2016-10-17 13:48:00

ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮ ለሰባት ሰማዕታት የቅድስናን ማዕረግ መስጠታቸው ታወቀ።


ቅዱስ አባታችን ፍራንቸስኮ በትላንትናው እለት ማለትም በጥቅምት 6/2009 ለሰባት ሰዎች ለቤተ ክርስቲያን፣ ለእምነታቸውና ለማሕበረሰቡ ባበረከቱት መልካም አብነት የቅድሳናን ማዕረግ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ መስጠታቸው ታወቀ።

ቅዱስነታቸው በእለቱ ባሰሙት ስብከት እንደ ገለጹት “ቅዱሳን የምንላቸው ሙሉ በሙሉ የጸሎት ምስጢር ውስጥ የገቡ  ወንዶች እና ሴቶች ሰዎች ናቸው፣ እነዚህም ሰዎች መንፈስ ቅዱስ ለእነርሱ እንዲጸልይና አብሮዋቸው እንዲታገል የፈቀዱ በጸሎት የታገሉ ሰዎች ናቸው” ማለታቸው ተገልጹዋል።

የቅድስናን ማዕረግ ከተሰጣቸው ሰዎች መካከል አንድ የአርጄንቲና፣ ሁለት የጣሊያን፣ ሁለት የፈረንሳይ፣ አንድ እስፔናዊና ጆዜ ሳንኬስ የተባለ አንድ መክሲኮአዊ ወጣት በጊዜው በሜክሲኮ በነበረው ስርዐት ለእምነቱ ሲል መስዋዕትነትን የከፈለው ሰማዕት እንደ ሚገኝበት የታወቀ ሲሆን በእለቱም ይህን የቅድስና ስነ-ስርዓት ለመከታተል በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከ80,000 በላይ ምዕመናን መገኘታቸውና ከእነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ የአርጄንቲናን ሰንደቃላማ የያዙ ይህንን ታላቅ በዓል ለመታደም የተገኙ አርጄንቲናዊያን መሆናቸው የታወቀ ሲሆን የአርጄንቲና ፕሬዚዳንት ማውሪሲዮ ማክሪ እና ቤተሰቦቻቸውም እንደሚገኙበት ታውቁዋል።

ቅዱስነታቸው በመግቢያ ስነ-ስርዓት ላይ “ጌታ ሆይ አንተን ሁልጊዜ በታማኝነትና በንጹዕ መንፈስ ማገልገል እንድንችል  በእኛ ውስጥ ለጋስና ጽኑ ልብን ፍጠርልን” የሚለውን ጸሎት ለእግዚኣብሔር ማቅረብ ተገቢ ነው በማለት የገለጹት ቅዱስነታቸው በራሳችን ጥረት ይህንን ዓይነት ልብ ልናገኝ አንችልም እግዚኣብሔር ብቻ ነው ይህንን አይነት ልብ ሊሰጠን የሚችለው ስለዚህም በጸሎታችን እግዚኣብሔር ይህንን ስጦታ እንዲሰጠን ልንጸልይ ያስፈልጋል በእዚህም ረገድ ብቻ ነው ልክ በዛሬው ሰንበት የእግዚኣብሔር ቃል የተገለጸውን ጠቅሰው የጸሎትን ጭብጥ መረዳትና ሁላችንም እዚህ ለቅድስና ማዕረግ ሹመት በዓል የተገኘን ሰዎች ሁላችን ይህን የጸሎት አስፈላጊነት መገንዘብ የምንችለውም በእዚሁ መልኩ ብቻ ነው ብለዋል።

እነዚህ ቅዱሳን ያለሙትን ግብ መተዋል በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ለጸሎት ምስጋና ይግባውና ለጋስና ጽኑ የሆነ ልብ ነበራቸው በጣም ይጸልዩ ነበር፣ በጣምም ተዋግተው አሸናፊ ለመሆንም በቁ ብለዋል።

