2017-03-07 10:35:00

ር.ሊ. ጳጳሳት ፍራንቸስኮ "“የዐብይ ጾም ወቅት ከክፉ መንፈስ ነፃ የምንሆንበት ወቅት ነው" አሉ።


ክቡራን እና ክቡራት ታዳሚዎቻችን ዐብይ ጾምን በተመለከተ በተከታታይ የተለያዩ አስተምህሮዎችን ወደ እናተ እያቀረብን መሆናችን ይታወቃል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ የላቲን ሥረዓት ተከታይ የሆኑ የካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት በየካቲት 22/2009 ዓ.ም. ዐብይ ጾምን በይፋ በጀመሩበት ወቅት ቅዱስነታቸው በእለቱ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት “የዐብይ ጾም ወቅት ከሚያጎድፈን እና ያልተገባን እንድንሆን በማድረግ የእግዚኣብሔር ልጆች የመሆን መብታችንን የሚነፍጉንን ነገሮች ሁሉ በምሕረት ድል እንድናደርግ የሚረዳን ወቅት ነው” የዐብይ ጾም ወቅት ብለዋል።

የእዚህን ዜና ሙሉ ይዜት ከእዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመንካት ማዳመጥ ትችላላችሁ!

በዛሬው ዝግጅታችን ቅዱስነታቸው በእለቱ ያሰሙትን ስብከት ሙሉ ይዘት እናቀርብላችኋለን እንድትከታተሉ ከወዲሁ እንጋብዛለን።

አሁንም ቢሆን በጾም፣ በለቅሶና በሐዘን በፍጹም ልባችሁ ተመለሱ ይላል እግዚኣብሔር፣ ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ” (.ኢዩኤል 2:12) ነቢዩ ኢዩኤል ይህንን ጥሪ ለሕዝቡ በእግዚኣብሔር ሥም ያቀርባል።  “ሕዝቡን ሰብስቡ ጉባሄውን ቀድሱ፣ ሽማግሌዎችን በአንድነት አቅርቡ፣ ሕጻናትን ሰብስቡ፣ ጡት የሚያጠቡትን አታስቀሩ፣ ሙሽራው እልፍኙን ይተው፣ ሙሽሪትም የጫጉላ ቤቷን ትተው” (. ኢዩኤል 2:16) በማለት ማንም ሰው ከእዚህ ጥሪ ውጭ ሊሆን እንደ ማይገባ ያሳስበናል። ሁሉም ምዕመናን ጌታቸውን እንዲያመልኩወደ አምላካችሁ ወደ እግዚኣብሔር ተመለሱ እርሱ መሓሪና ርኅሩኅ ቁጣው የዘገየና ፍቅሩ የበዛ ክፉ ነገር ከማምጣትም የሚታገስ ነውና” (.ኢዩኤል 2:13) በማለት ነቢዩ ጥሪውን ያቀርባል።

እኛም ይህንን ጥሪ ተቀብለን በምሕረት ወደ ተሞላው የአምላክ ልብ ልንመለስ ያስፈልጋል። አሁን ባለንበት የጸጋ ወቅት ወደ እግዚኣብሔር ምሕረት ዐይናችንን ልንመልስ ያስፈልጋል። የዐብይ ጾም ወቅት ከሚያጎድፈን እና ያልተገባን እንድንሆን በማድረግ የእግዚኣብሔር ልጆች የመሆን መብታችንን የሚነፍጉንን ነገሮች ሁሉ በምሕረት ድል እንድናደርግ የሚረዳን ወቅት ነው። ዐብይ ጾም ከባርነት ወደ ነፃነት፣ ከመከራ ወደ ደስታ፣ ከሞት ወደ ሕይወት ጉዞ የሚደረግበት ወቅት ነው።

