2017-01-11 15:42:00

በሮም የሚገኙ የኢትዮጲያ ካቶሊክ ምዕመናን ማኅበረሰብ አባላት የገና በዓልን በድምቀት አከበሩ።


በሮም ከተማና አካባቢው የሚኖሩ፣ ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ የምስራቅ አቢያተ ክርስቲያናት ምዕመናን፣ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መወለድ በማስታወስ አርብ ምሽት ታኅሣሥ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ማሳረጋቸው ታውቋል።

በሮም ከተማ የመድኃኔዓለም ቁምስና የኢትዮጵያ ካቶሊካዊ ምዕመናንም እንደዚሁ ከቫቲካን የኢትዮጵያ ጳጳሳዊ ኮሌጅ ካኅናት ጋር በመሆን የዋዜማ መስዋዕተ ቅዳሴን ማሳረጋቸውን ከቁምስናው የተላከልን ዜና ያመልክታል። በመስዋዕተ ቅዳሴው ላይ ዘጠኝ ካኅናት የተሳተፉ ሲሆን የእለቱን የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባት የተነተኑት ክቡር አባ ገብረመስቀል ሽኩር “አይዞአችሁ አትፍሩ፣ መልካም ዜናን ይዤላችሁ መጥቸአለሁ!” የሚለዉን የወንጌል መልዕክት በማስታወስ፣ መልካም ዜና የሆነውን የኢየሱስ ክርስቶስ መምጣት በየአመቱ ስናስታውስ ታሪክን እንደ ማስታወስ ብቻ ሆኖ እንዳይቀር፣ ነገር ግን የፍቅር፣ የሰላምና የደኅንነት ምንጭ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ተቀብለን ወደ ግል ሕይወታችን እንድናስገባው አሳስበዋል። ቤተ ክርስቲያን የኢየሱስ ክርስቶስን መወለድ በየዓመቱ እንድናስታውስ ስታደርግ ቀዳሚ ዓላማዋው በሚስጢረ ስጋዌ በኩል እግዚአብሔር ሥጋን በመልበስ ሰው ሆኖ መገለጡን እንደሚያስታውሰን አስረድተዋል። አክለውም በዓለማችን ዙሪያ የሚከሰቱትን ክፉ ነገሮች እና የሰላም መጓደል ስንመለከት “በእዉነት የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ተቀብሎ በሚገባ አውቆታል ወይ?” የሚያስብል ነው ካሉ በኋላ፣ ሁሉ ነገር ቢሟላ፣ ነገር ግን እግዚአብሔር ካልተጨመረበት ከንቱ እንደሆነ አስረድተዋል።

ክቡር አባ ታምሩ አዱኛ በሮም የመድኃኔዓለም ካቶሊካዊ ቁምስና መሪ ካኅን ለምዕመናኑ ሰላምታ አቅርበው በዓሉ የፍቅርና የሰላም እንዲሆን ተመኝተው በመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ ሥርዓት የተገኙትን ካህናትና ምዕመናንን አመስግነው፣ በቅርቡ በቫቲካን የኢትዮጵያ ጳጳሳዊ ኮሌጅ ምክትል አለቃ ሆነው የተመደቡትን ፍራንችስካዊ ካህን ክቡር አባ ገብረመስቀል መጂኖን ከምዕመናኑ ጋር አስተዋውቀው፣ ፍሬያማ የአገልግሎት ጊዜን ተመኝተውላቸዋል።

ምንጭ ዮሐንስ መኰንን








All the contents on this site are copyrighted ©.