2016-12-24 12:51:00

ቅዱስነታቸው በቅድስት መንበር ሥር በሚተዳደሩ ተቋማት ውስጥ ለሚሠሩ ሠራተኞች የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ።


ቅዱስ አባታችን ፍራንቸስኮ በታኅሣሥ 13/2009 ዓ.ም. እንደ አውሮፓዊያን የቀን አቆጣጠር በቅርብ ቀን የሚከበረውን የገና እና የአዲስ ዓመት መለወጫን አስመልክተው ለእርሳቸው የቅርብ የሥራ ተባባሪዎች ብጹዐን ካርዲናሎች እና ለቅድስት መንበር አስተዳደር አበይት አካላት ጋር ተገናኝተው እና የቅድስት መንበር እያደረገችው የምትገኘውን ተሐድሶ እውን ይሆን ዘንድ ሁሉም የሚመለክታቸው አካልት ተቀናጅተው መሥራት እንዳለባቸው ከገለጹ ቡኋላ በቫቲካን ወደ ሚገኘው የጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ በማምራት በቅድስት መንበር ሥር በሚተዳደሩ ተቋማት ውስጥ ከሚሠሩ ሠራተኞች ጋር በመገናኘት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ማስተላለፋቸው ተገልጹዋል።

የእዚህን ዜና ሙሉ ይዘት ከእዚህ በታች የሚገኘውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ።

ቅዱስነታቸው በግንኙነቱ ወቅት ባስተላለፉት መልእክት እንደ ገለጹት የሥራ እንድል የሰጣችሁን እግዚኣብሔርን በቀዳሚነት ማመስገን ይገባችኋል ካሉ ቡኋላ በሥራችሁ የምታገለግሉዋቸውን ሰዎች መብታቸውን እና ክብራቸውን በጠበቀ መልኩ ማስተናገድ ይጠበቅባችኋል ማለታቸውም ታውቁዋል።

“ሥራ ለሚሠራ ሰው እና ለቤተሰቡ አስፈላጊ ነገር ነው” በማለት መልእክታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “ለተሰጣችሁ የሥራ እድል እግዚኣብሔርን በማመስገን በዓለም ዙሪያ ሥራ መግኘት ላልቻሉ፣ ወይም ደግሞ ተገቢ ያልሆነ ሥራ ለሚሰሩ፣ በጣም ዝቅተኛ ክፍያ ለሚከፈላቸው፣ ጤናቸውን አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል አደገኛ የሆነ ሥራ ለሚሰሩ ሰዎች ሁሉ መጸለይ ይገባል” ብለዋል።

“የተሰጠንን የሥራ ኋላፊነት በሚገባ ለመወጣት ቁርጠኛ መሆን ይኖርባቹኋል” በማለት መልእክታቸውን የቀተሉት ቅዱስነታቸው በተለይም ደግሞ ተገቢ የሆነና ክብር ያለው ሥራ በማከናወን የእናንተን አገልግሎት የሚሹትን ሰዎች ሁሉ በማክበር እና በታማኝነት ማገልገል ይጠበቅባችኋል ብለዋል።

“በተለይም በእዚህ በቫቲካን ሥር የሚተዳደሩ ተቋማት ውስጥ ይህንን ተግባር በተጠናከረ ሁኔታ ማከናወን ይጠበቅብናል ብለው ምክንያቱም እኛ ወንጌልን የማብሰር ተግባር የምናከናውን በመሆናችን የተነሳ የቤተ ክርስቲያናችንን የማኅበራዊ አስተምህሮን የመተግበር ሞራላዊ ግዴታ ስላለብንም ጭምር ነው ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው ማብቂያ ላይ እንደ ጠቀሱት ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት በስኬት ለተጠናቀቀው ልዩ ቅዱስ የምሕረት አመት መስካት ላደረጉት ጥረት አመስግነው ሁሉንም ሠራታኞች እና ቤተሰቦቻቸውን በጸሎታቸው እንደ ሚያስቡዋቸው ገልጸው በተለይም ደግሞ በበሽታ የሚሰቃዩትን፣ የእድሜ ባለጸጎችን  ለየት ባለ ሁኔታ እንደ ሚያስቡዋቸው ገልጸው እና ሁሉም ሠራተኞች ለእርሳቸው ጸሎት ያደርጉ ዘንድ ጥሪ ካደረጉ ቡኋላ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት በድጋሜ አስተላልፈው መልእክታቸውን አጠናቀዋል።

 








All the contents on this site are copyrighted ©.