2016-12-13 09:54:00

ቅዱስነታቸው በስቃይ እና በመከራ ውስጥ የሚገኙትን የአሌፖ ከተማ ነዋሪዎችን ዓለም በፍጹም ሊዘነጋቸው አይገባም አሉ።


ቅዱስ አባታችን ፍራንቸስኮ በትላንትነው እለት ማለትም በታኅሣስ 2/2009 ዓ.ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ምዕመናን እና የሀገር ጎብኝዎች በተገኙበት ከመልዐከ እግዚኣብሔር ጸሎት በፊት ባስተላለፉት የተለመደው መልዕክታቸው እንደ ገለጹት ዓለም በስቃይ እና በመከራ ውስጥ የሚገኘውን በሶሪያ የእርስ በእርስ ጦርነት ከፍተኛ ውድመት እየደረሰበት ያለውን የአሌፖ ከተማ ነዋሪዎችን መዘንጋት እንደ ሌለብት ማሳሰባቸው ተገለጸ።

በሩሲያ የሚደገፉ የሶሪያ መንግሥት ወታደሮች በአማጺያን እጅ ከሁለት ዓመት በፊት የወደቀችሁን የአሌፖ ከተማን መልሶ ለመቆጣጠር ከፍተኛ የሆነ የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ መክፈታቸው የታወቀ ሲሆን በእዚህ ግጭት የተነሳ በባለፉት ጥቂት ሊባሉ በሚችሉት ሳምንታት በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው ይታወቃል።

“በእዚህ ታላቅ የስቃይ ሥፍራ ለሚገኙ ሰዎች በየቀኑ ጸሎት በማድረግ በስቃያቸው ማዘኔን በመግለጽ ላይ እገኛለው” ያሉት ቅዱስነታቸው ሊረሳ የማይገባው ጉዳይ በአሌፖ ከተማ ቤተሰቦች፣ ልጆች፣ አረጋዊያን የታመሙ ሰዎች. . . የመሳሰሉት እንደ ሚኖሩባት በፍጹም መዘንጋት የለበትም ካሉ ቡኋላ አለመታደል ሆኖ በሚገርም ሁኔታ  በከፍተኛ ሁኔታ ከጦርነት ዜና ጋር ተለማምደናል ነገር ግን በተለይም ብዙ ታሪክ፣ ባሕል እና እምነት ያላት ሶሪያ በፍጹም መረሳት የለባትም ብለዋል።

“እኛ ስለእዚህ ጦርነት የሚነግሩንን የተዛባ እና ሐሰት የሆኑ ዜናዎችን በመስማት ይህ ጦርነት አዎንታዊ የሆነ ገጽታ አለው ብለን አንቀበልም” ያሉት ቅዱስነታቸው “እኛ የምንመርጠው ስልጣኔን እንጂ ጥፋትን ባለመሆኑ የተነሳ ሁላችሁም ይህ ጦርነት ማብቂያ ያገኝ ዘንድ የየበኩላችሁን ጥረት እንድታደርጉ ጥሪ አቀርባለው፣ ሰላም ይሰፍን ዘንድ አዎንታዊ የሆነ ተግባር በመፈጸም ሶሪያ በተለይም ደግሞ ለአሌፖ ሕዝቦች ያለንን አጋርነት መግለጽ ያስፈልጋል” ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው ማብቂያ ላይ ምዕመናን ስሜታዊ ወይም የታይታ የሆነ ደስታን በአጠቃላይም ዓለማዊ የሆነ ደስታን ማስወገድ እንደ ሚጠበቅባቸው ገልጸው በአንጻሩም ትክክለኛውን እና ውስጣችንን በሚነካው ደስታ በመሞላት የጌታችንን መምጣት መጠባበቅ እንደ ሚገባቸው ካሳሰቡ ቡኋላ ቡራኬን ሰጥተው ምዕመናን ተሰናብተዋል።

 

 








All the contents on this site are copyrighted ©.