2016-12-30 17:17:00

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ እ.አ.አ. በ2016 ያካሄዱት አበይት ተግባራት እና የገጠሙዋቸው ተግዳሮቶች።


እንደ አውሮፓዊያኑ የቀን አቆጣጠር 2016 ዓ.ም. በመገባደድ ላይ ይገኛል። 2016 ዓ.ም. ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በጣም ብዙ ሥራ የበዛበት፣ 7 ሀገራትን የጎበኙበት፣ አነጋጋሪ ሆኖ ያለፈውን አሞሪስ ላይቲሲያ በአማሪኛው የፍቅር ሐሴት የተሰኘውን በቤተሰብ ዙሪያ የሚያጠነጥነውን ቃለ ምዕዳን የጻፉበት እንዲሁም ቅዱስ ልዩ የምሕረት ዓመት የተከበረበት፣ አጠቃላይ አስተህሮን ለምዕመናን ያደረጉበት፣ በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት መስዋዕተ ቅዳሴን ያሳረጉበት እና የቅድስት መንበር አጠቃላይ መዋቅር እንዲታደስ ያደረጉበት ዓመት ነው።

በተለይም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በእዚህ በመጠናቀቅ ላይ በሚገኘው የአውሮፓዊያኑ አመት ምዕመናን ሥር ነቀል የሆነ መንፈሳዊ ለውጥ እንዲያደረጉ ከፍተኛ ጥረት ያደርጉበት፣ በተለይም ቤተ ክርስቲያን ምዕመናኖቹዋ በወንጌል የሚገኘውን ደስታ በመሞላት ይህንንም ደስታ በዓለም ሁሉ ውስጥ ያዳርሱ ዘንድ ቤተ ክርስቲያን ጥረት እንድታደርግም በተደጋጋሚ ጥሪ ያቀረቡበት ዓመት ነው።

ቅዱስ ወንጌል መሰረቱን ያደረገው በሕግ ላይ ሳይሆን በእግዚኣብሄር ፍቅር ላይ ነው የሚለው misericordia et Misera ወይም በአማርኛው በግርድፉ ሲተረጎም (ምሕረት እና አሳር)  (የእግዚኣብሔር ምሕረት እና የሰው ልጅ አሳር) የተሰኘው የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ ሐዋሪያዊ መልዕክት ዋነኛው የ2016 ዓ.ም. የቅዱስ ልዩ የምሕረት አመት የማጠቃለያ መልዕክት ሆኖም ይቆጠራል። 

ቅዱስነታቸው በእዚህ እንደ አውሮፓዊያኑ የቀን አቆጣጠር እየተገባደደ በሚገኘው የ2016 ዓ.ም. በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ “ሕግ የተደነገገበት ዋንኛው ምክንያት እኛን የሕግ ባሪያዎች ለማድረግ ታስቦ ሳይሆን ነገር ግን ነጻ ልያደርገን እና የእግዚኣብሔር ልጆች እንድንሆን ይረዳን ዘንድ ነው” ይሉ እንደ ነበረም ይታወሳል። ቅዱስነታቸው በተጨማሪም ሕግን አክርሮ መያዝ እብሪተኛ እንድንሆን በማድረግ እኛ ከሌሎች የተሻልን ሰዎች ሆነን እንዲሰማን ያደርገናል።

ስለዚህም በእግዚኣብሔር ሕግ ላይ ተመርኩዞ መመላለስ አስፈላጊ ነው የሚለውን አክራሪ የሆነ አስተሳሰብ ለያዙ ሰዎች ሁሉ መጸለይ ያስፈልጋል። በተጨማሪም ጌታ እግዚኣብሔር አባት፣ ምህረትን የሚወድ፣ ርኅሩ፣ መልካም፣ ትሁት እና የዋሕ እንደ ሆነ ይረደ ዘንድ እንዲረዳቸው መጸለይ ያስፈልጋል፣ ይህም ሁላችንም ልንከተለው የሚገባው ባሕሪ ሊሆን ያስፈልጋል ማለታቸውም ያታወሳል።

