2017-02-16 14:21:00

የየካቲት 5/2009 ዓ.ም. እለተ ሰንበት ቃለ እግዚኣብሔር በክቡር አባ ተስፋዬ ገብረሚካኤል።


የተከበራችሁ የእግዚኣብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!

ጌታ አምላካችን መልካም ፈቃዱ ሆኖ የእኛን አመለካከት ለማስተካከልና ለማስተማር የተለያዩ ወቅቶችን በመጠቀም በአባታዊ ፍቅሩ የተዋረዱትን ስላከበረ፣ በሰዎች ዘንድ የተናቁትን በክብር ከፍ ከፍ ስለ አደረገ፣ የታረዙትን ስለ አስታወሰና እንዲሁም ግፍ ለሚደርስባቸው ሰዎች ሁሉ ጠበቃ ሰለ ሆነ ቸሩ አማላክችን ውዳሴ፣ ክብርና አምልኮ ለእርሱ ለዘላለም ይሁን!

የእዚህን ዜና ሙሉ ይዘት ከእዚህ በታች የሚገኘውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማደመጥ ትችላላችሁ!

በዛሬው እለት የተነበበልን የሕያው የእግዚኣብሔር ቃል ማንነታችንንና በሰዎች ላይ ያለንን አመለካከት በደንብ እንድንፈትሽ የሚረዳንና በተለይም በተለያዩ ማኅበራዊና መንፈሳዊ የሥራ መስኮች በኋላፊነት ለምንመራ ሁላችን ድምጽ አልባ ለሆኑ በዘመናችን በወረደ አመለካከት አናሳ ብሔረሰብ ተብለው ለሚገመቱ ሰዎች ሁሉ እንዴት ለእነርሱ ድምጽ መሆን እንዳለብን ቃሉ ያስረዳል።

ከዩሐንስ ወንጌል 4.1-42 ያለውምን ስናነብ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚያን ዘመን በጎሳ በዘር እና በባህል የነበረውን የጥላቻ አመለካከት እንዴት ባለ መልኩ እርሱ በሥጋ ከአይሁዳዊያን (ከተከበረ) ወገን ሆኖ ወደ ተናቀው ሳምራዊያን ወገን በፍቅር እና በጥበብ በመቅረብ የዘለዓለም ደስታ ተካፋዮች እንዲሆኑ ስያደርግ ይታያል። ኢየሱስ በዛሬው ወንጌል እንደ ተጠቀሰው ይህንን ለብዙ ዘመናት የቆየውን ጥላቻ ለማስወገድ ወይም ለማስታረቅ የወገኖቹንና የሌሎችንም የአስተሳሰብ ድንበር ስያልፍ እናያለን።

በመጀመሪያ ደረጃ በወገን አኳያ ስንመለከት እርሱ ያናገራት ሴት አይሁዳዊት ሳትሆን ሳምራዊት ነበረች። በሳምራዊያንና በአይሁዳዊያን መካከል ምንም ዓይነት ግንኙነት አልነበራቸውም። ምክንያቱም ሳምራዊያን በፖለቲካ፣ በዘር፣ በባሕል፣ በሐይማኖት ልዩነት ከአይሁዳዊያን ጋር ብዙ ቅራኔ ነበራቸው። እንዲሁም ሳምራዊያን ኦሪትን እንጂ ነቢያትን አይቀበሉም ነበር። እነዚህ ሁሉ ነገሮች ተደማምረው ከአይሁዳዊያን እንዲገለሉ አድርጎዋቸዋል።

አይሁዳዊያን ደግሞ ሕግን በሚገባ ጠንቅቀን እናውቃለን በሚል አስተሳሰብ በማንነታቸው የሚኩራሩ ሰዎች የነበሩ ሲሆን ከእዚህም ጭብጥ ሐሳብ በመነሳት ሌሎች ሰዎች “የአባቶቻችንን ወግ አይጠብቁም” ከሚል አስተሳሰብ ተነስተው ሌሎችን እንደ አረማዊ ይቆጥሩ ነበር። ሳምራዊቱዋም ሴት በዩሐንስ ወንጌል 4. 9 ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ውሃ አጠጭኝ” ባላት ጊዜ “አንተ አይሁዳዊ ሆነህ እንዴት እኔን ሳምራዊቷን ውሃ አጠጭኝ ብለህ ትጠይቀኛለህ!” ያለችበት ምክንያት በሁለቱ ወገኖች የነበረውን ጥላቻ፣ መራራቅ የአይሁዳዊያንን የበላይነትና የእርሷን ዘር (ወገን) የበታችነት ስሜትን በግልጽ ቁልጭ አድርጎ ያስቀመጥ ነው።

