2017-03-26 16:26:00

የስድስተኛው ዓብይ ጾም ቃለ እግዚኣብሄር በክቡር አባ መብራቱ ኃይሌጊዮርጊስ።


የተከበራችሁ የእግዚኣብሔር ቤተሰቦች እና በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!

እግዚኣብሔር አባታችን፣ በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሁም አጽናኝ እና ጠባቂያችን በሆነው በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ከክፉ ነገሮች ሁሉ ሰውሮን፣ እንደ መልካምነታችን ሳይሆን በምሕረቱ ጎብኝቶን ለዛሬው ቀን እንድንደርስ ስለረዳን ለእርሱ ለዘልዓለም ክብር እና ምስጋና ይሁን!

የዚህን ስብከት ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

በዛሬው እለት ሰንበት በስድስተኛው የዓብይ ፆም ሣምንት ውስጥ እንገኛለን። በዚህ ሰንበት አስተንትኖ እንድናደርግባቸው ቤተ ክርስቲያናችን የሰጠችን የእግዚኣብሔር ቃል መቅድሚያ የተወሰደው ሐዋሪያው ጳውሎስ ወደ ጢሞቴዎስ በጻፈው ሁለተኛ መልእክቱ 2:1-15 ላይ “የክርስቶስ መልካም ወታደር በመሆን መከራን መቀበል” የሚለው ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ከመጀመሪያው የሐዋሪያው የጴጥሮስ መልእክት 5:1-11 የተወሰደው “የእግዚሓብሔርን ሕዝብ ለማስተዳደር የተሰጠ መመሪያን” የሚመለከት ነው። የዛሬ ሰንበት ቅዱስ ወንጌል ደግሞ ከማቴዎስ 25:14-30 ላይ የተወሰደ “የሦስቱ አገልጋዮች ምሳሌ” ላይ ያተኮረ ነው።

በዛሬው እለት በስድስተኛው የዓብይ ፆም ሳምንት ላይ እንገኛልን። ፃም ወደ እግዚኣብሔር እና ወደ መንግሥቱ እንድንጓዝ የሚመራን መንግድ ነው እንጅ ጾም በራሱ ግብ አይደለም። ፆማችን በዛሬው እለት የተነበቡልንን የእግዚኣብሔር ቃል በተግባር በመተርጎም የክርስቶስ መልካም ወታደር፣ የእግዚኣብሔርን ሕዝብ በትህትና እንድናገለግል እንዲሁም መልካም የጌታ አገልጋይ በመሆን የተሰጠንን መክሊት በመጠቀም ፍሬ እንድናፈራ ጉልበት እና ኃይልን የሚያጎናጽፈን መሣሪያ ነው ፆም።

የእግዚኣብሔር መንግሥት መቼ እንደ ሚመጣ ስለማናውቅ ሕይወታችንን ጥበብ በተሞላው መልኩ መኖር ይገባናል። ዛሬ በተነበበልን ቅዱስ ወንጌል እንደ ሰማነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሦስቱን አገልጋዮች ምሳሌ በመጠቀም እነዚህ ሦስት አገልጋዮች ከጌታቸው በአደራ ንብረት እንደ ሰጣቸው ይተርክልናል። ይህም ንብረት እግዚኣብሔር አባታችን ለእኛ ለልጆቹ በአደራነት የሰጠንን ምክሊት ያመለክታል። ይህንን መክሊት እግዚኣብሔር ለእያንደንዳችን የሰጠን፣ ተጠቅመንበት ፍሬያማ እንድናደርገው ነው።

እያንዳንዳችን ከእግዚኣብሔር የተለያዩ ዓይነት ፀጋዎችን ተቀብለናል። ሕይወታችን፣ እምነታችን፣ መኖራችን፣ ደስታችን በእየ እለቱ የምናከናውናቸው ተግባሮች ሳይቀሩ ከእግዚኣብሔር የተሰጡን ነጻ የፀጋ ስጦታዎች ናቸው። እኛ ግን እነዚህን ነጻ የፀጋ ስጦታዎችን ብዙን ጊዜ በማስተዋል እና በጥበብ ስንጠቀምባቸው እና ፍሬ እንዲያፈሩ ስናደርጋቸው አንታይም።