ስለዚህም በዛሬው እለት የመጀመሪያ ምንባብ እንደ ተጠቀሰው ከአማሌቅ ጋር በውጊያ ላይ በነበረበት ወቅት በተራራ ላይ እጆቹን ዘርግቶ ቆሞ እንደ ነበረውና ከሁሉም በላይ የእግዚኣብሔር ሰውና የጸሎት ሰው እንደነበረው ሙሴ መጸለይ ይገባናል! በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ቀስ በቀስ ግን በድካም ምክንያት እጆቹ መታጠፍና ወደታች መውረድ ጀምረው ነበር በዚህም የተነሳ የሕዝቡ የድል ግስጋሴ መዳከም መጀመሩን ገልጸው አሮንና ሁር ሙሴን በድንጋይ ላይ ቆጭ እንዲል ካደረጉት ቡኋላ ክንዶቹ ሥር ድጋፍ በማስገባትና ቀና አድርገው ድል እስኪጎናጸፉ ድረስ መርዳታቸውን ገልጸዋል።

የእዚህ ዓይነቱ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚንጸባረቅ መንፈሳዊነት የሚጠይቁ ትግሎችን ማሸነፍ የምንችለው በጦርነት ሳይሆን በሰላም መንገድ ብቻ ነው በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው  ከሙሴ ታሪክ ብዙ ነገሮችን መማር እንችላለን ይህም ለጸሎት በምናሳየው ጽናት ውስጥ የሌሎች ድጋፍ እንደምያስፈልገን በከፍተኛ ሁኔታ እንማራለን ካሉ ቡኋላ ድካምን ልናስወግደው የምንችለው ነገር አይደለም፣ አንድ አንዴም እንዲሁ በዘፈቀደ ከድካማችን የተነሳ ጉዞዎቻችንን እንገታለን ነገር ግን በወንድሞቻችን እና በእህቶቻችን ድጋፍ ጌታ በእኛ በኩል ልያከናውነው የፈለገውን ሥራ እስኪጠናቀቅ ድረስ የእኛ በጸሎት መጽናት ያስፈልጋል ብለዋል።

ቅዱስ ሐዋሪያው ጳውሎስ የእርሱ ተከታይና የሥራ ተባባሪ ወደ ነበረው ወደ ጢሞቴዎስ በጻፈው መልዕክቱ የተማረውንና ያመነበትን ነገር አጥብቆ መያዝ እንዳለበት ገልጾ ነበር በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ነገር ግን ጢሞቴዎስ ይህንን ተግባር በግል ጥረቱ ብቻ ማከናወን አይችልም ምክንያቱም ለጽናት የሚደረገው ትግል ያለጸሎት መከናወን አይችልም ካሉ ቡኋላ አልፎ አልፎ የሚሆን ወይም ፍራ ተባ ያለ ጸሎት ሳይሆን የሚያስፈልገው፣ ነገር ግን ኢየሱስ በሉቃስ ወንጌል (ሉቃስ 18.1) እንደ ነገረንና እንዳስተማረን “ሳይታክቱ መጸለይ እንደ ሚገባ” መወቅ ይኖርብናል ብለዋል።

ይህም የክርስቲያን የሕይወት መነገድ ሊሆን ይግባል በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው በጽናት በእምነት ጸንቶ ለመቆም እንዲቻልና ምስክርነትን ለመስጠት እንዲቻል ሳይታክቱ በጸሎት መትጋት አስፈላጊ መሆኑን ከገለጹ ቡኋላ ይህንንም በምናደርግበት ወቅት በልባችን ውስጥ “ነገር ግን ጌታ ሆይ እንዴት ነው ሳይታክቱ መኖር የሚቻለው? እኛ ሰዎች ነን ሙሴም እንኳን ታክቶት ነበር! የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል ብለው ይህም እውነተኛ ጥያቄ ነው ካሉ ቡኋላ ከሙታን የተነሳው ለክርስቶስንና ለመንፈስ ቅዱስ መኖር ምስጋና ይግባውና ክንዶቹዋን ዘወትር ቅንና ሌሊት ወደ ሰማይ የተዘረጋው የክርስቶስ የአካል ክፍል የሆነችሁ የቤተ ክርስቲያን አባላት በመሆናችን የእርሱ የአካል ክፍሎች ነን እንጂ ብቻችንን አይደለንም ብለው ለቤተ ክርስቲያን እና ለቤተ ክርስቲያን ጸሎት ምስጋና ይግባውና በእምነታችን ጸንተን የምንኖረው እና መመስከር የምንችለው በቤተ ክርስቲያን ድጋፍ ብቻ ነው ብለዋል።

