2016-11-28 16:20:00

ማእከላዊት ረፓብሊክ አፍሪቃ


እንደምናስታውሰው የዛሬ አንድ ዓመት በፊት በማእከላዊት ረፓብሊክ አፍሪቃ ርእሰ ከተማ ባንጉዪ ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮ ቅዱስ በር በመክፈት ያስጀመሩት እ.ኤ.አ. ህዳር 20 ቀን 2016 ዓ.ም. የተጠናቀቀው ልዩ የምሕረት ዓመት በማስመልከት በማእከላዊት ረፓብሊክ አፍሪቃ በወንጌላዊ ተልእኮ አገልግሎት 25ኛ ዓመታቸውን ያስቆጠሩ ለተወሰነ የእረፍት ቀናት እዚህ ኢጣሊያ ለጊዜው የሚገኙት ኢጣሊያዊ ልኡከ ወንጌል ኢተጫሚ ቀርመለሳውያን ገዳም አባል አባ አውረሊዮ ጋዘራ ከቫቲካን ረዲዮ ጋር ባካሄዱት ቃለ ምልልስ፥ በእውነቱ የዚህ በቅርቡ የተጠናቀቀው ልዩ የምሕረት ዓመት ወጤት እየታየ ነው። በመካከለኛይቱ ረፓብሊክ አገር ያለው ሁኔታ እየተሻሻለ ነው። ችግሮቹ በሞላ ተቋጭተዋል ለማለት ባይቻልም የሚፈለገው ለውጥ በውይይት ብቻ ተከዋኒ እንደሚሆን በመደጋገም ቅዱስ አባታችን የሰጡት ምዕዳን ሰፊ እማኔ እያገኘ መጥቷል። ይኽ ደግሞ ቅዱስ አባታችን በዚያች አገር ሐዋርያዊ ጉብኝት በማካሄድ ቅዱስ በር በመክፈት ውይይት ብቻ የችግሮቻችን መፍትሔ ነው ሲሉ በአጽንኦት ያሰመሩበት ህሳብ ተደማጭነት እያገኘ መሆኑ የሚመሰክር ነው ብሏል።

በአገሪቱ የተካሄደው ሕዝባዊ ምርጫ ያስገኘው ውጤት ለሕዝቡ ጥያቄና አገሪቷ አጋጥሟት ያለው ችግር በሚገባ በመተንተን ለመፍታት ያቀና መሆን አለበት በእውነቱ ከዚህ አንጻር ሲታይ ገና ብዙ መሠራት እንዳለበት ነው የምንረዳው።

ኢጣሊያ ለመካከለኛይቱ ረፓብሊክ አፍሪቃ እ.ኤ.አ. ከ 2017 እስለ 2019 ዓ.ም. አምስት ሚሊዮን ኤውሮ ለዳግመ ግንባታ እርዳታ ለመስጠት ቃል መግባቷ ገልጠው በቅርቡ በብራሰልስ የኤውሮጳ ኅብረት አገሮች ለማእከላዊት ረፓብሊክ አፍሪቃ ድጋፍና ትብብር በሚል ርእስ ሥር በተካሄደው ጉባኤ መሳተፋቸውና ኅብረቱ ለአገሪቱ ድጋፍ ብዙ ጥረት እያደረገ ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በበኩልም ብዙ ሥራዎችን እያከናወነ ቢሆንም ቅሉ ውጤት አጥጋቢ አይደለም በቦዞኡም ከተማ የነበሩት 400 የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታ አስከባሪ ኃይል አባላት ክልሉን ለቀው ወጥቷል። በዚያ ክልል አሁንም ታጣቂ ኃይሎች እንዳሉና ብዙ ችግር እያስከተሉ ባሉበት በአሁኑ ወቅት ክልሉን ለቆ መውጣት ተቀባይነት የሌለውና ምክንያቱ ምን ይሆን ለመገመቱም ሆነ ለመረዳቱ የሚያዳግት ነው። የጸጥታ ኃይሎቹ ብዙውን ጊዜ የአገሪቱ ብሔራዊ ቋንቋ የሆነውን ፈረንሳይኛን ጨርሰው የማያውቁ በመሆናቸው ከሕዝቡ ጋር ለመወያየት የማይችሉ መግባባትና ስለ ሁኔታውም ከሚመለከተው አካል ቀርቦ ለመወያየት በጣም እክል የሚያጋጥማቸው ሆነው ነው የሚታዩት። ስለዚህ በጠቅላላ በአገሪቱ ያለው ችግር ግምት ውስጥ በማስገባት የተባበሩት መንግሥታት ድጋፍ ዘርፈ ብዙ መሆን ይገባዋል። ለምሳሌ የጤና ጥበቃው ጉዳይ የትምህርትና ሕንጸት በተመለከተ ያለው ችግር እግጅ አሳሳቢ ነው። በመሆኑም በዚሁ ጉዳይ ድጋፍና ትብብር እጅግ ያስፈልጋል ብሏል።

ኣሳቸው በሚኖሩበት ባንጊዪ በሚገኘው የማኅበሩ ገዳም ውስጥ እ.ኤ.አ. ከ 2013 ዓ.ም. ጀምሮ መጠለያ የተሰጣቸው 3 ሺሕ ተፈናቃዮች እንዳሉም ጠቅሰው። በአየር ማረፊያው ባለው ክልል ጭምር 20 ሺሕ ተፈናቃዮች ይገኛሉ ብለው። በአገሪቱ ያለው ችግር እንዲፈታ ከተፈለገ በእውነቱ ዓለም አቀፋዊ ገብነት ወሳኝ ነው። የተፈናቀለው ቤቱንና ንብረቱን ለቆ የወጣው ሕዝብ ወደ ቤቱና ወደ መጣበት ክልል ለመመለስ የሚፈልግ ቢሆንም እንዲመለስ የሚያበቃው ዋስትና የሚሰጠው ተስፋና ድጋፍ ከሁሉም በላይ ሰላምና መረጋጋት ያስፈልገዋል።

በመጨረሻም በቅርቡ ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮ ለካርዲናልነት ማእርግ ከሾሟቸው ውስጥ አንዱ በአገሪቱ ቀዳሜ ካርዲናል ለመሆን የበቁት የባንጉዪ ሊቀ ጳጳሳት ብፁዕ አቡነ ንዛፓላይንጋ ናቸው። ይኽ ቅዱስ አባታችን ለአገሪቱ የሰጡት አቢይ ስጦታ ቅዱስነታቸው በችግር ውስጥ ያለው የማእከላዊት ረፓብሊክ አፍሪቃ ሕዝብ ቅርብ  መሆናቸውና የአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ በሚገባ እንደሚከታተሉ የሚያረጋግጥ ነው፡  በብሔራዊ አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለአገሪቱ ሰላምና ግንባታ አቢይ ድጋፍ ነው በማለት ያካሄዱት ቃለ ምልልስ አጠቃሏል።








All the contents on this site are copyrighted ©.