2017-01-19 11:29:00

ር. ሊ. ጳ. ፍራንቸስኮ 103ኛው የዓለም ስደተኞች ቀን በተከበረበት ወቅት ለሕጻናት ስደተኞች ትኩረት ይሰጥ ዘንድ ጥሪ አቀረቡ


በጥር 7/2009 ዓ.ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የስደተኞች ቀን በተከበረበት ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ ለሕጻናት ስደተኞች ከፍተኛ ትኩረት ይሰጥ ዘንድ ማሳሰባቸው ተገለጸ። ቅዱስነታቸው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ይህንኑ የስደተኞች ቀን ለመታደም ለተገኙ ስደተኞች እና በተመሳሳይ ጊዜም አስተላልፈውት የነበረውን የጠቅላላ አስተምህሮ ለመከታተል ለተገኙ ምዕመናን እና የሀገር ጎብኝዎች ካስተላለፉት የጠቅላላ አስትምህሮ በመቀጠል ካሳረጉት የመልአከ እግዚኣብሔር ጸሎት ቡኋላ አጽኖት ሰጥተው ባስተላለፉት መልዕክት እንደ ገለጹት በተለያዩ አስገዳጅ በሆኑ ምክንያቶች የተነሳ ሀገራቸውን ጥለው ለተሰደዱ ስደተኞች በተለይም ሕፃናት ለሆኑ ስደተኞች ከፍተኛ የሆነ ትኩረት እንዲሰጣቸው አሳስበዋል።

የእዚህን ዜና ሙሉ ይዘት ከእዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ።

ቅዱስነታቸው መልዕክታቸውን ባስተላለፉበት ወቅት እንደ ገለጹት በተለይም በአዋቂ ሰዎች ሳይታጀቡ ብቻቸውን ሀገራቸውን ጥለው ለተሰደዱ ለአቅመ አዳም እና ሄዋን ላልደረሱ ሕፃናት ጥበቃ ስለሚያስፈልጋቸው  በተቻለው መጠን  አስፈላጊ የሆነ ከለላ ይሰጣቸው ዘንድ ጥሪ አድርገው አዲስ ከተቀላቀሉት የማኅበረሰብ ክፍል ጋር ተዋህደው ይኖሩ ዘንድም ድጋፍ እንዲሰጣቸው በአክብሮት ጥሪ አድርገዋል።

“እነዚህ ወንድማቻችንና እህቶቻችን በተለይም ደግሞ ያለወላጆቻቸው ጥበቃ ብቻቸውን የተሰደዱ ሕፃናት ስደተኞች ለብዙ አደጋዎች የተጋለጡ ናቸው” በማለት መልእክታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ለባርነት እስከመሸጥ እና ለአስገዳጅ የወሲብ ባርነት እስከ መጋለጥ ድረስ የሚዳርጋቸው አደጋ ውስጥ ስለ ሚገኙ ተገቢው እንክብካቤ ሊደረግላቸው ይገባል ብለዋል።

በጥር 7/2009 ዓ.ም. 103ኛው የዓለማቀፍ የስደተኞች ቀን ታስቦ የዋለ ሲሆን በእዚህ 103ኛ የስደተኞች ቀን ለየት ባለ ሁኔታ ትኩረት ተሰጥቶ የነበረው በእድሜ አናሳ ስለሆኑ ሕፃናት ስደተኞች ሲሆን “ሕፃናት ስደተኞች፣ ለአደጋ የተጋለጡ እና ድምጽ አልባ ናቸው” በሚል መሪ ቃል ተከብሮ እንደ ነበረም ተገልጹዋል።

ቅዱስነታቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ ስደተኞች በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በተገኙበት ባስተላለፉት መልእክት እንደ ገለጹት “ውድ ወዳጆቼ ሆይ!  እናንተን በእንግድነት በተቀበላችሁ ማኅበረሰብ ውስጥ በሰላም እንደ ምትኖሩ ተስፋ አደርጋለሁኝ” ያሉት ቅዱስነታቸው  “በእንግድነት የተቀበላችሁን ሀገር ሕግ እና ባህል በማክበር፣ በተመሳሳይ መልኩም ከእየ ሀገራችሁ ይዛችሁት የመጣችሁትን በሕላችሁንም በመጠበቅ” መኖር ይገባችኋል ካሉ ቡኋላ “የተለያዩ ባሕሎች በሚዋሀዱበት ወቅት ሁሉ ሁላችንንም የበለጸገ ማኅበረሰብ እንድንገነባ ያደርገናል ብለዋል።

ቅዱስነታቸው ስደተኞችን በመቀበል አስፈላጊውን እገዛ በማድረግ ላይ ከሚገኙትን ማህበራት ውስጥ አንዱ የሆነውን የሮም ሀገረ ስብከት እያከናወነ ስለሚገኘው መልካም ተግባር ከፍተኛ ምስጋናን አቅርበው ስደተኞችን በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ እየደገፉ የሚገኙትንም ሰዎች ሁሉ አመስግነው እና በእዚህ መልካም ተግባራቸው እንዲቀጥሉ አበረታተው የዛሬ 100 አመት ገደማ ወደ ዘላለም ሕይወት የተሻገረችሁና የስደተኞች የበላይ ጠባቂ የሆነችውን  ቅድስት ፋራንሰስ ዛቪየር ዘ ካብሪኒ መልካም አርአያን በመከተል እርሷ በሕይወቷ ዘመን ሁሉ “ቤት ንብረታቸውን ጥለው ለተሰደዱ ሰዎች እና ቤተሰቦች ሁሉ በታላቅ ብርታት የክርስቶስን ፍቅር ተጨባጭ በሆነ መልኩ እንደ መሰከረች ሁሉ እኛም የእርሷን አብነት በመከተል ሀገራቸውን በተለያዩ ምክንያቶች ጥለው የተሰደዱትን ወንድም እና እህቶቻችንን ማገዝ ይጠበቅብናል ካሉ ቡኋላ መልዕክታቸውን አጠናቀዋል።

 








All the contents on this site are copyrighted ©.