለሚሆኑ ምዕመናን በእርሳቸው መሪነት ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት እንደ ገለጹት “ክርስቲያኖች በእግዚኣብሔር እርዳታ ተብትቦ ከያዛቸው የሕይወት ፍርስራሽ ውስጥ በመውጣት ሕይወታቸውን በአዲስ መልኩ መገንባት ይገባቸዋል” ማለታቸውም ተገለጸ።

ቅዱስነታቸው በስበከታቸው መጀመሪያ ላይ እንደ አውሮፓዊያኑ የቀን አቆጣጠር በ2012 በደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ወዳጅ ዘመዶቻቸውን እና ነብረቶቻቸውን በአደጋው ላጡ ወገኖች እንደ ገለጹት “እግዚኣብሔር የሚከሰቱትን ክፉ የሚባሉ ነገሮች ሁሉ ምዕታታዊ በሆነ መልኩ አያጠፋቸው፣ ነገር ግን በስቃይ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ሁሉ በእምነት አማክይነት እግዚኣብሔር ቀርቦአቸው እንደ ምያጽናና” ገልጸዋል።

በእለቱ በላቲን ስርዓተ አምልኮ አቆጣጠር በአምስተኛው የዓብይ ጾም ሰንበት በተነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ (ዩሐንስ 11:1-45) በተጠቀሰው “የአልዓዛርን ከሞት መነሳት” በሚያወሳው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ መሰረቱን ባደረገው ስብከታቸው ቅዱስነታቸው እንደ ገለጹት ኢየሱስ ራሱ አልዓዛር በመሞቱ የተነሣ አልቅሶ እንደ ነበር አስታውሰው “በስቃይ ውስጥ በምንገኛባቸው ወቅቶች ሁሉ ከስቃያችን ብዛት የተነሳ አስተዋይነታችንን እናጣለን” ካሉ ቡኃላ ኢየሱስም ቢሆን ከዚህ ዓይነቱ ስሜት ውጭ አልነበረም ብለዋል።

“አልዓዛር በተቀበረበት የመቃብር ሥፍራ በአንድ ወገን ተስፋ የመቁረጥ፣ የሐዘን እና ግራ የመጋባት መንፈስ ነበር፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሞትን እና ክፉ ነገርን ማሸንፍ የምችል ተስፋ ይታይ ነበር” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “ኢየሱስ የፈጸመው ተግባር ሕይወትን የማራዘም ተግባር ተደርጎ መቆጠር፣ በአንጻሩ ግን ኢየሱስ ይህንን ተግባር የፈጸመው “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፣ በእኔ የሚያምን ቢሞት እንኳን በሕይወት ይኖራል” የሚለውን መግለጽ ስለፈለገ የፈጸመው ተግባር መሆኑን ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል።

ቅዱስነታቸው ስብከታቸውን በቀጠሉበት ወቅት እንደ ገለጹት “በሐዘን ወይም ደግሞ በተስፋ ውስጥ ከእነዚህ ሁለት ነገሮች በየተኛው ወገን መሰለፍ እንደ ምንፈልግ መወሰን ይገባናል” ያሉት ቅዱስነታቸው በሕይወት ፍርስራሽ ውስጥ ተቀብረው የሚገኙ ሰዎች አሉ፣ እንደ እናንተ የመሰሉት ደግሞ በእግዚኣብሔር እርዳታ ከፍርስራሽ ውስጥ በመውጣት የመልሶ ግንባታን በማከናወን ትገኛላችሁ ብለዋል።

ቅዱስነታቸው የዛሬ አምስት አመት ገደማ በኤሚሊአ ሮማኛ ክልል በደረሰው ከፍተኛ የመረት መንቀጥቀጥ አደጋ ዘመድ አዝማዶቻቸውን እና ንብረቶቻቸውን ያጡ ከሰባ ሺ በላይ የሚገመቱ ምዕመናን በታደሙበት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን በስብከታቸው አጽኖት ሰጥተው እንደ ገለጹት ተስፋ በመቁረጥ ራሳቸውን ሐዘን ውስጥ በመክተት፣ በፍርሃት እና በተስፋ በቆረጠ ስሜት ምንም ዓይነት ፋይዳ የለኝም ወደ ምለው አመክንዮ በፍጹም መግባት የለባቸችሁም ብለዋል።

“ኢየሱስ ለአልዓዛር የተናገራቸው ቃላት ለእኛም ትርጉም ሊሰጡን ይገባል” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “ሐዘንን እና ተስፋ መቁረጥ ሁሉ ከኃላችን ጥለን፣ ኢየሱስ የሚሰጠን ተስፋ አንደ አዲስ እንድነወለድ እና ሐዘናችንን ወደ ደስታ የመቀየር አቅም አለው፣ ከወደቅንበትም እንድንነሣ ይረዳናል” ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በስብከታቸው ማገባደጃ ላይ እንደ ገለጹት “ተስፋን ለተጠማው ዓለማችን ሕይወት መስካሪዎች ሁነን እንድንገኝ ፀጋውን ይሰጠን ዘንድ እግዚኣብሔርን እንጠይቀው” ካሉ ቡኃላ ለእለቱ ያዘጋጁትን ስብከት አጠናቀዋል።

በሰሜናዊ ጣሊያን የሚገኘው የኤሚሊያ ሮማኛ ክልል እንደ አውሮፓዊያኑ የቀን አቆጣጠር 2012 የዛሬ 5 አመት ገደማ  በመሬት መንቀጥቀጥ መልክያ መሣሪያ በሬክተር እስኬል 6.1 ያስመዘገበ ክፍተኛ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ መድረሱ የሚታወስ ሲሆን በወቅቱም 28 ሰዎች በአደጋው ሕይወታቸውን ማጣታቸውም የሚታወቅ ሲሆን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በትላንትናው እለት ማለትም በመጋቢት 24/2009 ዓ.ም. በስፍራው ተገኝተው ያደርጉት የአንድ ቀን ሐዋሪያዊ ጉብኝት በስፍራው እየተካሄደ የሚገኘውን የመልሶ ግንባታ በጣም አምርቂ እና በተመሳሳይ መልኩም ለተጎዱ አከባቢዎች በምሳሌነት የሚጠቀስ ተግባር በመሆኑ የተነሳ ለእዚህ ታላቅ ለሚባል ተግባር ምስጋናን ለማቅረብና በአደጋው ሰለባ የሆኑ ሰዎችን ለማጽናናት ታቅዶ የተደረገ  የአንድ ቀን ሐዋሪያዊ ጉብኝት እንደ ነበረም ተያይዞ የደረሰን ዜና ያመለክታል።

 








All the contents on this site are copyrighted ©.