ሕይወት በየደረጃው ብዙ ተጨማሪ የፀጋ ስጦታዎችን የምናገኝበት ሂደት ነው። ስለዚህም በእየ እለቱ የሚሰጡን የፀጋ ስጦታዎች፣ የሚሰጡን በነጻ ከሆነ እነዚህን ስጦታዎች ለግላችን ጥቅም ብቻ እንዲውሉ ማድረግ ግን ተገቢ አይደለም። ማስታወስ የሚገባን ትልቁ እውነታ ሊሆን የሚገባው እነዚህን አምላካችን የሰጠንን የፀጋ ስጦታዎች ሁሉ ወደ እርሱ ክብር እንድናቀና የሚመሩን ስጦታዎች ሊሆኑ ይገባል። እነዚህ የተሰጡን መክሊቶች ሊባዙ እና ፍሬ ሊያፈሩ ይገባል። ምክንያቱም በመጨረሻው ቀን በአደራና በእምነት ከሰጠን አምልካችን ጋር ሒሳብ ማወራረዳችን አይቀሬ ነው። በመጨረሻው ቀን እግዚኣብሔር በአደራ እና በእምነት የሰጠንን መክሊት ፍሬ ማፍራቱን ወይም አለማፍራቱን ይጠይቀናል። እግዚኣብሔር ለእያንድአንዳችን የሚሰጠን ስጦታ እንደ እየአቅማችን በቁጥር እና በዓይነት ይለያያል። ምን አልባትም ለአንዱ አምስት፣ ለሌላው ደግሞ ሦስት ወይም አንድ መክሊት ብቻ ሊሰጥ ይችላል። ዋናው ነገር የመክሊቱ መብዛት ወይም ማነስ ሳይሆን በእግዚኣብሔር የሚገመገመው፣ ነገር ግን በአንጻሩ ትርፋማ መሆን አለመሆኑ ነው የሚገመገመው። እነዚህ ከእግዚኣብሔር የተሰጡን መክሊቶች በገንዘብ ሊተመኑ የማይችሉ ውድ የፀጋ ስጦታዎች ናቸው። እያንዳንዱ ሰው ለተቀበለው መክሊት ከፍተኛ ሐላፊነት ተሰጥቶታል። ስለዚህም እያንዳንዳችን ይህንን የተሰጠን መክሊት ከእጆቻችን ሾልኮ እንዳይወጣ መንከባከብ እና እንዲበረክት ማድረግ ይገባናል። ይህንን ስናደርግ ብቻ ነው በመጨረሻው ቀን በአምልካችን ፊት ለፍርድ በምንቀርብበት ወቅት “አንተ ታማኝ እና ደግ አገልጋይ! በጥቂት ነገር ታማኝ ሆነህ ስለተገኘህ በብዙ ነገር ላይ እሾምሃለው” (ማቴዎስ 25:21) የሚለውን የአምላካችንን ድምጽ መስማት የምንችለው። ለምናሳየው ታማኝነት የሚከፈለን ካሳ ግን በምንም ዓይነት ሁኔታ ከሠራነው ሥራ ጋር ሊነጻጸር የማይችል ትልቅ ስጦታ ነው የሚሰጠን። ይህም ለዘልዓለም ከአምላክችን ጋር እንድንኖር የሚሰጠን የፀጋ ስጦታ ነው።

ዛሬ ኢየሱስ በወንጌል በምሳሌነት ያቀረበልን የሦስቱ አገልጋዮች ታሪክ በጣም ውብ እና የእያንድአንዳችንን ሕይወት የሚወክል ታሪክ ነው። እያንድአንዳችን ሌላውን ሰው ለመምሰል የምናልመውን ሕልም እና የምናደርገውን ሩጫ አቁመን ራሳችንን ለመሆን መሞከር ይገባናል። እያንድአንዳችን ከእግዚኣብሔር አባታችን የተፈጥሮን ፀጋ እና እምነትን ተቀብለናል። ስለዚህም በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል፣ ትርፋማ ልናደርገውም ይገባል፣ የአኗኗር ዘይቤአችንን በመቀየር ለዘላለም ሕይወት ተገቢ የሚያደርገንን ዓይነት ሕይወት በመኖር ምክሊታችንን ፍሬያማ ማድረግ ይጠበቅብናል።

