2017-01-10 10:25:00

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮ በየጎዳናው ላይ ለሚኖሩና ቋሚ የመኖሪያ ስፍራ ለሌላቸው ሰዎች መጸለይ እንደ ሚገባ ማሳሰባቸው ተገለጸ።


ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በታኅሣሥ 30/2009 ዓ.ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለጠቅላላ አስተምህሮ ለተሰበሰቡ ምዕመናን እና የሀገር ጎብኚዎች ባስተላለፉት መልዕክት እንደ ገለጹት በየጎዳናው ላይ ለሚኖሩ ቋሚ የመኖሪያ ስፍራ ለሌላቸው ሰዎች መጸለይ እንደ ሚገባ ማሳሰባቸው ተገለጸ።

የእዚህን ዜና ዝርዝር ከእዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ።

ቅዱስነታቸው ይህንን መልዕክት ያስተላለፉት በእለቱ እንደ ጎሮጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር የተከበረውን የጌታችን የመዳኋኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ የተጠመቀበትን ቀን በሚዘከርበት የጥምቀት በዓል መስዋዕተ ቅዳሴን ካሳረጉ ቡኋላ ሲሆን ይህንንም የጥምቀት በዓል ማዕከል ባደረገው የጠቅላላ አስተምህሮዋቸው እንደ ገለጹት ኢየሱስ በዩሐንስ ለመጠመቅ በመጣበት ወቅት ዩሐንስ ኢየሱስን አንተ ነህ እንጂ እኔን የምታጠምቀኝ እኔ አንተን ማጥመቅ አይገባኝም በማለት ልያስቆመው ሞክሮ እንደ ነበረም ገልጸዋል።

ነገር ግን አሉ ቅዱስነታቸው ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው በእግዚኣብሔር እና በሰዎች መኋከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብ፣ የእግዚኣብሔርን ፈቃድ ለመፈጸም እግዚኣብሔር ለእኛ ቅርብ መሆኑን ለማሳየት እንዲሁም የእርሱ ልጆች መሆናችንን ለመግለጽ በመምጣቱ የተነሳ በዩሐንስ መጠመቅ ፈልጎ እንደነበረም ጨምረው ገልጸዋል።

ኢየሱስ በተጠመቀበት ወቅት “ይህ የምወደው እና በእርሱ ደስ የሚለኝ ልጄ ነው” የሚል የእግዚኣብሔር ድምጽ ተሰምቶ እንደ ነበረ በመግለጽ አስተምህሮዋቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው መንፈስ ቅዱስ በእርግብ አምሳል ተገልጦ እንደ ነበረም አስታውሰዋል። ኢየሱስ ከጥምቀቱ ቡኋላ በየዋህነተ የተሞላውን የምድራዊ አገልግሎቱን መጀመመሩን በማስታወስ አስተምህሮዋቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ሁሉም የክርስቶስ ተከታይ የሆኑ ሚስዮናዊያን በአገልግሎታቸውን ሁሉ ይህንን የክርስቶስ አብነት ማጸባረቅ ይኖርባቸዋል ካሉ ቡኋላ ሰዎች ላይ በመጮህ ወይም ሰዎችን በመዝልፍ ሳይሆን በጥንካሬ እና በፍቅር በተሞላ የሕይወት ምሳሌን በማሳየት ክርስቶስን መመስከር ይገባል ብለዋል።

ቅዱስነታቸው ከምዕመናን ጋር በመቀባበል ካሳረጉት የመልዐከ እግዚኣብሔር ጸሎት ቡኋላ ለምዕመናን እንዳሳሰቡት በጎዳና ላይ የሚኖሩ ሰዎችን በተለይም ደግሞ በጎዳና ላይ በመኖራቸው የተነሳ በከፍተኛ ብርድ ምክንያት ነብሳቸውን እያጡ የሚገኙ ሰዎችን ማስታወስ ይገባል ካሉ ቡኋላ እነዚህን ሰዎች መርዳት እንድንችል እግዚኣብሔር ልባችንን ያራራልን ዘንድ መጸለይ ያስፈልጋል ካሉ ቡኋላ የእለቱን አስተምህሮዋቸውን አጠናቀዋል።

በተያያዘ ዜናም አሁን በመላው አውሮፓ የሚታየውን ከፍተኛ ቅዝቃዜን ምክንያት በማድረግ የመኖሪያ ስፍራ በማጣታቸው ምክንያት በየጎዳናው ላይ የሚገኙ ሰዎችን ይህ ከፍተኛ የቅዝቃዜው ወቅት እስክያልፍ ድረስ በቅድስት መንበር ሥር የሚታዳደሩ 3 የእንግዳ መቀባያ ስፍራዎች በጎዳና ላይ ለሚኖሩ ሰዎች ክፍት እንደሚሆኑ የተገለጸ ሲሆን በተጨማሪም ይህንን ቅዝቃዜ መቋቋም የሚያስችሉ አልባሳትም በየጎዳንው ላይ ለሚኖሩ ሰዎች በነጻ እንደ ሚታደልም ለመረዳት ተችሉዋል።

 








All the contents on this site are copyrighted ©.