የኢየሱስም ጥማት የነበረው በሁለቱ ወገኖች መካከል የነበረውን ተገቢ ያልሆነ የጥላቻ አጥርን ነቅሎ መጣልና የእግዛኢብሔርን መንግሥት መወረስ የሚቻለው በነገሮች ሳይወሰኑ በእውነተኛ ፍቅር መኖር ሲችሉና እርሱም የመጣው ለአንድ ወገን ደኅንነት ብቻ ሳይሆን ዓለማቀፋዊ ደኅንነትን እንዳመጣ ለማሳየት ፈልጎ ነው።

ሐዋሪያው ጳውሎስ ወደ ሮም ሰዎች በጻሐፈው መልእክቱ ላይ እንዲህ ይላል “የእግዚኣብሔር ሕዝብ ያልነበረውን ሕዝቤ ብዬ እጠራዋለሁ” (9.25) ይላል። ሳምራዊያንም እንዲህ ዓይነት ሰዎች ነበሩ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ሕዝቦቹ እንዲሆኑ ይህችን ሴት እንዴት እንደ ተጠቀመ ሰምተናል።

በሁለተኝ ደረጃ ደግሞ አይሁዳዊያን ለሴት ልጅ የሚሰጡት አመለካከት የወረደ ነበር። ወንዶች ጥዋት ጥዋት ስጸሊዩ “አምላኬ ሆይ ሴት አድርገህ ስለ አልፈጠርከኝ አመሰግንሃለው” ይሉ ነበር።  የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርትም በእዚሁ ዓይነት ባሕል ውስጥ ስላደጉ “ኢየሱስ ከሴት ጋር ሲነጋገር በማየታቸው “በጣም ተደነቁ” (ዩሐንስ 4.27) ይላል። ይህንንም ማድረጉ እርሱ የመጣው ማንንም ሰው በጎሳ፣ በፆታ፣ በብሔር እና በሐይማኖት  ሳይለያይ ሁሉንም የመንግሥቱ ወራሻች እንዲሆን ስለፈለገ መሆኑን ያሳየናል። በሌላ በኩል ስንመለከት ደግሞ የቃሉ አብሳሪ እንዲሆንም ሲጠቀምባቸውም እናያለን። እርሱዋም ማንነቷን በግልጽ ከተናገረች ቡኋላ እርሱ መሲሕ መሆኑን እንዳወቀች የመጣችበትን ዓላማ በመተው ወደ ወገኖቹዋ ሩጣ በመመለስ እርሷ የሰማችሁን የሕይወት ቃል እነርሱም እንዲሰሙ በማድረጉዋ የተነሳ እርሷ አምና ወገኖቹዋም እንዲድኑ አድርጋለች።

እንደ እርሷዋ የዋህ ለሆኑ ሰዎች ቅዱስ ኤፍሬም እንዲ ይላል “ለአንዲት እርግብ ስንዴ ስጥተን ስናቀርባት ለራሱዋ ብቻ በልታ ዝም አትልም፣ ነገር ግን ወደ ወገኖቹዋ በመሄድ ስንዴ ወደ አለበት ቦታ ሁሉንም ጥርታ ታመጣለች” ብሉዋል። በተመሳሳይ መልኩም ይቺ ሳምራዊት ሴት እንደ እርግቡዋ የዋህ የነበረች ሴት በመሆኑዋ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ባልሽን ጠርተሽ ነይ ባላት ጊዜ ስለ ሕይወቱዋ እውነቱን ከተናገረች ቡኋላ ለወገኖቹዋ የቃሉ መስካሪ ሆነች።

ክቡራን እና ኩቡራት ወንድሞቼና እህቶቼ እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!

