2017-01-12 10:24:00

ቅዱስነታቸው በጳውሎስ 6ኛ አዳራሽ ባስተላለፉት ጠቅላላ አስተምህሮ ተስፋ የሰው ልጅ ዋንኛ ስንቁ ሊሆን ይገባል ማለታቸው ተገለጸ


ቅዱስ አባታችን ፍራንቸስኮ በጥር 3/2009 ዓ.ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለጠቅላላ ሳምንታዊ አስተምህሮ ለተገኙ ምዕመናን እና የሀገር ጎብኚዎች ባስተላለፉት የጠቅላላ አስተምህሮ እንደ ገለጹት ተስፋ የሰው ልጅ ዋንኛ ስንቁ ሊሆን ይገባል፣ በተለይም መጭው ጊዜ መልካም እንደ ሚሆን ተስፋ ማድረግ፣ በሕይወት ማመን፣ በአጠቃላይም አዎንታዊ የሆነ አስተሳሰብ መያዝ አስፈላጊ ነው ማለታቸው ተገለጸ።

የእዚህን ዜና ሙሉ ዝርዝር ከእዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ።

“የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደ ምን አረፈዳችሁ!” በማለት አስተምህሮዋቸውን የጀመሩት ቅዱስነታቸው “ባሳለፍነው የታኅሣሥ ወር እና በእዚህ በያዝነው የጥር ወር መግቢያ አከባቢ የስብከተ ገናን እና የክርስቶስ ልደት በዓላትን አክብረናል። ይህ የስራዓተ ሉጥርጊያ ወቅት የእግዚኣብሔር ልጆች ተስፋን በድጋሜ ያነሳሳ ወቅት ነበር” በማለት አስተምህሮዋቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው እንዲህ አይነቱ ተስፋ ሕይወታችንን ትርጉም ባለው መልኩ እንድንኖር ይረዳናል ብለዋል።

መጽሐፍ ቅዱሳችን በእግዚኣብሔር ቃል በመታመናችን ምክንያት ከሚፈጠረው እውነተኛ ከሆነው ደስታ ጎን ለጎን ሐሰት በሆነ ተስፋ እና ዓለማዊ በሆኑ ጣዎቶች የመፈተን አደጋ ይገጥመናል በማለት አስተምህሮዋቸው የቀጠሉት ቅዱስነታቸው እነዚህም ሐሰት የሚባሉ ጣዎቶች ገንዘብ፣ ስልጣን እና አካላዊ ውበት መሆናቸውንም ገልጸዋል።

በእግዚኣብሔርን ተስፋ ማድረግ ብርታትን እና ተደጋጋሚ ጥረትን  የሚጠይቅ ጉዳይ ነው ያሉት ቅዱስነታቸው በተቃራኒው የሚገኘው ሐሰተኛ የሆነ ተስፋ ግን ያለ ብዙ ጥረት በቀላሉ የሚገኝ በቀላሉ ልንቆጣጠረው የምንችለው ነገር ነው ብለዋል።

የመዝሙረ ዳዊት ጸሐፊ ይህንን ዓይነቱን ጣዎት በአጽኖት ያወግዛል በማለት አስተምህሮዋቸን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ይህንንም ውግዘቱን በመዝሙረ ዳዊት በምዕራፍ 115, 4-8 ላይ እንደ ተጠቀሰው “የእነርሱ ጣዖታት ግን የሰው እጅ የሠራቸው፣ብርና ወርቅ ናቸው። አፍ አላቸው አይናገሩም፤ ዐይን አላቸው አያዩም፣ ጆሮ አላቸው አይሰሙም፤ አፍንጫ አላቸው አያሸቱም፤ እጅ አላቸው አይዳስሱም፤ እግር አላቸው አይሄዱም፤ በጒሮሮአቸውም ድምፅ አይፈጥሩም። እነዚህን የሚያበጁ የሚታመኑባቸውም ሁሉ እንደ እነርሱ ይሁኑ” በማለት እንዳወገዛቸው ጨምረው ገልጸዋል።

ቅዱስነታቸው አስተምህሮዋቸውን በቀጠሉበት ወቅት እንደ ገልጹት እግዚኣብሔር ሁልጊዜም ቢሆን ከእኛ በላይ መሆኑን ገልጸው እኛም የተፈጠርነው በእርሱ መልክ እና አምሳል ቢሆንም ቅሉ እርሱን ግን ወደ እኛ ማንነት ዝቅ ልናደርገው ወይም ደግሞ አዲስ የሆነ ጣዎት መፍጠር አንችልም ካሉ ቡኋላ በፍጹም ወደ እኛ ገጽታ እና ወደ እኛ ፍላጎት እግዚኣብሔርን ልናሳንሰው እንደ ማንችል በአፅኖት ገልጸዋል።

ቅዱስነታቸው በአስተምህሮዋቸው ማገባደጃ ላይ እንደ ገለጹት በእግዚኣብሔር ቃል በመታመን እና እርሱ የገባልንን ቃል ተስፋ በምናደርግበት ወቅት ሁሉ እርሱን እየመሰልን እንሄዳለን ብለው ይህም ተግባራችን ለእኛ ሲል በተወለደው፣ በሞተው እና ከሙታን በተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት ተካፋዮች እንድንሆን እና በእርሱ ጥበቃ ስር እንድንሆን ያደርገናል ካሉ ቡኋላ የእለቱን በተስፋ ዙሪያ ያጠነጠነ አስተምህሮዋቸውን ቅዱስነታቸው አጠናቀዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.