2016-12-13 09:21:00

ቅዱስ አባታችን ፍራንቸስኮ በፑሊያ ጠቅላይ ግዛት የሚገኘውን ጳጳሳዊ ዘረዐ ክህነት ጎበኙ።


ቅዱስ አባታችን ፍራንቸስኮ በታኅሣሥ 1/2009 ዓ.ም. በፑሊያ ጠቅላይ ግዛት በሚገኘው  በፒዮስ 6ኛ ጳጳሳዊ የዘረዐ ክህነት ተማሪዎች መኖሪያ ተገኝተው ከዘረዐ ክህነት ተማሪዎች ጋር መወያየታቸው የታወቀ ሲሆን በእለቱም ቅዱስነታቸው ያስተላለፉት መልዕክት ማዕከሉን አድርጎ የነበረው “የአባልነት ስሜት” በሚል ጭብጥ ዙሪያ ላይ ያጠነጠነ እንደ ነበረም ተገለጸ።

“እናንተ የክርስቶስ የአካል ክፍል፣ የቤተ ክርስቲያን አባል፣ የእግዚኣብሔር መንግሥት ተካፋዮች መሆናችሁ ሲሰማችሁ ብቻ ነው በዘረዐ ክህነት ቆይታችን ልትዘልቁ የምትችሉት” ያሉት ቅዱስነታቸው በማንኛውም ሁኔታ ራሳቸውን ጤናማ ባልሆነ መልኩ ራስን ከማምለክ ዝንባሌ ራሳቸውን እስከ አላላቀቁ ድረስ  የጥሪ ሕይወታቸውን በትክክል ማስክሄድ እንደ ሚያዳግታቸው ገልጸው ይህንን ፈተና በንቃት መከታተል እንደ ሚኖርባቸውም ጨምረው አሳስበዋል።

የዘረዐ ክህነት ከሌሎች ጋር  እንዴት ግንኙነት መፍጠር እንደ ሚቻል የምትማሩበት ስፍራ ነው በማለት ንግግራቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ይህም አሁን በዘረዐ ክህነት ሕይወታችሁ የሚትቀስሙት ክህሎት ካህን በምትሆኑበት ሰዓት በከፍተኛ ሁኔታ በክህነት ሕይወታችሁ እንደ ስንቅ ሆኖ እንደ ሚረዳቸው ገልጸዋል።

በመጨረሻም ቅዱስነታቸው እንደ ገለጹት “የአባልነት ስሜት” የሚለውን ሀረግ መረዳት የሚገባን በተቃራኒው የሚገኘውን ቃል ማለትም “ራስን ማግለል” በሚለው ጭብጥ ውስጥ አስገብተን መመልከት ይገባናል ካሉ ቡኋላ የዘረዐ ክህነት ተማሪዎች ዋንኛ ተግባራቸው ለሚያገኙዋቸው ሰዎች ክርስቶስን በማሳወቅ የክርስቲያን ማሕበረሰብ አባላት እንዲሆኑ ማድረግ መሆን እንደ ሚገባው ጠቅሰው ይህንንም መተግበር መጀመር የሚጠበቅባቸው በዘረዐ ክህነት ውስጥ ተገልለው የሚገኙ ወንድሞቻቸውን በማቅረብ ሊሆን እንደ ሚገባም አሳስበው የአባልነት ስሜት መሰማት ማለት ታላቅ ሐላፊነት መሆኑን ካሉ ቡኋላ በዘረዐ ክህነት ለሚሰጠው የሕነፃ ትምሕርት ከፍተኛ የሆነ ትኩረት ይሰጡ ዘንድ አሳስበው ንግግራቸውን አጠናቀዋል።

 








All the contents on this site are copyrighted ©.