በወንጌል ውስጥ እንደ ተጠቀሰው ሕይወት ለአንድ ክርስቲያን የተሰጠ ተልዕኮ ነው። ስለዚህም ይህንን ሕይወታችን  በእየለቱ ለራሳችን እና ለባልንጀሮቻችን ፍሬ ያፈራ ዘንድ የተቻለንን ማድረግ ይጠበቅብናል። ይህንንም አቅማችን በፈቀደው መልኩ በተግባር በምንመነዝርበት ወቅቶች ሁሉ ከእግዚኣብሔር አባታችን በርከት ያሉ ሽልማቶችን እናገኛለን።

በተለይም በዚህ በጾማችን ወቅት የተሰጡንን የእመነት፣ የጸሎት እና የፍቅር ስጦታዎችን ተጠቅመን እነዚህ መክሊቶቻችን ፍሬያማ እና ትርፋማ እንዲሆን የምንተጋበት ወቅት ሊሆን ይገባል። በዚህ የጾማችን ወቅት መክሊታችን ፍሬ እንዳያፈራ የሚያግዱንን የስንፍና ተግባራትን ሁሉ አውልቀን የምንጥልበት ወቅት ሊሆ ይገባል። ምክንያቱም ጌታችን ዳግም በሚመጣበት ወቅት ሕሳባችንን ለማወራረድ የግድ በእርሱ ፊት መቆማችን አይቀሬ ነው። ጌታችን በእያንዳንዳችን መዳፍ ውስጥ በኃላፊነትና በአደራነት ያስቀመጠልንን መክሊት የመከባከቢያ ጊዜ ሊሆን ይገባል የጾም ወቅት። የተሰጡንን መክሊቶች ብቻ ጠብቀን መቆየትም አያዋጣም። ትርፋማ እንዲሆኑ ማድረግ ነው የሚገባን። ልክ አንድ ነጋዴ የሚነግደው ትርፍ ለማግኘት እንደ ሆነ ሁሉ፣ እኛም የተሰጠን የክርስትና ሕይወት ለራሳችን ኑረን እንድናልፍ ብቻ ሳይሆን ኑረን ሌሎችን ማኖር እንድንችል የተቀበልነው የፀጋ ስጦታ በመሆኑ የተነሳ ወንድምና እህቶቻችንን የማገልገል መንፈሳዊ፣ ግብረገባዊ እና ሰባዊ ኃልፊነትን እግዚኣብሔር ሰጥቶናል ።

 

የተወደዳችሁ የእግዚኣብሔር ቤተሰቦች እና በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሰዎች ሁሉ!

በዚህ በስድስተኛው የዓብይ ጾም ሳምንት ወደ ራሳችን በመመለስ በሕይወታችንና በአኗኗር ዘይቤአችን ላይ ግምገማ በማድረግ ግለ ሂሲ የምናደርግበት ወቅት ሊሆን ይገባል። “የክርስቶስ መልካም ወታደር በመሆን መከራን መቀበል የምንዘጋጅበት ወቅት ሊሆንም ይገባል። የእግዚሓብሔርን ሕዝብ ለማስተዳደር የተሰጠን ኃልፊነት በጥንቃቄ መወጣት ይጠበቅብናል።

እግዚኣብሔር አባታችን በመጨረሻው ቀን “አነተ ታማኝና ደግ አገልጋይ! በጥቂት ነገር ታማኝ ሆነህ ስለተገኘህ በብዙ ነገር ላይ እሾምሃለው!” የሚለውን ድምጹን መስማት የሚይስችለንን መልካም ተግባራትን በመፈጸም፣ መክሊታችን ፍሬያማ ይሆን ዘንድ እናታችንና የክርስቲያኖች ሁሉ ረዳት የሆነችው እመቤታችን ቅድስት ማሪያም በአማላጅነቷ ትረዳን ዘንድ ልንማጸናት ይገባል።

የሰማነውን በልቦናችን ያሳድርልን።

አሜን!!

 








All the contents on this site are copyrighted ©.