ጾማችን በጀመርንበት ቀን በግንባራችን ላይ የተቀባነው አመድ ሥር መሰረታችንን በማስታወስ ከፈር መሠራታችንን እና ወደ አፈር እንደ ምንመለስ ያስታውሰናል። እርግጥ ነው በእግዚኣብሔር የፍቅር እጆች ውስጥ አፈር ነን፣ እስትንፋሱንም በእያንዳንዳችን ላይ እፍ በማለት የሕይወት መንፈስን ሰጠን፣ አሁንም እየሰጠን ይገኛል። ሸፋፍኖ ከያዘን የራስ ወዳድነት መንፈስ፣ በራስ ወዳድነትና በምን አገባኝ ስሜት እንድንጓዝ ሸፋፍኖ ከያዘን መንፈስ፣ የርኅራኄ መንፈሳችንን ሸፋፍኖ ከያዘን መንፈስ፣ አድማሳችንን ከሚያጠበው እና የልብ ምታችንን ከምያቀዘቅዙት ከእነዚህ እና ከማንኛውም ዓይነት ለየት ካለ መንፈስ  የሚታደገንን የሕይወት እስትፋሱን በቀጣይነት ሊሰጠን ዝግጁ ነው።

የእግዚኣብሔር የሕይወት እስትንፋስ እምነታችን እንዲቀበር ከሚያደርጉት፣ ለጋሾች እንዳንሆን፣ እምነታችንን ከሚያደመዝዙ ማነኛውም ዓይነት መንፈሶች እኛን ይታደገናል ያድነናልም። የዐብይ ጾምን ወቅት መለማመድ ወይም መኖር ማለት አምልክ ባለ ማቋረጥ የሚለግሰን እስትንፋሱን በመቀበል የጨቀዬ ታሪካችንን ፍሬአማ በሆነ መልኩ እንዲነጻ ማድረግ ማለት ነው።

የእግዚኣብሔር እስትንፋስ ሁል ጊዜ እኛ ለመረዳት ከሚያዳግተን እና ምንም እንኳን እኛን እንደ ሚጎዱን እያወቅን፣ ነገር ግን ጤናማ ነገር እንደ ሆኑ አድርገን የምንተገብራቸውን ተግባሮች ውስጥ ታፍነን እንድንኖር ከሚያደርጉን መነፈሶች ሁሉ ነፃ ያወጣናል። የሚጎዱን ነገር ግን እኛ ከእነዚህ ነገሮች ጋር በመለማመዳችን የተነሳ እንደ ጤናማ አድርገን የምንቆጥራቸውን  ተግባሮች፣ በጭላንጭል ውስጥ ያሉትን መንፈሶች፣ የጭንቀት መንፈሶችን ሳይቀር እንድናሸንፍ ይረዳናል።

የዐብይ ጾም ወቅት እምብዬው የምንልበት ወቅት ነው። የዐብይ ጾም ወቅት መንፈሳዊ ሕይወታችንን አፍኖ በመያዝ ሕይወታችንን በምን አገባኝ መንፈስ በመመረዝ የሌሎች ሰዎች ሕይወት እኔን በፍጹም አይመለከተኝም እንድንል የሚያባብሉን መንፈሶችን በመቃወም እነዚህን ክፉ መንፈሶች እንብዬው አታስፈልገኝም በማለት ይምንቃወምበት ወቅት ነው የዐብይ ጾም ወቅት።

የዐብይ ጾም ወቅት ሕይወታችንን የሚመርዙ ነገሮችን ሁሉ እብዬው በማለት ከሕይወታችን እነዚህን መርዛማ ነገሮችን የምናስወግድበት ወቅት ነው። የዐብይ ጾም ወቅት ትርጉም የለሽ የሆኑ ባዶ ቃላትን፣ ሰዎችን መፈረጅ፣ በሰዎች ላይ ተገቢ ያልሆነ ሂስ እንድናደርግ የሚገፋፉንን ስሜቶች እንብዬው አታስፈልግኝም የምንልበት ወቅት ነው የዐብይ ጾም ወቅት።