የቅዱስነታቸው የ2016 ዓ.ም. ዋነኛ የአስተምህሮዋቸው ትኩረት ሆኖ የቆየው እራሳችሁን ድንገተኛ ለሆነው ለመንፈስ ቅዱስ ጣልቃ ገብነት ክፍት አድርጉ ማለታቸውም የታወቀ ሲሆን ከመጀመሪያው ክፍለ ዘመን አንስቶ መንፈስ ቅዱስ ነው ቤተ ክርስቲያንን እየመራ ወደ ፊት እንድትራመድ ያደርጋት የነበረው፣ አዲስ መንገድ እንድትከተል ስያደርጋት የነበረውም መንፈስ ቅዱስ ነው፣ የእግዚኣብሔርንም አዲስ ግልጸት ቤተ ክርስቲያን እንድትቀበል የሚያደርጋትም መንፈስ ቅዱስ ነው ማለታቸውም ያታወሳል።

ከመጀመሪያው አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ ቤተ ክርስቲያን የምትከተለው ጎዳን ይህንኑ ነው። መንፈስ ቅዱስ አዲስ  የሚመስሉ ነገሮችን በሚገልጽበት ወቅቶች ሁሉ “እንደ እዚህ ያለ ነገር በፍጹም ተደርጎ አይታወቅም!” “እንደ እዚህ ሊደረግ አይገባም!”  በማለት መቃወም ተገቢ አይደለም በማለት በተለይም ደግሞ የቅድስት መንበር አስተዳደር መታደስ አለበት በማለት በቁርጠኛነት ተግባራቸውን በማከናወን ላይ የሚገኙ ቅዱስነታቸው እየገጠማቸው የሚገኘውን ተግዳሮቶችን ከእዚህ አስተሳሰብ ጋር አነጻጽረው ተናግረዋል።

ቅዱስነታቸው የህንን የህዳሴ ጉዞን ለሚቃወሙ ሰዎችን ሁሉ የሁለተኛው የቫቲካን ጉባሄ በተከናወነበት ጊዜ ከነበረው ከፍተኛ ተቃውሞ ጋር አነጻጽረዉታል። ዛሬም ቢሆን በአንድ መንገድ ይሁን በሌላ መፈስ ቅዱስ የቤተ ክርስቲያን ሕዳሴን በማከናወን ወደ ፊት እየተጓዘ ይጋኛል። ቅዱነታቸው በተደጋጋሚ እንደ ገለጹት ቤተ ክርስቲያን ልትከተለው የሚገባት መንገድ የሕብረት፣ የማዳመጥ፣ የመወያየት፣ የመጸለይ እና ቁርጠኛነትን የተከተለ መንገድ መጓዝ ይኖርባታል ይሉ እንደ ነበረ ይታወሳል።

ቅዱስነታቸው በእዚህ በመገባደድ ላይ በሚገኘው የአውሮፓዊያኑ የ2016 ዓ.ም. ሰይጣን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ክፍፍልን በመፍጠር ቤተ ክርስቲያንን ሊያፈራርሳት ይፈልጋል በማለት አጽኖት ሰጥተው መንጋራቸውም ይታወቃል። ስለእዚህም አሉ ቅዱስነታቸው ይህንን የሰይጣንን ሴራ ለማክሸፍ ያስችለን ዘንድ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሕብረት እንዲመጣ መሥራት ያስፈልጋል ማለታቸውም ያታወቃል።

ምክንያቱም አሉ ቅዱስነታቸው “በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚከሰተው ክፍፍል የእግዚኣብሔር መንግሥት እንዳያድግ ያደርጋል፣ ጌታ ማን እንደ ሆነ በሚገባ እንዳይታይም ያደርጋል”። ስለእዚም ቤተ ክርስቲያን እንዳትፈራርስ የተቻለንን ነገር ሁሉ ማድረግ ይጠበቅብናል። ቅዱስነታቸው አክለውም ቤተ ክርስቲያን ሕይወት ያላት አካል በመሆኑዋ የተነሳ ቀጣይነት ባለው መልኩ መታደስ ይኖርባታል፣ ትክክለኛ ለውጥ እንዲመጣ የሚያደርጉትም ሁሉ ቅዱሳን ናቸው ማለታቸውም ይታወሳል።

 








All the contents on this site are copyrighted ©.