2017-02-21 10:48:00

ቅዱስነታቸው በስብከታቸው "ክርስቲያኖች ቂምና በቀልን አስወግደው የምሕረት እና የጸሎት መንገድ መያዝ ይኖርባቸዋል" አሉ።


ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በየካቲት 12/2009 ዓ.ም. በሮም ከተማ የሚገኘውን የማሪያ ጆዜፓ ቁምስናን መጎብኘታቸውና በእዚያም ቁምስና የመስዋዕተ ቅዳሴን ማሳረጋቸውን ለመረዳት ተችሉዋል። በእለቱ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት ቅዱስነታቸው አጽኖት ሰጥተው እንደ ገለጹት ክርስቲያኖች ቂምና በቀልን ከሕይወታቸው ውስጥ አስወግደው ወደ ቅድስና የሚያመራውን የምሕረት እና የጸሎት መንገድ መያዝ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

በምንም ዓይነት መልኩ የቂም በቀል መንገድን መከተል የለብንም ያሉት ቅዱስነታቸው በምትኩም ክፉ ነገሮችን ለሚፈጽሙብን ሰዎች ሁሉ መጸለይ እንደ ሚገባ ገልጸው ይህም ተግባር ግጭትን በማስወገድ ሰላም እዲሰፍን ያደርጋል፣ ይህም ተግባር ክርስቲያኖችን ወደ ቅድስና መንገድ እንዲያመሩ ያደርጋቸዋል ብለዋል።

እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የስርዓተ-ሊጡርጊያ አቆጣጠር በተነበበው የእለቱ ወንጌል ላይ ትኩርታቸውን በማድረግ ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው በእዚህም ስብከታቸው ወደ ፍጽምናና ወደ ቅድስና እንድናመራ ያግዘናል ያሉትን ተግባራትን ጠቃቅሰው በዋነኝነት  የፍጽምናና የቅድስናን መንገድ እንዳንከተል እንቅፋት የሚሆኑትን ቂም እና በቀል ማስወገድ ይጠበቅብናል ብለዋል።

አንድ አንድ ጊዜ ሰዎች “ይህንን ነገር ፈጽመህብኛል ለእዚህም ተግባርህ ዋጋ ትከፍልበታለህ” ሲሉ ይደመጣሉ በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ይህ አባባል ግን የክርስቲያኖች ቋንቋ ሊሆን አይገባም ካሉ ቡኋላ እግዚኣብሔር ክፉ ተግባራትን ለሚፈጽሙብን ሰዎች ሁሉ መጸለይ እንደሚጋባ ነው የሚያስተምረን ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በቴሌቪዢኖቻችን እና በጋዜጦች ላይ እንደ ምንመለከተው ዓለማችን በጦርነትና በግድያ በተለይም ሕጻናት የሆኑ ልጆች ሲሰቃዩ እንመለከታለን፣ እናነባለንም ያሉት ቅዱስነታቸው ይቅር መባባል እነዚህን በደሎች ሁሉ ያስቀራል ወደ ሰላም እና ወደ ቅድስና መንገድ ይመራል ብለዋል።

እግዚኣብሔር መሐሪ፣ ቅዱስና ፍጹም ከሆነ እኛም እንደ እርሱ ይቅር ባይ፣ ቅዱስና ፍጹማን ልንሆን ያስፈልጋል ያሉት ቅዱስነታቸው እነዚህን የሚፈጽሙ ሰዎች ሁሉ ቅዱሳን ሊባሉ ይችላሉ፣ የክርስትና ሕይወት በጣም ከባድ የሚባል ሕይወት ሳይሆን እነዚህን ነገሮች በመፈጸም የሚገኝ ቀላል ሕይወት ነው ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በስብከታቸው ማጠቃለያ ላይ እንደ ገለጹት ጸሎት የጥላቻ እና የጦርነት ማርከሻ ፍትሁን መድኋኒት ነው ካሉ ቡኋላ የማይወዱዋችሁ ሰዎች ካሉ ጸልዩላቸው ምክንያቱም ጠንካራ ጸሎት ጥላቻን ገርስሶ ሰላምን ያጎናጽፋል ካሉ ቡኋላ ለእለቱ ያዘጋጁትን ስብከት አጠናቀዋል።

 








All the contents on this site are copyrighted ©.