2017-01-19 15:18:00

ቅዱስነታቸው ክርስቲያኖች ጠንክረው ከሠሩ በመካከላቸው ሕብረት እና እርቅን መፍጥረ ይችላሉ ማለታቸው ተገለጸ።


ቅዱስ አባታችን ፍራንቸስኮ በጥር 10/2009 ዓ.ም. ክርስቲያኖች ጠንክረው ከሰሩ በመካከላቸው  ሕብረት እና እርቅን መፍጥረ ይችላሉ ማለታቸው ተገለጸ። ቅዱስነታቸው ይህንን መልእክታቸውን ያስተላለፉት በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ 6ኛ አዳራሽ ለተገኙ ምዕመናን እና ለሀገር ጎብኝዎች ባስተላለፉት ምልእክት ሲሆን መልእክታቸውም ትኩረቱን አድርጎ የነበረው በጥር 10/2009 ዓ.ም. የተጀምረውን እና ለአንድ ሳምንት የሚቆየውን ለክርስቲያኖች ኅብረት የሚደረገው ጸሎት አስፈላጊነት እና ከእዚህ ቀደም የክርስቲያን ተስፋ በሚል አርዕስት ዙሪያ አድርገውት ከነበረው አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል ያካተተ እንደ ነበረም ለመረዳት ተችሉዋል።

የእዚህን ዜና ሙሉ ይዘቱን ከእዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ።

ከሚለያዩን ነገሮች ይልቅ አንድ የሚያደርጉን ነገሮችን መመልከት ይኖርብናል በማለት አስተምህሮዋቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ክርስቲያኖች ህብረታቸውን ለማጠናከር አስፈላጊውን ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ቅዱስነታቸው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው ከተመረጡ ቡኋላ ለድኾች እንክብካቤ ይደረግ ዘንድ እና በክርስቶስ ስም የተሰየሙ ክርስቲያኖች ሁሉ በአንዱ በክርስቶስ ስም ስለሚጠሩ ህብርትን ፈጥረው የክርስትናን እሴቶችን በመላው ዓለም ለማዳረስ መትጋት እንደ ሚኖርባቸው በተደጋጋሚ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወቃል።

ይህንንም አሳባቸውን ለማጽናት በማሰብ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር በጥር 12/2016 ዓ.ም. በኩባ ዋና ከተማ ሀቫና የሞስኮ እና የመላው ራሻ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ ከሆኑት ፓትሪያርክ ቀረሎስ ጋር ተገናኝተው ከመቸው ጊዜ በከፋ ሁኔታ በአሁኑ ወቅት የሚታየውን በክርስትያኖች ላይ የሚደረሰውን ከፍተኛ ስደት ለመቀረፍ እና በዓለማችን ውስጥ በአሁኑ ወቅት እየዳሸቀ የመጣውን ስነ-ምግባራዊ እሴቶችን መልሶ ለመጎናጸፍ፣ እንዲሁም የክርስቲያኖች ሁሉ የጋራ መጠሪያ የሆነውን ክርስቶስን በጋራ ለዓለም መመስከር የሚችላበትን መንገድ ለመቀየስ ያስችላቸው ዘንድ መመካከራቸው እና የጋራ መግለጫ አውጥተው እንደ ነበረ ይታወሳል።

ቅዱስነታቸው ክርስትያኖች ሕብረታቸውን ያጠናክሩ ዘንድ የጀመሩትን ተግባር ለማጠናከር በማሰብ በጥቅምት ወር 2016 የሉተራን ቤተ ክርስቲያን ከካቶሊክ የተለየችበትን 500ኛ አመትን ለመዘከር በተዘጋጀው እና በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት መኸከል ያለውን መልካም ግንኙነት ለማጠናከር በማሰብ “ከግጭት በተስፋ ወደ ሕብረት” በሚል አርዕስት ተዘጋጅቶ በነበረው የሦስት ቀን ጸሎት ላይ ለመሳተፍ ወደ ስዊድን ተጉዘው እንደ ነበረ መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን ይህም ተግባራቸው ክርስቲያኖች እየፈጠሩት ያለውን ሕብረት ለማጠናከር እና ይህንንም ጥረት ተጨባጭ በሆነ መልኩ ለመግለጽ አስበው ያደረጉት ጉብኝት እንደ ነበረም ይታወቃል።

የክርስትያን ተስፋ በሚል አርዕስት በተከታታይ ስያስተላለፉት የነበረውን አስተምህሮ ስለ ክርስቲያን ሕብረት አስፈላጊነት ካስተላለፉት መልእክት ቡኋላ ቅዱስነታቸው በቀጣይነት ያቀረቡ ሲሆን የእለቱ የክርስቲያን ተስፋ በሚል ጭብጥ ላይ ያጠነጠነው አስተምህሮዋቸው፣ የተሰጠው ተልዕኮ በጣም ከባድና አስቸጋሪ በመሆኑ የተነሳ ይህንን አስቸጋሪ ተልእኮ ጥሎ በመሸሽ ላይ ስለነበረው ነብዩ ዮናስ የሚያወሳ አስተምህሮ እንደ ነበረም ለመረዳት ተችሉዋል።

“ነብዩ ዮናስ ተሳፍሮበት የነበረው መርከብ በከፍተኛ ማዕበል በተናወጠበት ወቅት በመርከቡ ላይ የነበሩ አረማዊ ቀዛፊዎች የእግዚኣብሔር ሰው የሆነው ነቢዩ ዮናስ ይህንን ከፍተኛ እና ሞትን ልያስከትል የሚችል አደጋ እንዲያመልጡ ይረዳቸው ዘንድ እንዲጸልይላቸው ጠይቀውት እንደ ነበረም ገልጸዋል።

ይህም ታሪክ በተስፋ እና በጸሎት መሃከል ቀጥተኛ የሆን አግንኙነት እንዳለ ያሳያል ያሉት ቅዱስነታቸው ሁላችንም ከሞት ጋር ፊት ለፊት በምንጋፈጥበት የጭንቀት ወቅቶች ሁሉ “ሰብዓዊ ድክመታችን በመረዳት ከእዚህ ስቃይ ለመዳን መጸለይ እንዳለብን በፍጥነት እንገነዘባለን” ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በአስተምህሮዋቸው መደምደሚያ ላይ እንደ ገለጹት ነብዩ ዮናስ በእነዚህ አረማዊያን ቀዛፊዎች ስም ጸሎት ማድረግ በመቻሉ አረማዊያን ቀዛፊዎቹ እውነተኛውን እግዚኣብሔር እንዲያውቁት ረድቶዋቸው ነበር ብለው የክርስቶስ አካላዊ ሞት እና ሞትን ድል አድርጎ የተነሳበት ሚስጢር ለእያንዳንዳችን፣ ሞት በራሱ የተስፋ ጥሪ እና አዳኝ የሆነውን እግዚኣብሔርን የምንገኛኝበትን ጸሎት ማድረግ እንዳለብን ያስተምረናል ካሉ ቡኋላ አስተምህሮዋቸውን አጠናቀዋል። 

 








All the contents on this site are copyrighted ©.