የዐብይ ጾም ወቅት የክርስቶስ መከራ ተካፋይ የሆኑ ወንድም እና እህቶችን በማግለል እግዚብሔርን ብቻ እንድንፈልግ የሚያደርገንን አፍኖ የያዘንን መንፈስ እንብዬው አታስፈልገኝም የምንልበት ወቅት ነው። በአጠቃላይ የዐብይ ጾም ወቅት  እምነታችንን ሊቀንሱ የሚችሉትን መንፈሶች፣ ክፉ ባሕሎችን፣ አግላይ የሆኑ ባሕሪያትን ሁሉ እንብዬው አታስፈልጉኝም የምንልበት ወቅት ነው የዐብይ ጾም ወቅት።

የዐብይ ጾም ወቅት የማስታወሻ ጊዜ ነው። በእዚህ የዐብይ ጾም ወቅት የምናሰላስልበትና ራሳችንን እግዚኣብሔር በሩን ቢዘጋብን ምን ልንሆን እንችላለን ብለን የምንጠይቅበት ወቅት ነው። ይቅርታን መለገስ የማይሰለቸውና ሁልጊዜ አዲስ ሰዎች እንድንሆን እድል ከሚሰጠን ከእግዚኣብሔር ምሕረት ወጭ ብሆን ምን ልሆን እችላለሁ? ብለን ራሳችንን የምንጠይቅበት ወቅት ነው የዓብይ ጾም ወቅት። የዐብይ ጾም ወቅት በጣም ብዙ ሰዎች ሕይወታችንን ደግፈው፣ እጃቸውን ዘርግተው እንዲሁም ተጨባጭ በሆነ መልኩ እኛን በመርዳት ተስፋ ሳንቆርጥ ወደ ፊት እንድንጓዝ እና አዲስ ሕይወት እንድንኖር ያስቻሉንን ሰዎች ሁሉ የማስታወሻ ጊዜ ነው የጾም ወቅት።

የዐብይ ጾም ወቅት እንደ ገና በአዲስ መልኩ መተንፈስ የምንጀምርበት ወቅት ነው። የዐብይ ጾም ወቅት ልባችንን በመክፈት ውስጣችንን ከክፉ ነገር አጽድቶ መልካም ሰዎች እንድንሆን ለሚያደርግን መንፈስ ልባችንን የምንከፍትበት ወቅት ነው።

የዐብይ ጾም ወቅት በክፉ ነገሮች ፊት ቆመን ልብሳችንን የምንቀድበት ወቅት ሳይሆን መልካም ነገሮችን እንድናከናውን የሚረዳንን ልባችን የምንከፍትበት ወቅት ነው። የዐብይ ጾም ወቅት እንድንገለልና ሽባ እንድንሆን የሚያደርጉንን ነገሮች ሁሉ አውልቀን የምንጥልበት ወቅት ነው። የዐብይ ጾም ወቅት ርኅራኄን የምናሳይበት ወቅት ነው። የዐብይ ጾም ወቅት በመጽሐፈ መዝሙር 51: 12 15 ላይ እንደ ተጠቀሰውከአዳኝነትህ የሚመነጨውን ደስታ መልሰህ ስጠኝ እንድታዘዝህም ፈቃደኛ አድርገኝ፣ እኔም አመሰግንሃለሁ!” የምንልበት ወቅት ሊሆን ይገባል።

ክቡራን እና ክቡራት ታዳሚዎቻችን ቀደም ሲል ስትከታተሉት የነበራችሁት በየካቲት 22/2009 ዓ.ም. ዐብይ ጾምን በተጀመረበት ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በሮም ከተማ በሚገኘው በቅድስት ሳቢና ቤተ ክርስቲያን ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ያሰሙትን ስብከት ነበር። አብራችሁን ሆናችሁ ዝግጅቶቻችንን ስለተከታተላችሁን እናመሰግናለን።

 








All the contents on this site are copyrighted ©.