ኢየሱስ በዛሬው ወንጌል “እግዚኣብሔር ቀንና ሌሊት ወደ እርሱ ለሚጮኹ ምርጦቹ አይፈርድላቸውምን ?” (ሉቃስ 18.7) ብሎ ቃል መግባቱን ሰምተናል በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ይህም የጸሎት ምስጢራዊነትን የሚገልጽ ነው ተስፋ ሳንቆርጥ ሳንታክት ጩኸታችንን መቀጠል እንዳለብን ያስገነዝበናል በምንደክምበት ጊዜ ሁሉ ክንዶቻችን እንደ ተዘረጉ ይቆዩ ዘንድ የእርሱን ርዳታ መጠየቅ ይጠበቅብናል ብለዋል።

የዚህን አይነት ጸሎት ነው ኢየሱስ የገለጸልንና በመንፈስ ቅዱሱ አማካይነት የሰጠን በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው መጸለይ ማለት ሃሳባዊ በሆነ ዓለም ውስጥ መጠጊያ መፈለግ ወይም ደግሞ በውሸትና በግለኝነት ስሜት ውስጥ መሸሸግ ማለት አይደለም ካሉ ቡኋላ በተቃራኒው መጸለይ ማለት መታገል ማለት ነው በተጨማሪም መንፈስ ቅዱስ መጸለይ ስለሚያስተምረን፣ በጸሎታችን ወቅት እንዲመራንና የልጅነትን መንፈስ ተላብሰን መጸለይ እንችል ዘንድ መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን ይጸልይ ዘንድ ልንፈቅድለት ያስፈልጋል ብለዋል።

ቅዱሳን የሆኑ ወንድሞች እና እህቶች ሙሉ በሙሉ በጸሎት ምስጢር ውስጥ ራሳቸውን ያስገቡ ሰዎች ብቻ ናቸው በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው እነዚህም ሰዎች መንፈስ ቅዱስ ከእነርሱ ጋር አብሮ ይታገል ዘንድ የፈቀዱ፣ በጸሎት ኋይል የሚታገዙ ሰዎች እንደነበሩም ጠቅሰው እስከ መጨረሻ ድረስ በሙሉ ኋይላቸው ታግለው ድልን ተጎናጽፈዋል ነገር ግን የታገሉት በራሳቸው ኋይል ብቻ ሳይሆን በእነርሱ ውስጥና ከእነርሱ ጋር ሆኖ ድልን እንዲጎናጸፉ አብሮ በታገለው በጌታ እገዛ ነው ብለዋል።

እነዚህ ዛሬ የቅድስናን ማዕረግ ያገኙ ሰባት ቅዱሳን መልካሙን የእምነት ውግያ የተዋጉት በፍቅርና በጸሎት ኋይል ነው ያሉት ቅዱስነታቸው ለእዚህም ነው በእምነታቸው ጸንተው በፍቅርና በማይታክት ልብ እስከ መጨረሻ የቆዩት ካሉ ቡኋላ የእነርሱን አብነት በመከተልና በእነርሱ ምልጃ እግዚኣብሔር የጸሎት ሰዎች እንድንሆን ይርዳን ካሉ ቡኋላ ቀንና ሌሊት ወደ እግዚኣብሔር እንጮኸለንና እርስ በእርሳችን በጸሎት መደጋገፍ እንድንችልና መልኮታዊ ምሕረት ድል እስኪጎናጸፍ ድረስ ክንዳችን ወደ እርሱ ከፍ አድርገን መቆየት እንድንችል ጌታ ይርዳን ካሉ ቡኋላ ስብከታቸውን አጠናቀዋል።

 








All the contents on this site are copyrighted ©.