ከእዚህ ለየት ካለው የኢየሱ አቀራረብ እና የሳምራዊቱዋ ሴት ሕይወት ምን እንማራለን? በዘመናችን ከሚታዩ ችግሮች ጋር እንዴት እናነጻጽራለን? ዛሬም በአከባቢያችን፣ በሀገራችን፣ በአጠቃላይ እንዲሁም በዓለማችን በቀጥታ ሆነ በተዘዋዋሪይ አንዱ አንዱን የሚበድል፣ የሚጨቁን ወይም ደግሞ የበላይነት ስሜት ለማሳየት የተለያዩ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ። ለምሳሌ ሐይማኖትን፣ ባሕልን፣ ጎሳን፣ ቀለምንና ፆታን በመጠቀም ጥቃትን ለሚፈጽሙ ሰዎች እንደ እውነተኛ ክርስቲያን ሁሉም የራሱን ድርሻ መወጣት አለበት።

ይህም ማለት ትንሽ እሳት በጎሬበታችን ስትቀጣጠል ካየን ቀስ በቀስ በሁሉም ዘንድ ከመዛመቱዋ በፊት በጎ ሕሊናችንን በመጠቀም የተጣሉትን ማስታረቅ፣ የተራራቁትን ማቀራረብ፣ ለተገፉ ሰዎች ሁሉ ጥብቅናን መቆም፣ ፍትህ በተጓደለበት ሥፍራ ሁሉ ፍትህ ይሰፍን ዘንድ ከሰዎች ዘንድ ሊሰነዘሩ የሚችሉ ጥቃቶችን ሳንፈራ ከእግዚኣብሔር ምስጋናን ለማግኘት መታገል ያስፈልጋል። ቅዱስ ጴጥሮስ በአንደኛው መልዕክቱ (2.20) ላይ “ መልካም አድርጋችሁ መከራን ስትቀበሉ ብትታገሱ ከእግዚኣብሔር ምስጋናን ታገኛላችሁ” ይለናል። ከላይ የተጠቀሱትን ነገሮች ለማድረግ በምንጥርበት ጊዜያቶች ሁሉ ከራሳችን ወገኖች ተቃውሞ እንደ ሚደርስብን መርሳት የለበንም። አይደለም ለእኛ ጌታ ኢየሱስንም “ለምን ከቀራጮችና ከኋጥያተኞች ጋር አብረህ ትመገባለህ?” ተብሎ ተወቅሶ ነበር። በወጣይነትም የእርሱ ደቀማዛሙርት ላይም ተመሳሳይ የሆነ ትችት ደርሶባቸው ነበር። በሐዋሪያት ሥራ (11.3) ላይ ሐዋሪያ ጴጥሮስ “ለምን ወደ አልተገረዙ ሰዎች ቤት ገብተህ ከእነሩሱ ጋር ትበላለህ” ተብሎ መወቀሱን እናገኛለን። እኛም መፍራት የሚገባን የወንድሞቻችንን የጨለማ አስተሳሰብና ወቀሳ ሳይሆን ከአብርሃም አምላክ የተሰጠንና ወደ አብርሃም አምላክ የሚመራንን ሕሊናችንን ነው መፍራት የሚጠበቅብን። ምክንያቱም ሕሊናውን በአግባቡ የሚጠቀም ሰው እውነትን ይናገራል (ሮም 9.1)። ቅዱስ አጎስጢኖስ እንዲህ ይላል “ሕሊናዬ ከእግዚኣብሔ የተሰጠኝ ልሉ የሆነ ስጦታዬ ስለሆነ መልካም የሆኑ ነገሮች ሁሉ በነፃ የምቀዳባት ምንጭ ናት” ይለናል።    

እውነት ለመናገር የወንጌል አስተምህሮ ተቃራኒ ከሆነ ወግ እና ባሕል እስረኛነት ካልተላቀቅን በስተቀር መተግበሩ መጣም ከባድ ይሆንብናል። ስለዚህ እስረኛ መሆን ካለብን የኢየሱስን ወይም ደግሞ የአባቶቻችንን ወግ እና ልማድ. . . ከሁለቱ አንዱን መምረጥ ያስፈልጋል።

ምርጫውን ለእያንዳንዳችን እተዋለሁኝ።

ነገር ግን ትክክለኛውን ውሳኔ ማድረግ እንድንችል እግዚኣብሔር በጸጋው ይርዳን አሜን!








All the contents on this site are copyrighted ©.